የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የደረሰባትን ወቅታዊ ችግር አስመልክቶ መግለጫ ሰጠች

ነሐሴ 20 ቀን 2012 ቅዱስ ፓትርያርኩ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ የጠ/ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ብጹዕ አቡነ ያሬድ፣ በርካታ ብጹዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የጠቅላይ ቤተ-ክህነት የመምሪያ ኃላፊዎች: የአ.አ ሀ/ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መልአከ ሕይወት አባ ኃ/ገብርኤል ነጋሽ፣ እንዲሁም በርካታ የሚዲያ ባለሙያዎችና እንግዶች በተገኙበት በቤተ ክርስቲያኒቱ እና ተከታይ ምእመናኖቿ ላይ እየደረሰ ስላለው ዘግናኝ ፍጅትና መከራ መግለጫ ሰጥታለች።

በሀገራችን ኢትዮጵያ ሰኔ 22 ቀን/2012 ዓ/ም በአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ላይ በአዲስ አበባ ከተማ በተፈጸመው ግድያ ምክንያት የተነሣ በአዲስ አበባ እና በኦርምያ ክልል የበርካታ ወገኖች ሕይወት መጥፋቱ ፣ አካል መጉደሉ እንዲሁም እጅግ ከፍተኛ የሀገር ሀብት መውደሙ የሚታወስ ነው።


በመግለጫው ላይ የአርቲስቱ ሞት የቤተ-ክርስቲያን ሐዘንም በመሆኑ በሀዘን ስሜት ውስጥ እያለሁ እንኳን በኦሮሚያ አንዳንድ አካባቢዎች እንደጠላት በመቁጠር ኦርቶዶክሳውያን ተከታዮቼን ኦርቶዶክስ በመሆናቸው ብቻ አስቃቂ በሆነ መልኩ ማለትም በሜንጫ ፣በገጀራ፣ በድንጋይና በጦር መሣሪያ 67 ኦርቶዶክሳውያን ተገድለዋል አስከሬናቸውም በየሜዳው ተጎትቷል፣ በዱር በአውሬዎች እንዲበላ ተደርጓል ለዘመናት ያፈሩት ሀብትና ንብረትም ወድሟል በዚህም የተነሣ በሕይወት የተረፉት አማኞችም በከፍተኛ ሥነ ልቦናዊና ማኅበራዊ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች እንደሚገኙም ገልጻለች።

አጥፊዎችን አንታገስም :ተገቢውን ፍትሕ እንሰጣለን፣ የተጎዱትንም እንክሳለን በማለት ቃል የገቡት የመንግሥት አካላት ቃላቸውን አለመፈጸማቸውን አረጋግጣለች።

በመንግሥት አካላት ቸልተኝነት ይልቁን የመንግሥት መዋቅርን ተገን አድርገው በኦሮሚያ ክልል የብሔርና የእምነት ጽንፈኞች በፈጸሙት ግፍ በእጅጉ ማዘኗንና የገለጸችው ቤተክርስቲያን ጉዳቱ በተፈጸመበት ስፍራ ሁሉ ተዘዋውሮ የደረሰውን በደልና ግፍ አጥንቶ የሚያቀርብ ከፍተኛ ኮሚቴ ማዋቀሯንና ለጆሮ የሚሰቀጥጥ መከራ የደረሰ መሆኑን ከኮሚቴው የመጀመሪያ ሪፖርት መረዳቷን አሳውቃለች።

በመጨረሻም የጥፋቱን አስከፊነት በዐብይ ኮሚቴው ሪፓርት የተረዳችው ቤተክርስቲያን ተጎድዎቹን በአስቸኳይ ባሉበት ለመርዳትና መልሶ ለማቋቋም እየተንቀሳቀሳቀሰች መሆኑን ገልጻ መንግሥት በአስቸኳይ ሊፈጽማቸው የሚገቡ ተግባራትንም በመግለጫው አስረድታለች፣ ለተከታይ ምእመኗ እና ለበጎ አድራጊዎች ሁሉ ተጎድዎችን ይረዱ ዘንድ ጥሪዋን አስተላልፈለች።

በዚሁ የኦርቶዶክሳውያን ግፍና መከራ በበዛበት ኦሮሚያ ክልል ውስጥ በወርሃ ጥቅምት /2012 ዓ.ም በአንድ ቀን ብቻ 97 ሰዎች በግፍ መገደላቸውና ከፍተኛ ንብረት መውደሙም የሚታወስ ነው።

                                         መ/ር ሽፈራው እንደሻው የሀገረ ስብከቱ ዘጋቢ