የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ስራ አስከያጅ ክቡር መልአከ ሕይወት አባ ኃይለ ገብርኤል ነጋሽ( ቆሞስ) የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላለፉ
❖የተከበራችሁ የሀገረ ስብከታችን የዋና ክፍል እና የክፍል ሐላፊዎች እንዲሁም ሠራተኞች፣
❖የተከበራችሁ የክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጆች እና ሠራተኞች፣
❖ውድ የገዳማትና የአድባራት አስተዳዳሪዎች፣ የሥራ ሓላፊዎችና ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣
❖ የተወደዳችሁ የሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎችና መላው ኦርቶዶክሳውያን የመንፈስ ልጆቻችን፣
እንኳን ከ2012 ዓ.ም. ዘመነ ዮሐንስ ወደ 2013 ዓ.ም. ዘመነ ማቴዎስ በሰላምና በጤና አሸጋገራችሁ ፣ አሸጋገረን !
” ለከ ውእቱ መዓልት ወዚኣከ ይእቲ ሌሊት ።
አንተ ፈጠርከ ፀሐየ ወወርኀ ።
ወአንተ ገበርከ አድባረ ምድር ኩሎ፤
ክረምተ ወሐጋየ ዘአንተ ፈጠርከ።”
“ቀኑ የአንተ ነው ሌሊቱም የአንተ ነው አንተ ፀሓዩንና ጨረቃውን አዘጋጀህ ። አንተ የምድርን ዳርቻ ሁሉ ሠራህ በጋንም ክረምትንም አንተ አደረግህ ።”
/መዝ. 73፡16-17/ ።
ዓለማትና ዘመናት ባለቤት አላቸው ። ባለቤታቸውም ፍጥረትን የፈጠረ ፣ ዘመናትን ያስጀመረ ልዑል እግዚአብሔር ነው ። ሃይማኖት የምንለውም ይህ ዓለም ፈጣሪና አስተዳዳሪ አለው ብሎ ማመን ነው ። በፍጥረቱ ፈጣሪነቱን ፣ በዘመናት ዑደት ደግሞ አስተዳዳሪነቱን የገለጠ እግዚአብሔር አምላካችን ነው ። እንደ ፈላስፎች አምላክ የለሽ ፣ እንደ ግሪካውያን ልዑልና ንዑስ አምላክ ብለን ምንታዌ አማልክትን ፣ እንደ ሰባልዮስ አካልን አጣፍተን ፣ እንደ አርዮስ የመለኮት ተዋረድ/ማዕረግ/ ሰጥተን ፣ እንደ አይሁድ አንድ ገጽ ብለን ፣ እንደ አረማውያን እንጨት ጠርበን ድንጋይ አለዝበን ፣ እንደ አሕዛብ ለእያንዳንዱ ፍጥረት የግል አምላክ ሰጥተን ሳይሆን ሁሉንም የፈጠረ አንድ እግዚአብሔር ነው ብለን እናምናለን ። ዓለማትን ካለ መኖር ወደ መኖር ያመጣ ፣ ባሻ ጊዜ ሲያሳልፍ ጠያቂና ተከራካሪ የሌለበት አምላክ አለ ብለን እናምናለን ። ዘመናትን ሲያስጀምር እርሱ ግን ዘላለማዊ እንደሆነ እናምናለን ። የታሪክ ባለቤት ትውልድ ነው ቢባልም የታሪክ ባለቤትና ተቆጣጣሪ እግዚአብሔር ነው ብለን እናስተምራለን ። ፍጥረትም ሲያልፍ ፣ ዘመናትም መቆጠር ሲያቆሙ የማታልፍ ርስት መንግሥተ ሰማያት ፣ የማይቆጠር ዘላለማዊነት እንደሚመጣ እናምናለን ፣ እናሳምናለን ።
