በቦሌ ክፍለ ከተማ በተለምዶ ሃያ አራት ተብሎ በሚጠራው አከባቢ ተገንብቶ የተጠናቀቀው የቅዱስ ገብርኤልና የቅድስት አርሴማ ቤተክርስቲያን ተመረቀ
እጅግ በሚያስደንቅ ሁኔታ በፍጥነት ተሠርቶ ያለቀው ይህ ቤተክርስቲያን ብፁእ አቡነ ፊልጶስ የደቡብ ኦሞ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ዩንቨርስቲ የበላይ ጠባቂ፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መልአከ ሕይወት ቆሞስ አባ ኃይለ ገብርኤል ነጋሽ፣ የጠቅላይ ቤተክህነት ሠራተኞች፣የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የየክፍሉ ኃላፊዎች፣የቦሌ ክፍለ ከተማ ሠራተኞች፣ካህናትና ዲያቆናት፣የሰንበት ትምህርት ቤት አባላትና የአከባቢው ምእመናን በተገኙበት ሐምሌ 18 በጸሎት ተባርኮ ታቦተ ሕጉ ገብቷል፡፡
ከዚህ በፊት በቦታው ላይ በተፈጠረ ሁከት በአሳዛኝ ሁኔታ የሁለት ወንድሞች ሕይወት ማለፍ እና በተወሰኑ ወጣቶች ላይ የአካል ጉዳት መድረሱ ብዙኃንን ያሳዘነ ድርጊት መሆኑ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡
የሁለቱን ወንድሞች ሕይወት ማለፍና በቦታው ያለውን ችግር በተመለከተ ከመንበረ ፓትርያሪክ ጀምሮ እስከ ምእመናን ድረስ በጉዳዩ ላይ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶበት ቤተክርስቲያኑ በአጭር ጊዜ ተሠርቶ ለምርቃት መብቃቱ ሁሉንም የቤተክረስቲያኒቷን አማኞች አስደስቷል፡፡
የቤተክርስቲያኑ አስተዳዳሪ መጋቤ አእላፍ ቀሲስ ስንታየሁ ይህንን በተመለከተ ለምእመኑ የእንኳን ደስ አላችሁ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ልጆቻቸውን በሰማእትነት ላጡት ቤተሰቦች የማጽናኛ ሽልማት ተዘጋጅቶ በብፁእ አቡነ ፊልጶስና በክቡር ሥራ አስኪያጁ መልአከ ሕይወት ቆሞስ አባ ኃይለ ገብርኤል ተበርክቶላቸዋል፡፡
ክቡር ሥራ አስኪያጁ “በለሱን የጠበቀ ፍሬዋን ይበላል” (ምሳ 27፡18) የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል መነሻ በማድረግ በክብረ በአሉ ላይ ለተገኙት ምእመናን የትእግስትን ውጤት አብራርተውና አስፍተው አስተምረዋል፡፡ ለቦታው ትልቅ አስተዋጽኦ ላደረጉ የቤተክርስቲያን አባቶች፣ምእመናን እንዲሁም ለአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ እና ለመንግሥት አካላት ምሥጋና አቅርበዋል፡፡
ብፁእ አቡነ ፊልጶስ “አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ” (ማቴ 16፡16) በሚል መለኮታዊ ቃል መነሻነት ስለምስክርነትና ስለሰማእትነት ሰፋ ያለ ትምህርት በመስጠት አባታዊ ምክራቸውን በማስተላለፍ ምእመናኑን አጽናንተዋል፡፡የቅዱስ ፓትርያሪኩን የእንኳን ደስ አላችሁ መልእክትም ለሕዝበ ክርስቲያኑ አድርሰዋል፡፡ ቦታውም ምእራፈ ሰማእታት ተብሎ እንዲጠራ ሰይመዋል፡፡
ዘጋቢ፡ መ/ር ወንድምአገኝ ደጀኔ
ፎቶ፡ መ/ር ዋሲሁን ተሾመ