የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ክቡር መልአከ ሕይወት አባ ኃ/ገብርኤል ነጋሽ በሚሊኒየም ፓርክ ችግኝ ተከሉ

ሰኔ 10 ቀን 2012 የአ.አ ሀ/ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መልአከ ሕይወት አባ ኃ/ገብርኤል ነጋሽና የዋና ክፍል ኃላፊዎች ፣የአዲስ አበባ የሃይማኖት ተቋም ጉባኤ አባላት፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳድር ም/ከንቲባ ተወካይና የጸጥታ ዘርፍ ኃላፊ ፣ እንዲሁም የየካ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ሠራተኞችና በርካታ የአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች በተገኙበት በየካ ተራራ ላይ በሚገኘው ሚሊኒየም ፓርክ የችግኝ ተከላ ተካሂዷል።

በችግኝ ተከላ መርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ መልአከ ሕይወት አባ ኃ/ገብርኤል ነጋሽ ባስተላለፉት መልእክት አረንጓዴ ልማት የተጀመረው ከሥነ ፍጥረት ጀምሮ እንደሆነ ከቅዱሱ መጽሐፋችን እንረዳለን፣ ዕጽዋትና የሰው ልጅ ሕይወት የማይለያዩ ይልቁንም አንዱ ለሌላው እጅግ ተመጋጋቢዎች ናቸው ብለዋል።

በመቀጠልም ዛሬ አብረን በጋራ ችግኝ በመትከል ፍቅራችንን፣ አንድነታችንና ኢትዮጵያዊነታችንን በዚህ ስፍራ አሳርፈናል የተከልነው ችግኝ ጸድቆ፣ አድጎና አፍርቶ እንድናየው ደግሞ የእንክብካቤ ሥራውን በጋራ እንሥራ በማለት አሳስበዋል።

በመጨረሻም የችግኝ ተከላ መርሐ ግብሩን ያዘጋጁትን አካላት አመስግነው፣ በአባቶችና መሪዎች የተጀመረውን ይህንን መልካም ተግባር ሁሉም የሀገሪቱ ዜጎች ሊሳተፉበት እንደሚገባ ጥሪ አስተላልፈዋል ።

                                                                         
                            መ/ር ሽፈራው እንደሻው የሀገረ ስብከቱ ዘጋቢ