ሐምሌ 18 ቀን በምዕራፈ ሰማዕት ቅዱስ ገብርኤል እና ቅድስት አርሴማ ቤተ ክርስቲያን የቡራኬ ሥነ ሥርዓት ላይ የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ያስተላለፉት መልእክት

“በለሱን የጠበቀ ፍሬዋን ይበላል፡፡” ምሳ. 27፡18

ብጹዕ አባታችን አቡነ ፊሊጶስ
የተከበራችሁ በዚህ የተሰበሰባችሁ ምእመናን እና ምእመናት የሁሉ ፈጣሪ፣ የሁሉ መጋቢ የሆነው አምላካችን፤ በዚህ በኀዘንና በጭንቀት ወቅት የምንጽናናበት፣ ቃሉን የምንሰማበትን ቅዱስ ቤቱን እንድናከብር ስለፈቀደልን ክብርና ምሥጋና ለእርሱ ይሁን!!
እንኳን ደስ አለን!!!
እንኳን ደስ አላችሁ!!!

ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን እግዚአብሔርን ደጅ በመጥናት፣ ትእግስትን ገንዘብ በማድረግ የሚገኘውን ልዩ ጸጋ በምሳሌ ሲገልጽልን “በለሱን የጠበቀ ፍሬዋን ይበላል” ብሎናል፡፡
አንድ ገበሬ የተከለውን የበለስ ችግኝ ፍሬውን ለመብላት፤ ችግኙን በአግባቡ ከመትከል ጀምሮ፣ ወቅቱን ጠብቆ የመኮትኮት፣ ፍግና ውሃ የማቅረብ በአጠቃላይ የሚያስፈልገውን ሁሉ ሟሟላት እንዳለበት የታመነ ነው፡፡ ችግኙ አድጎ፣ አብቦ ፍሬ እስኪያፈራና ፍሬውን እስኪመገብ ድረስ በርካታ ውጣ ውረድና ድካም ይገጥመዋል፡፡ ነገር ግን በስተመጨረሻ ፍሬውን ሲመገብ የፍሬው ጣዕም ያሳለፈውን ውጣ ውረድና ድካም አስረስቶ ለሌላ ድካም ዝግጁ ያደርገዋል፡፡
የተከበራችሁ ምእመናን በእግዚአብሔር ፈቃድ፣ በመልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ተራዳኢነት እንዲህ ተሰብስበን የምናከብረው የዛሬው በዓል፤ ብርቅዬ ልጆቻችንን በሕይወተ ሥጋ አጥተን፣ በብዙ ኀዘን ውስጥ አልፈን፣ ህንጻው ቤተ ክርስቲያኑን በዚህ መልክ ለመገንባት የጊዜ፣ የገንዘብ፣ የጉልበትና የዕውቀት ሀብት ፈሶበት፣ ብዙ ድካምና ውጣ ውረድ የበዛበት መንገድ መጓዛችን ግልጽ ነው፡፡ ይህም በአንድ በኩል ቅዱስ ጳውሎስ “መከራ ትዕግሥትን እንዲያደርግ ትዕሥትም ፈተና ፈተናም ተስፋን እንዲያደርግ እያወቅን በመከራችን ደግሞ እንመካለን” እንዳለ (ሮሜ. 5፡3-4) መከራው የኦርቶዶክሳዊ ተዋሕዶ ሕይወታችን አንዱ መገለጫና በዋጋ የምንከብርበት መሆኑን እየመሠከርን፤ በሌላ በኩል በታላቅ ደስታ፣ በይባቤና በምስጋና የምናቀርበው መሥዋዕት ያሳለፍነውን የኀዘንና የልቅሶ፣ የድካምና የውጣ ውረድ ጉዞ አስረስቶ በመንፈሳዊ ሐሴት የምንደምቅበት ክስተት መሆኑ፤ ጽናትና ብርታት፣ ኃይልና ጉልበት የሆነን አምላካችንን በታላቅ የምሥጋና ቃል የምናመሰግንበት ሆኖ እናገኘዋለን፡፡
ብጹአን አበው…
ክቡራንና ክቡራት..
በዛሬው ዕለት ይህንን በዓል ስናከብር ልናስተውለው የሚገባን ትልቁ መልእክት፤ በሕይወተ ሥጋ የተለዩን ወንድሞቻችን፤ በአጸደ ነፍስ በአብርሃም እቅፍ ሆነው ነፍሳቸው ሐሴት እያደረገች በመሆኑ፤ በዚህ ሥፍራ ለጸሎትና ለምሥጋና የሚመጣ ሁሉ ይህንን በማሰብ ሊጽናና እንጂ ሊያዝን እንደማይገባ ነው፡፡
በዕድሜ የምትስሏቸው ወንድሞቻቸው የምትሆኑ ወጣት ልጆቻችንም ለዚህ ቤተ ክርስቲያን መመሥረት በተለያየ መልኩ የከፈላችሁት ዋጋ ፍሬ አፍርቶ ለዚህ በቅቶ በማየታችሁ እንኳን ደስ አላችሁ!! ይህንን ቀን ለማየት የደከማችሁት ድካም ውጤቱን ማየታችሁ ለበለጠ መንፈሳዊ ዋጋ እንድተተጉ የሚያበረታ ተግባራዊ ትምህርት መሆኑን በመረዳት፤ ቤተ ክርስቲያናችሁን በጸጋችሁ ማገልገላችሁን እንድትቀጥሉ፣ መንፈሳዊ ትምህርታችሁን እንድታጎለብቱ፣ የአደራ መልእክታችንን እያስተላለፍን እግዚአብሔር ጉልበታችሁን ይባርክ ፍቅራችሁን ያጽና እንላለን፡፡
በመጨረሻም በዚህ ሥፍራ በተለያዩ መንገዶች የተራዱትን ሁሉ፣ ቦታውን በፈቃዳቸው የለገሱ የእስልምና እምነት ተከታይ ወንድማችን እንዲሁም የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ እና በየመዋቅሩ ያሉ የመንግሥት ሐላፊዎችን በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት ስም ምስጋናችንን እናቀርባለን።
ምስጋና ለእግዚአብሔር ይሁን!

ሐምሌ 18 ቀን 2012 ዓ.ም.
አዲስ አበባ
ኢትዮጵያ