የቅዱስ ገብርኤል ዓመታዊ ክብረ በዓል በምዕራፈ ሰማዕት ቅዱስ ገብርኤልና ቅድስት አርሴማ ቤተ ክርስቲያን በድምቀት ተከበረ

ሐምሌ 19/2012 ዓ.ም (አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ) የሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል ዓመታዊ ክብረ በዓል በአዲስ አበባ ከተማ በለምዶ 24 ቀበሌ በሚባለው አካባቢ አዲስ በታነጸው የቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን በከፍተኛ ድምቀት ተከበረ፡፡
ከወራት በፊት ቤተ ክርስቲያን ለመትከል በተደረገ የምእመናን እንቅሰቃሴ፤ ከፍተኛ ውዝግብ ተነስቶበት የነበረው ይህ ሥፍራ፤ በአካባቢው ምእመናን ከፍተኛ ጥረት እና በሀገረ ስብከቱ የቅርብ ክትትል በአጭር ጊዜ ውስጥ ግንባታው ተጠናቆ በትላንትናው ዕለት ብጹአን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ ክቡር የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የሀገረ ስብከቱና የክፍለ ከተማው ሐላፊዎች በተገኙበት ሥርዓተ ቡራኬው የተከናወነ ሲሆን፤ በዛሬው ዕለትም በዓሉ በርካታ ምእመናን በተገኙበት በድምቀት ተከብሯል፡፡

በዕለቱ ከተገኙ ብጹአን አበው ሊቃነ ጳጳሳት መካከል የደቡብ ኦሞና የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ሊቀ ጳጳስ የሆኑት አቡነ ፊልጶስ ቤተ ክርስቲያኑን “ምዕራፈ ሰማዕት” ብለው ሰይመዋል፡፡ በዕለቱ የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ክቡር መልአከ ሕይወት አባ ኃይለ ገብርኤል ነጋሽ በቡራኬ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉ ሲሆን፤ “በዛሬው ዕለት በታላቅ ደስታ፣ በይባቤና በምስጋና የምናቀርበው መሥዋዕት ያሳለፍነውን የኀዘንና የልቅሶ፣ የድካምና የውጣ ውረድ ጉዞ አስረስቶ በመንፈሳዊ ሐሴት የምንደምቅበት ክስተት መሆኑ፤ ጽናትና ብርታት፣ ኃይልና ጉልበት የሆነን አምላካችንን በታላቅ የምሥጋና ቃል የምናመሰግንበት ሆኖ እናገኘዋለን” ብለዋል፡፡

በሥፍራው ከወራት በፊት በጸጥታ ኃይሎች በተተኮሰ ጥይት ሁለት የአካባቢው ወጣቶች በዕረፍተ ሥጋ መለየታቸው የሚታወስ ነው፡፡