ቀኑ የሰው ቢሆን ኖሮ መኖር የሚችሉት ጉልበት ያላቸው ሰዎች ብቻ ነበሩ ። ነቢዩ ግን “ቀኑ ያንተ ነው” አለ ። አንድም ቀን የተባለው መልካም ዕድል ፣ ብርሃናዊ ዘመን ነው ። የተቀበልናቸው በጎ ነገሮች ሁሉ የእርሱ ናቸው ። የበጎነታችን ሽልማት ሳይሆን የፈጣሪነቱ ስጦታ ናቸው ። ቀኑ የሰው ቢሆን ኖሮ የምንሰጣቸውና የምንነሣቸው ሰዎች አሉ ። እርሱ ግን ይህችን ቀን ለክፉዎችና ለደጎች ሰጥቷል ። ለእገሌ ይህ አይገባውም ብሎ የሚሟገተውም የለም ። በስጦታው የማይከሰስ አምላክ ነው ። ሌሊቱም ያንተ ነው ይለዋል ። ዕረፉ ብሎ የሰጠው ሌሊት ፣ በሞት እኛን የሚሰበስብበት ምሽት የእርሱ ገንዘብ ነው ። መከራውንም የማስተማሪያ ክፍሉ የሚያደርግ እርሱ ነው ። በበደላችን የምትመጣው ሌሊትም የእርሱ የቅን ፍርዱ ናት ። ከበደላችን አሳንሶ እንጂ አብዝቶ የከፈለን ምንም ነገር የለም ። ፎቶ አንሺው ፊልሙን በጨለማ ክፍል ውስጥ አሳልፎ መልክ እንዲያወጣ ፣ በጨለማው ውስጥ አሳልፎ መንፈሳዊ መልክን የሚሰጠን ልዑል አምላክ እግዚአብሔር ነው ።
የዘመናትና የወራት ልክ እንዲታወቅ ፣ ለቀን መብራት ለሌሊት ወጋገን እንዲሆኑ ፀሐይና ጨረቃን ያዘጋጀ እግዚአብሔር ነው ። አዘጋጀ ተብሏልና ስንዱ አምላክ ፣ ሁሉን አርቆ የሚያይ ፈጣሪ መሆኑን እናውቃለን ። ፀሐይ የተባለውም ሁሉን የሚመግበው ቸርነቱ ፣ ጨረቃ የተባለውም በመከራ ዘመን ማጽናናቱ ነው ። በፀሐይ አድልኦ የለም ፣ አባትነቱም ለሁሉ ነው ። ጨረቃም በጨለማ ታበራለች ፣ በክፉ ዘመንም አጽናኝ ነቢያትን ይልካል ።
በጋውን ለአበባ ፣ ለፍሬ ፣ ለአጨዳ ፣ ለመሰናዶ ፣ ለሰርግ ፣ ለደስታ አደረገ ። ክረምቱንም ለዘር ፣ ለእርሻ ሰጠ ። በጋንና ክረምትን ሳይሳሳት ፣ አስታዋሽ ሳይፈልግ በጊዜው የሚያመጣ እግዚአብሔር ምስጋና ይገባዋል ። ክረምቱ አልፎ ፣ ወንዞች ጎድለው ፣ የተራራቀ የሚገናኝበት ፣ የጠፉ ወፎች ድምፃቸውን የሚያሰሙበት ፣ አበቦች የሚታዩበት ፣ በቤት የተዘጋባቸው እንስሳት በመስኩ የሚሰማሩበት በጋ ይኸው መጣ ። ይህን ስጦታ ለሰጠን አምላክ ምስጋና እናቀርባለን ።
ያለፈው ዓመትም ብዙ ቸርነቱን ያየንበት ቢሆንም አሳዛኝ መከራንም ያስተናገድንበት ፣ ቤተ ክርስቲያንም የሰማዕትነት ጽዋ የተቀበለችበት ነው ። ምእመናንም በደማቸው ስለ ክርስቶስ የመሰከሩበት ዓመት ነው ። በአንደኛው ዓይናችን ብናለቅስም በአንደኛው ዓይናችን የምንደሰተው ክርስትና ዋጋ የሚያስከፍል ሃይማኖት መሆኑን በማወቃችን ነው ። ችግሮችን ስናስተናግድ ግን ለዚህ ችግር የእኔ ጉድለት ምንድነው? ብለን መጠየቅ አለብን ። አንድነትን ፣ ፍቅርን አብዝተን ካልሰበክን አሁንም ጥፋት ያንዣብበናል ። እኛ ያልሰበሰብነውን ትውልድ ክፉ አግኝቶት መጠቀሚያ እንዳደረገው ማመንና ንስሐ መግባት ያስፈልገናል ። ዘረኝነትን ፣ አድመኝነትን ፣ መጠላለፍን እኛ ተርፎን ለዓለም አበድረናል ። ብዙ ጥፋቶች የእኛ ጥላዎች ናቸው ። ቤተ ክርስቲያንንም አክብረን ስላላስከበርናት ለአደጋ ዘመን አሳልፈን ሰጥተናታል ።
