ጾመ-ሐዋርያት

ቀድሱ ጾመ ወስብኩ ምሕላ ጾምን ለዩ ምሕላንም አውጁ“ (ኢዮ 1÷14)
ጾም የሚለው ቃል “ጾመ“ ተወ ፤ታቀበ፤ ታረመ ከሚለው የግዕዝ ቃል የተገኘ ሲሆን ጥቅል ትርጉሙም ጥሉላትን መባልዕትን ፈጽሞ መተው መከልከልና መወሰን ወይም ደግሞ ሰውነትን ከሚያምረውና ከሚያስጎመጀው መብልና መጠጥ እንዲሁም ከክፉ ነገር ሁሉ ራስን መጠበቅ መቆጣጠርና መግዛት ማለት ነው፡፡ ጾም የመላ ሰውነታችንን መታዘዝ የሚጠይቅ መንፈሳዊ ተግባር እንጅ በተወሰኑ ብልቶች ላይ ብቻ ገደብን የሚጥል አለመሆኑን ሊቁ ቅዱስ ያሬድ በጾመ ድጓው ሲያወሳ “ይጹም ዐይን፤ ይጹም ልሳን፤ ዕዝንኒ ይጹም እም ሰሚዐ ሕሱም በተፋቅሮ ,,,,,ዓይን ክፉ ነገርን ከማየት፤ አንደበትም ክፉ ነገርን ከመናገር ይጹም፤ጆሮም ክፉ ከመስማት በፍቅር ይጹም በማለት ይመክረናል፡፡ ከቅዱስ ያሬድ ምክር በመነሣት ሰውነታችንን የምንከለከለው ከእህልና ውኃ ማለትም ከምግበ ሥጋ ብቻ ሳይሆን እግዚአብሔር አምላካችን ከሚያሳዝን እና ሰዎችን ከሚጎዳ ከማንኛውም ዓይነት በደል ማለትም ከሐሜት ፤ ከዝሙት ፤ ከክፋት ምቀኝነትና ከሐሰት ከመሳሰሉት የሥጋ ፍሬዎች ፈጽሞ መቆጠብና መከልከል መሆኑን እንድንረዳ አድርጎናል፡፡
❖ የጾም መሠረታዊ ዓላማ
ጾም ከጸሎትና ከስግደት እንዲሁም ከምጽዋት ጋር የሚፈጸም የቅድስት ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ ትጥቅ በመሆን የአንብዐ ንስሓ ምንጭና የመልካም ተጋድሎ መሠረት ነው፡፡ በሃይማኖት ምክንያት ለተወሰኑ ጊዜያት ከምግብና ከመጠጥ የምንከለከለው ግን ምግብና መጠጥ በራሳቸው ኃጢአት ኖሮባቸው አይደለም ይልቁንም ምግብ በልተን መጠጥም ጠጥተን ፈቃደ ሥጋችንን ከምናደልብና የሥጋ ፍሬ ለሆነው ኃጢአት ከምንዳረግ ይልቅ መንፈሳዊ ትጥቃችንን በማጥበቅና ስሜታችንን በመጎሰም ፈቃደ ሥጋችንን ለፈቃደ ነፍሳችን ለማስገዛት እና ምስጋና የሚገባውን እግዚአብሔርን ከቅዱሳን መላእክቱ ጋር እያመሰገንን የምንኖርበትን ሰማያዊና ዘላለማዊ ሕይወትን የምናስብበት መሆኑን ሐዋርያው ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ“ ምግብ ለሆድ ነው፤ ሆድም ለምግብ ነው፤ እግዚአብሔር ግን ይህንም ያንንም ያጠፋቸዋል” (1ኛ ቆሮ 6÷13) በማለት ያስገነዝባል፡፡ ከዚህ በመነሣት የምንጾምበት መሠረታዊ ዓላማ ለመራብና ለመጠማት ወይም አካላዊ ሥጋችንን ለማጎሳቆል ሳይሆን መንፈሳዊ ሕይወታችንን ለማጽናትና ዘለዓለማዊውን መንግሥተ ሰማያትን ለመውረስ ነው፡፡
❖ የጾም ዓይነቶች
ጾም በመንፈሳዊ ዓላማው ምንም እንኳን ልዩነት ባይኖረውም የግል እና የአዋጅ ወይም የሕግ ጾም በመባል በሁለት ክፍሎች የሚከፈል ሲሆን የፈቃድ ጾም የሚባለው በግል ፈቃድ ላይ የተመሠረተ ሆኖ ለንስሓና ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ግንኙነት ለማጠናከር የሚጾም ነው፡፡ የአዋጅ ወይም የሕግ ጾም ደግሞ ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን መሠረት አድርጎ የሚታወጅና ሁሉም የእምነቱ ተከታዮች የሚጾሙት የጾም ዓይነት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን ቀኖና መሠረት በአዋጅ የሚጾሙ ሰባት አጽዋማት ሲኖሩ ከእነዚህም መካከል አንዱ የሐዋርያት ወይም የሰኔ ጾም በመባል ይታወቃል፡፡
