የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ስራ አስከያጅ ክቡር መልአከ ሕይወት አባ ኃይለ ገብርኤል ነጋሽ( ቆሞስ) የ2013 ዓ.ም በዓለ መስቀልን አስመልክተው የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላለፉ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
እንኳን ለ2013 ዓ.ም. ለጌታችንና ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ መስቀል በሰላምና በጤና አደረሳችሁ !!!

“የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት፥ ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነውና።”
/1ቆሮ. 1፡18 /

መስቀል በቤተ አይሁድ የርግማን ምልክት ፣ በቤተ አሕዛብ መራራ ቅጣት ፣ በቤተ ክርስቲያን ግን የድኅነት ሰሌዳ ነው ።
ጌታችን ሞታችንን ወደ ሕይወት እንደ ለወጠ ፣ የርግማን ምልክትንም የመባረኪያ ትእምርት አድርጎልናል ። ከጌታችን ሞትና ትንሳኤ ጀምሮ መስቀል በክርስቶስ ደም የተቀደሰ መንበር ፣ ሰማይና ምድርን ያገናኘ መሰላል ፣ ሕዝብና አሕዛብን ያጋጠመ ድልድይ ነው ።

መስቀል ዓለም ያወገዘቻቸውና የቀጣቻቸው ወንጀለኞች በጭንቅ የሚሞቱበት ሳይሆን መስቀል ኃጢአተኞች ስርየትን የሚያስታውሱበት የምሕረት መጥቅዕ ወይም ደወል ሁኗል ። ከክርስቶስ መስቀል በፊት ለኃጢአተኞች ፍርድ እንጂ ምሕረት አልነበረም ። መስቀልንም ባሰቡ ጊዜ ርግማንና የቅጣት ጽናትን ብቻ ያስቡ ነበር ።

ከክርስቶስ ሞት እና ትንሳኤ በኋላ ግን የሰው ልጅ በእግዚአብሔር የተወደደበት የፍቅሩ መግለጫ ሁኗል ።
ሰማይና ምድር የሚያገናኛቸው ምክንያትና አንቀጽ ጠፍቶ ነበር ። ወልደ እግዚአብሔር ሕያው ወልደ ማርያም ሥግው መድኃኔ ዓለም የማይገባውን ሞት በመቀበሉ ፣ የሰው ልጆች የማይገባቸውን ምሕረት አገኙ ። መስቀልም ጸጋን ማብሰሪያ ፣ የቸርነቱ አዋጅ መንገሪያ ሆነ ።

የመስቀልን በዓል ስናከብር የመስቀልን ትርጉም እየፈጸምን ሊሆን ይገባዋል ። የመስቀል ትርጉም ወደ ራስ መመልከት ፣ በሌሎችም አለመፍረድ ነው ። የሌሎችን ስምና ክብር መጠበቅ የመስቀል እሴት ነው ። በመስቀል መፈራረድ ቀርቶ ምሕረት ታውጇል ።

ሁላችንም በአንድነት የጠፋን መሆናችንን ተገንዝበን በአንድ መድኃኒት ተፈውሰናል ። ይህን መስቀል አይሁድ ክርስቶስን ከመጥላታቸው የተነሣ ሊያዩት አይፈቅዱም ። አሕዛብም ጣኦቶቻቸው የተዋረዱበት ነውና አይወዱትም ። እኛ ክርስቲያኖች ግን መንገደ ሰማይን ያገኘንበት ነውና እንወደዋለን ። ሁሉም ተቋም የራሱ ምልክት አለው ። አካለ ክርስቶስ የሆነችው ቤተ ክርስቲያንም ምልክትዋ መስቀል ነው ።

መስቀል ድኅነት ለሰው ልጆች የተሰጠበት ዘላለማዊ ዙፋን ነው ።
ባለ ዙፋኑን የምንወድ ከሆነ መስቀሉንም እንወደዋለን ። መስቀል ላይ ፍቅርና ፍትሕ ሙሉ ሁነዋል ። ዛሬም መሪዎች እንደ አባት ሕዝቡን መውደድ ፣ እንደ ዳኛም ያጠፉትን መገሠጽ ይገባቸዋል ።
ሰላም እንዲሆን ፍትሕ መጽናት አለበት ። መስቀል ይህን ሁሉ ትርጉም የያዘ የአማንያን ትምህርት ቤት ነው ።

በዓሉን የሰላም ፣ የፍቅርና የአንድነት ያድርግልን!!

ያየነውን ብርሃን ያጽናልን!!

ያስከፋንን ጨለማ ያርቅልን!!!

መልአከ ሕይወት አባ ኃይለ ገብርኤል ነጋሽ(ቆሞስ)

የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ

የአዲስ አበባ ሃይማኖት ተቋማት ቦርድ ሰብሳቢ