የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ከምእመናን ያሰባሰበችውን 40 ሚሊየን ብር በኦሮሚያ ክልል ጉዳት ለደረሰባቸው ምእመናን አከፋፈለች
ብፁዕ አቡነ ሄኖክ የምዕራብ አርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ብፁዕ አቡነ መቃርዮስ የምሥራቅ ሐረርጌና የሱማሌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ የእርዳታ አሰባሳቢ ዐቢይ ኮሚቴ እና የጥናት ኮሚቴ በተገኙበት በዛሬው ዕለት ስለ ተገኘው ድጋፍና አከፋፈሉን በተመለከተ በጠቅላይ ቤተክህነት ግቢ ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጥቷል፡፡
የዐቢይ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ መኮንን ሰሙ በሰጡት መግለጫ በኦሮሚያ ክልል ለተጎዱት ምእመናን ዐቢይ ኮሚቴው ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ ያለ እረፍት ከፍተኛ እንቅስቀሴ እያደረገ መሆኑን ገለጸው ከብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ጋር በመሆን ቦታው ድረስ በመገኘት የተጎዱ ምእመናን በመጎብኘትና በማጽናናት እንዲሁም በአጥኚ ክፍሉ ጥናት በማካሄድ ከፍተኛ ሥራ መሠራቱን አብራርተዋል፡፡ ዐቢይ ኮሚቴውም አጠቃላይ 3 ቢሊየን ብር በእርዳታ ለመሰብሰብ አቅዶ የተነሣ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ዐቢይ ኮሚቴው በመጀመሪያው የእርዳታ ዙር 44.4 ሚሊዮን ብር ከአገር ውስጥና ከአገር ውጪ ካሉ ምእመናን መሰብሰቡንም ተናግረዋል፡፡ ከተገኘው እርዳታ 40 ሚሊዮኑ ብር በኢትዮጲያ ንግድ ባንክ አማካኝነት በጥናቱ መሠረት ለተጎዱ በአስር አህጉረ ስብከቶች ሥር ለሚገኙ ምእመናን በቀጥታ ከባንኩ በሚዘጋጅላቸው አካውነታቸው እንደሚላክላቸው ተናግረዋል፡፡ ቀሪው 4.4 ሚሊዮን ብር ደግሞ በሚጠኑ ጥናቶች መሠረት ለተጎዱ ምእመናን የሚደርስ ይሆናል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በብዛት በየቦታው ስለሚገኝ ለዚህ አገልግሎት ተመራጭ መሆኑ የተጠቀሰ ሲሆን ባንኩም ለተጎጂ ምእመናን የባንክ ደብተሮችን አዘጋጅቷል፡፡ ለተጎጂዎች የተሰበሰበው ብር አንዳችም አይባክንም፤ለሌላ ለምንም ጥቅም እነደማይውልም አስረግጠው ተናግረዋል፡፡ ንግድ ባንኩም ላደረገው አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የዐቢይ ኮሚተው ምክትል ሰባሳቢ ንቡረ እድ ኤልያስ የትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ዋና ሥራ አስኪያጅ እርዳታውን አስመልክቶ ባደረጉት ንግግር ጉዳዩ የመተጋገዝ፤የመረዳዳት ብቻ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ነው ሲሉ ገልጸውታል፡፡ የምናደርገው ድጋፍ የቤተክርስቲያናችንንና የአገራችንን ህልውና የሚያስቀጥል መሆኑን ጠቅሰው ለወደፊትም ጥቃትና ጉዳት እንዳይደረስ ጭምር መሥራት አለብን ብለዋል፡፡ ለምእመናንም የምናስተላልፈው መልእክት ቢኖር ከአሁን በኋላ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቆርጣ የተነሣች መሆኗንና ምእመናን በሙሉ ከቅዱስ ሲኖዶስና ከዐቢይ ኮሚቴው ጎን እነዲሰለፉ ሲሉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በመግለጫው ላይ የጥናት ኮሚቴው አባል የሆኑት አቶ አበራ እንደሻው ጥናታዊ ስነ ጽሑፍ ያቀረቡ ሲሆን በጥናቱም እንደገለጹት ከዐቢይ ኮሚቴው ጋር በመወያየትና በመናበብ እንዲሁም የቴክኒክ ባለሙያዎችን በመመደብ በምእመናን ላይ የደረሱትን የጉዳቶች መጠን በቦታው በመገኘት 95 ፐርሰንት ታማኝነትና እውነተኛነት ያለው በመረጃና በማስረጃ የተደገፈ ጥናት መሠራቱን አብራርተዋል፡፡ ይህም ጥናት የተሰበሰበው ገንዘብ ለማን እና ምን ያህል ይሰጥ የሚለውን የገንዘብ አከፋፈል ሂደቱን ምቹ ያደርጋል ብለዋል፡፡
በተጨማሪም የጥናቱ ከሚቴ አባል የሆኑት ዶ/ር ንጉሱ ለገሰ ጥናቱን አስመልክተው ንግግር ያደረጉ ሲሆን የጥናቱ ኮሚቴ ከዐቢይ ኮሚቴና ከንዑስ ኮሚቴ ጋር አብሮ በጋራ በመሆን በመነጋገር፤ በመወያየትና በትክክለኛ የመረጃ ፍሰት እውነተኛ የሆነ ጥናታዊ ጽሑፍ መሠራቱን ጠቅሰዋል፡፡ ይህም ጥናት 40 ሚሊዮን ብሩ በ10 አህጉረ ስብከቶች ሥር ለሚገኙ ለተጎዱ ምእመናን እንደ ጉዳታቸው መጠን ለማከፋፈል ይረዳል ብለዋል፡፡ እርዳታው በሌሎች አህጉረ ስብከቶች እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡
የምዕራብ አርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሄኖክ የድረሱልንን ጥሪያችንን ሰምታችሁና ተቀብላችሁ አንድ ላይ በመቆም ለወገኖቻችሁ ስለ ደረሳችሁ እጅግ በጣም ደስ ብሎኛል በማለት በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጪ ያሉ ምእመናን ላደረጉት ከፍተኛ አሰተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል፡፡ ይህም መልካም ሥራ አንድነታችን የተንጸባረቀበት፤በአንድነት የቆምንበት ነው ሲሉ ገልጸውታል፡፡ ጉዳት የደረሰባቸው ምእመናንም አዲሱን ዓመት በመጽናናት እንዲያሳልፉ ይረዳቸዋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡ እርዳታውን በተጠናከረ መልኩ ማስኬድ አለብን፤ ተፈናቀዮችን ወደ የቤታቸው ልንመልሳቸው ይገባል፤ በዚህ አያበቃም ወደ ፊት ከባድ ሥራ ይጠብቀናል ሲሉ አባታዊ መልእከታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ብፁዕ አቡነ መቃርዮስም የምሥራቅ ሐረርጌና የሱማሌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ቤተክርስቲያን በተወሰኑ አካለት ልትደበደብ ልትቃጠል አይገባትም ምክንያቱም ቤተክስቲያን ሀገር ናት በማለት ገልጸዋል፡፡ ምንም ሳያደርጉ በእምነታቸው ምክንያት ብቻ የታሰሩትን ምእመናን መንግሥት ሊፈታቸው ይገባል ብለዋል፡፡ ቤተክርስቲያናችንን በመጠበቅ ኃላፊነታችንን እንወጣ ካሉ በኋላ መጪውንም ዘመን የደስታ ዘመን ያድርግልን በማለት መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡
መ/ር ወንድምአገኝ ደጀኔ የሀገረ ስብከቱ ዘጋቢ