የአ/አ/ሀ/ስ/ ዋና ሥራ አስኪያጅ ክቡር መልአከ ሕይወት አባ ኃይለገብርኤል ነጋሽ(ቆሞስ) የ2012 ዓ.ም የቅድስት ድንግል ማርያም ጾመ ፍልሰታን አስመልክተው የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላለፉ
እንኳን ለ2012 ዓ.ም. ጾመ ፍልሰታ ለማርያም በሰላም አደረሳችሁ!!!
“ተንሥእ እግዚኦ ውስተ ዕረፍትከ።
አንተ ወታቦተ መቅደስከ።”
“አቤቱ ፥ ወደ ዕረፍትህ ተነሥ፥
አንተና የመቅደስህ ታቦት።”
/መዝ. 132፡8/
ነቢዩ ዳዊት ከአንድ ሺህ ዓመት በፊት ምሥጢር ተገልጦለት፣ ትንቢት ቀድሞለት የጌታችንንና የእመቤታችንን ትንሣኤ ተናግሯል። የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ዕረፍትና ትንሣኤ ደግሞም ዕርገት እንደ ተራ ነገር የሚታይ ሳይሆን የከበረና ምእመናንም በጾም በጸሎት ሁነው የእናታችንን በረከት የሚለምኑበት ነው። እግዚአብሔር እንቢተኛውንና ተጠራጣሪውን የሰው ልቡና ለማሳመን አስቀድሞ መንገድ የሚጠርጉ ታሪኮችንና ክስተቶችን በማምጣት የታወቀ አምላክ ነው። በሐዋርያት ሲሰብከን፣ በነቢያት አረጋግቶ፤ ሕገ ኦሪትን ሲሰጥ ሕገ ልቡናን አድሎ ነው። እንዲሁም የእመቤታችን ትንሣኤ ግራ የሚያጋባቸው ሰዎች እንደሚነሡ ያውቃልና አስቀድሞ በብሉይም በሐዲስም ከሞት የተነሡ ሰዎችን አዘጋጀ። ወለተ ኢያኢሮስና አልዓዛር ከሞት ተነሥተዋልና የእመቤታችን ትንሣኤ ድንቅ አይደለም። ዕርገቷም እንዳያጠራጥረን አስቀድሞ ሄኖክና ኤልያስ እንዲያርጉ አድርጓል። የእመቤታችንን ትንሣኤ ሐዋርያዊ መሠረት ያላቸው ጥንታውያን አብያተ ክርስቲያናት በሙሉ የሚቀበሉትና የሚያስተምሩት ነው። ይህም በቀጥታ ከሐዋርያትና ከሐዋርያነ አበው፣ ከሊቃውንት ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ የተቀደሰው ትውፊታችን አካል ነው።
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የክርስቶስ መቅደሱም ታቦቱም ናት። መቅደሱ ናትና ማደሪያው፣ ታቦቱ ናትና ቃለ እግዚአብሔርን የተሸከመች ናት። ጌታችን ሞትን አሸንፎ እንደ ተነሣ እናቱ ቅድስት ድንግል ማርያምም ከሞት እንድትነሣ አድርጓል። በዚህም እርሱ ክብሩ ለዘላለም መሆኑን፣ ያገለገሉትን የማይጥል መሆኑን አስተምሮናል። ዛሬም አገልግዬ ተጣልሁ የምንል፣ ከምድረ ርስት፣ ከሰው ውዳሴ የምንፈልግ ከሆነ የእናታችን መንገድ ያልታየን ምስኪኖች ነን። እርስዋ ዘመኑዋ በሙሉ መስቀል የነበረበት የመከራ ጉዞ ነው። ክብሯ ከሰማይ ነው። ሰዎች ሁሉ በነበሩበት ዘመን ተጠልተው ይሆናል፣ እርስዋ ግን በዘላለም ዕረፍት ሳለችም ሰይጣን ብዙ ጠላቶችን ሲያስነሣባት ስናይ፣ የመዳናችን ጠላት የሆነው ከይሲ ምን ያህል እንደ ተዋጋት ያሳየናል።
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በትንሣኤ አካል፣ በዘላለም ዕረፍት ለች፣ የክርስቶስን ጌትነት ለሚያምኑ ሁሉ እናት የሆነች፣ በጸሎትዋም በጣር ላይ ላለ ዓለም የምትቆም ተወዳጅ እናታችን ናት። በዚህ በጾመ ማርያምም በታላቅ ትሕትና ሁነን ቅድመ እግዚአብሔር መቅረብ፣ እንባቸው እየፈሰሰ ያሉትን መከረኞች ማጽናናት ይገባናል። መላው ዓለም እየተጨነቀበት ያለውን የኮቪድ 19 ወረርሽኝ የሰውን አካላዊ ግንኙነት እየገታ፣ ሰዎች በብቸኝነት ወደ ጭንቀት እየሄዱ ናቸውና ጊዜው በፈቀደው መገናኛ በኩል እየተገናኘን ማጽናናት ይኖርብናል። ከሁሉ በላይ መዓቱም ምሕረቱም ገንዘቡ ነውና እንዲምረን በብዙ እንባ አምላካችንን መለመን ይገባናል። ሰዓታት በመቆም፣ ኪዳን በማድረስ፣ ውዳሴ ማርያም ቅዳሴ ማርያም በመተርጎም፣ ቅዳሴ በመቀደስ፣ በሠርክ ጸሎተ ምህላ ሕዝቡን በማገልገል ያለ እረፍት የሚያገለግሉትን አበው ድካማቸውን በቅዱሳን ዋጋ እንዲቀበልልን የምንጸልይበት፣ ለአገር መሪዎችም የሰሎሞንን ጥበብ የምንለምንበት፤ ከቂም ከበቀል፣ ከዘረኝነት ቍራኛ ተፈትተን ወደ እግዚአብሔር የምንመለስበት የሱባኤ ጊዜ እንዲሆን ቤተ ክርስቲያን ጥሪዋን ታስተላልፋለች ።
እግዚአብሔር አምላክ አገልግሎታችንን ሁሉ በብሩህ ገጽ ይቀበልልን።
መልአከ ሕይወት አባ ኃይለ ገብርኤል ነጋሽ/ቆሞስ/የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