አሁንም ትልቁ መፍትሔአችን ወንጌልን ጠንክሮ ማስተማር ፣ ቅድስናን መኖር ፣ በቅንነት ማስተዳደርና የድሆችን እንባ ማበስ ነው ። ሌብነትን ተጠይፈን ፣ አባቶቻችን የሠሩትን ሥርዓት አክብረን ለቀጣይ ዘመን ማሻገር ያስፈልገናል ። አገራችን በገዛ ልጆቿ አንገት የደፋችበት ጭካኔ ማብቃት አለበት ። ለዚህ ደግሞ የእኛ ኃላፊነት ብዙ ነው ።
እኔና ከእኔ ጋር የሚያገለግሉት ወደ ሀገረ ስብከቱ ከፍተኛ ኃላፊነት ከመጣንበት ጊዜ ጀምሮ ከሀገረ ስብከቱ የሥራ ሓላፊዎችና ከሁሉም ሰራተኞች ጋር በመሆን ቦታው ለባለሙያው እንዲሆን ፣ የተጎዱ የአስተዳደር ዘርፎች ፍትሕ እንዲያገኙ እየሮጥን ነው ። ሥራችንን ግን ጀመርን እንጂ አልጨረስንምና በአዲሱ ዓመት በቃለ እግዚአብሔር እየተመራን፣ በጸሎት እየተጋገዝን በመመካከር እና በመናበብ አብረን እንድንሠራ የሀገረ ስብከቱን እድገት ለሚናፍቁ ሁሉ በአክብሮት ጥሪዬን አቀርባለሁ። ትልቁ ልማትም ሰው ላይ የሚፈስስ ሀብት ነውና ካህናት ምእመናንን በቃልም በተግባርም እንዲያንፁ ለሕዝቡ ካላሰብን በእግዚአብሔርም በታሪክም ፊት ስንወቀስ እንኖራለንና የሁለት ዓለም ስደተኛ እንዳንሆን በፍፁም ትህትና አሳስባለሁ ።
በመጨረሻም 2013 ዓመተ ምሕረት በመልካም እያስተዳደርን ቤተ ክርስቲያንን የዘመን ጌጥ ለማድረግ ያለንን ትልም በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ የዕለት ተዕለት አባታዊ መመሪያ እና ጸሎት ፣ በብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ምክር ታግዘን ከፍጻሜ እንደምናደርሰው ያለኝን ጽኑ ተስፋ እየገለጽኩ በዓሉን ስናከብርም የተጎዱትን በማሰብ፣ በዓለም ላይ በተከሰተው የኮሮና ወረርሽኝ የተጨነቁትን በማጽናናትና በመተሳሰብ እንዲሆን እየተማፀንኩ ዘመነ ማቴዎስ የሰላም ፣የፍቅር የአንድነት፣ የስምምነት፣ የሀገራችን ሰላም የሚረጋገጥበት፣ ቤተ ክርስቲያናችን ከፍ ብላና ደምቃ የምትታይበት ዓመት እንዲሆን እመኛለሁ።
በድጋሚ እንኳን አደረሳችሁ!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!
መልአከ ሕይወት አባ ኃይለ ገብርኤል ነጋሽ( ቆሞስ)
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ
የአዲስ አበባ ሃይማኖት ተቋማት ቦርድ ሰብሳቢ