የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ቆሞስ ክቡር መልአከ ሕይወት አባ ኃ/ገብርኤል ነጋሽ፣ የሀገረ ስብከቱ የዋና ክፍል ኃላፊዎችና የክፍለ ከተማ ሠራተኞች በጋራ የችግኝ ተከላ መርኃ ግብር አካሄዱ
ሐምሌ 24/2012 ዓ.ም (አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ)
❖ ❖ ❖ ❖ ❖ ❖ ❖ ❖ ❖ ❖ ❖ ❖ ❖ ❖ ❖ ❖ ❖ ❖ ❖ ❖ ❖ ❖ ❖ ❖ ❖ ❖ ❖ ❖ ❖ ❖
ዛሬ ሐምሌ 24/ 2012 ዓ/ም የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ቆሞስ ክቡር መልአከ ሕይወት አባ ኃ/ገብርኤል ነጋሽ፣ የሀገረ ስብከቱ የዋና ክፍል ኃላፊዎች፣ የሀ/ስብከቱ ሠራተኞች፣ የላፍቶ ክፍለ ከተማ ሠራተኞችና የላፍቶ ክፍለ ከተማ አድባራትና ገዳማት የአስተዳዳሪዎች ተወካይ በተገኙበት በላፍቶ ክፍለ ከተማ በጎፋ መ/ብርሃን ቅዱስ ኡራኤልና ቅድስት አርሴማ ቤተ ክርስቲያን በሚያምር መልኩ የችግኝ መርኃ ግብር ተከላ ተካሂዷል።
ከችግኝ ተከላ በኋላ በሀገረ ስብከቱ ክፍል ኃላፊ መ/ሐዲስ ኃይለ እግዚእ “ወዘሕጎ ያነብብ መዓልተ ወሌሊተ ወይከውን ከመ ዕፅ እንተ ትክልት ኀበ ሙሓዘ ማይ እንተ ትሁብ ፍሬሃ በበጊዜሃ” …በውኃ ፈሳሾች ዳር እንደ ተተከለች፥ ፍሬዋን በየጊዜዋ እንደምትሰጥ፥ ቅጠልዋም እንደማይረግፍ ዛፍ ይሆናል፤ የሚሠራውም ሁሉ ይከናወንለታል።” በሚል ርእስ ተነስተው የእፀዋት ጥቅምና ፍሬ ከመንፈሳዊ ሕይወት አያይዘው የችግኝ ተከላና ጥቅሙን ሰፋ ባለ መልኩ አስተምረዋል።
በመጨረሻም የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ቆሞስ ክቡር መልአከ ሕይወት አባ ኃ/ገብርኤል ነጋሽ የችግኝ ተከላ መርኃ ግብሩን አስመልክተው ላቅ ያለ ውጤቱንና ጥቅሙን በማውሳት ችግኝን መትከል ብቻ ሳይሆን ዋናው መንከባከብ ነውና በሚገባ ልትንከባከቡት ይገባል፣ እኛም ዛሬ እዚህ ተገኝተን አሻራችንን አስቀምጠናል እየመጣንም እንከታተላለን ብለዋል። አያይዘውም ችግኝን መትከል፣ ዕጸዋትን ማብዛትና ማሳደግ፣ አከባቢን በአረንጓዴ ደን መሸፈን ለሃገር እድገትና ሰላም እንዲሁም የልማት ምልክት ነውና በጋራና በሕብረት ሁነን ሳንታክት ችግኝ እየተከልን እንዲሁም በሚገባ እየተንከባከብን ስለ ሰላምና አንድነት አብዝተን ልንጸልይ ይገባል በማለት ንግግራቸውን በቃለ ምዕዳንና በጸሎት ዘግተዋል።
ዘጋቢ፡ መ/ር ኪዱ ዜናዊ
ፎቶ፡ መ/ር ዋሲሁን ተሾመ
ለተጨማሪ መረጃ የሀገረ ስብከቱ ማኅበራዊ ሚዲያዎችን ይጎብኙ
ፌስ ቡክ ገጽ:- አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት/Addis Ababa Diocese
ድረ-ገጽ:- www.addisababa.eotc.org.et
ተሌ ግራም ቻናል:- t.me/AddisAbabaDiocese
ዩትዩብ ቻናል:- www.youtube.com/channel/UCtYqL7fu87AVTGHaZDPToFg