የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ክቡር መልአከ ሕይወት አባ ኃ/ገብርኤል ነጋሽ በሀገረ ስብከቱ ሥር ከሚገኙ አድባራትና ገዳማት አስተዳዳዎች ጋር ተወያዩ

Photo file

ሐምሌ 23 ቀን 2012 የአ.አ ሀ/ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መልአከ ሕይወት ክቡር አባ ኃ/ገብርኤል ነጋሽ: የሀገረ ስብከቱ የዋና ክፍል ኃላፊዎች የክፍላተ ከተሞች የሥራ ኃላፊዎችና የአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች በተገኙበት በሀገረ ስብከቱ የስብሰባ አዳራሽ ጠዋትና ከስአት በተደረገው ውይይት የጾመ ፍልሰታ ሱባኤ አገልግሎት እና የአድባራትና ገዳማት የደመወዝ እስኬል ማስተካከያን በተመለከተ በሁለት አጃንዳዎች ዙሪያ ውይይት ተካሂዷል።

የውይይት መርሐ ግብሩን ያስጀመሩት የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ በሀገረስብከታችን በአድባራትና ገዳማቱ ያለው የሰው ኃይል ክምችት ከአግባብ ውጭ ከመሆኑም በላይ በየጊዜው የሚደረገው የደመወዝ ጭማሬም የቤተ ክርስቲያናችንን ምጣኔ ሀብት ያላገናዘበ ስለሆነ አዲስ የደመወዝ ጭማሬ እስኬል ማስተካከያ በአዲስ መልኩ በማስተካከል ላይ እንገኛለን: ለረጅም ጊዜ ሲያገለግል የቆየው የደመወዝ እስኬል የደብር አስተዳዳሪዎችን ያገለለ ነበር አሁን እየተሠራ ያለው የደመወዝ ማስተካከያ እስኬል ግን የሁሉንም ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል።

በተያያዘ ዜናም የዘንድሮው የጾመ ፍልሰታ ሱባኤ አገልግሎት ወቅታዊውን በሽታ ለመከላከል በሚያስችልና እጅግ ጥንቃቄ በተሞላው መልኩ እንዲፈጸም ጥብቅ መመሪያ አስተላልፈዋል።

በጉባኤው ላይ የተሳተፉት የስብሰባው ታዳሚዎች “የመጨረሻው እስኬል ላይ ደርሳችኋል ተብለን የበይ ተመልካች ሁነን ነበር አሁን እየተሠራ ባለው ማስተካከያ ግን ደስ ተሰኝተናል: ወረርሽኙ በሀገራችን በአስጊ ሁኔታ እየጨመረ ስለመጣ እኛም የሚተላለፉ መመሪያዎችን በየደብራችን በመፈጸምና በማስፈጸም የሕዝበ ክርስቲያናችንን ሕይወት መታደግ እንዳለብን አምነን የቻልነው በማድረግ ላይ እንገኛለን ብለዋል።

በመጨረሻም ዋና ሥራ አስኪያጁ ይህ ወቅት ፈታኝ ነው: በመተባበርና በመተጋገዝ አብዝቶም በመጸለይ እንጅ በመዘናጋት አናልፈውምና ሕዝበ ክርስቲያናችንን እናስተምር :ራሳችንንም እንጠብቅ በማለት አባታዊ መልእክት አስተላልፈዋል ።

መ/ር ሽፈራው እንደሻው የሀገረ ስብከቱ ዘጋቢ

የሀገረ ስብከቱ ማኅበራዊ ሚዲያዎች
ፌስ ቡክ ገጽ:- www.facebook.com/AddisAbabaDiocese/
ድረ-ገጽ:- www.addisababa.eotc.org.et
ተሌ ግራም ቻናል:- t.me/AddisAbabaDiocese
ዩትዩብ ቻናል:- www.youtube.com/channel/UCtYqL7fu87AVTGHaZDPToFg