❖ የሐዋርያት ጾም ስያሜና ቀኖናዊ መሠረቱ
ጾመ-ሐዋርያትን ለመጀመሪያ ጊዜ የጾሙት ቅዱሳን ሐዋርያት ሲሆኑ የጾሙበትም ዋና ምክንያት በሐምሳኛው ቀን ሀብተ መንፈስ ቅዱስ ስለተቀበሉና እግዚአብሔር ስላደረገላቸው መልካም ነገር ነው፡፡ ከዚህም የተነሣ ጾሙ የሐዋርያት ጾም ሲሰኝ ከክረምቱ መግባት ቀደም ብሎ በወርኃ ሰኔ የሚጾም በመሆኑ ደግሞ የሰኔ ጾም በሚል ስያሜ ይጠራል፡፡
ጌታችንና አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ምድር የመጣበት መለኮታዊ ዓላማ አጠናቆ ወደ ባሕርይ አባቱ ከማረጉ በፊት ቅዱሳን ሐዋርያትን ሰብስቦ “እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፤ ያዘዝኋቸውን ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” (ማቴ 28 ÷19-20) በማለት ታላቁን ተልእኮ አዟቸው ነበር፡፡ ነገር ግን በፍርሃት ውስጥ ሆነው ይህንን መለኮታዊ አደራ የተቀበሉት ሐዋርያት ለአገልግሎት ከመሰማራተቸው በፊት ከፍርሃታቸው የሚያላቅቃቸው ፤ የሚያጽናናቸው እና የሚያበረታታቸው እንዲሁም ከሐሰተኛው ዓለም ለይቶ ወደ እውነት ሁሉ የሚመራቸው ሰማያዊ ኃይል ያስፈልጋቸው ነበርና “አንትሙሰ ንበሩ ሀገረ ኢየሩሳሌም እስከ ትለብሱ ኃይለ እምዓርያም .. እናንተ ግን ኃይልን እስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ተቀመጡ፡፡(ሉቃ 24፤49) የሚል ትእዛዝ ተነግሯቸው ተስፋም ተስጥቷቸው ነበር፡፡
በተስፋውም መሠረት ኢየሩሳሌም በማርቆስ እናት በማርያም ቤት ሁሉም ተሰብስበው በጸሎት እየተጉና በአንድ ልብ ሆነው ይህንን ሕያው ተስፋ በመጠባበቅ ሳሉ ጌታችንና አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን መካከል በተነሣ በሃምሳኛው ቀን መንፈስ ቅዱስ በአምሳለ እሳት ወረደላቸው፤ ያስጨነቃቸውም የፍርሃት መንፈስ ተወግዶ በምትኩ ደፋሮችና በብዙ ቋንቋዎች የሚናገሩ ሆኑ፤ በሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ ስብከትም ብዙ ነፍሳት ዳኑ፤ ዕለቱም የቤተ ክርስቲያን መመሥረት እውን የሆነበትና አዲስ ምዕራፍ የተከፈተበት ስለነበር የቤተ ክርስቲያን የልደት ቀን ተባለ፡፡( የሐዋ. 2÷1-47)
የመንፈስ ቅዱስ ኃይል ተገልጦ ፍርሃትና ስጋታቸው የተወገደላቸው ቅዱሳን ሐዋርያት ለወንጌል አገልግሎት ከመሠማራታቸው በፊትና ሕገ ወንጌልን ከማስተማራቸው አስቀድሞ አገልግሎታቸው እንዲቃና፤ መንፈስ ቅዱስ እንዳይለያቸውና የመንፈስ ቅዱስን ምሪትና ኃይል ለመቀበል ሱባኤ ያዙ፤ ሀብተ መንፈስ ቅዱስም በአገልግሎታቸው እንደሚበዛ ሲያረጋግጡ ቅዱሱን ወንጌል የሚያገለግሉበትን ክፍለ ዓለም ዕጣ በመጣጣል ዕጣው ወደ ደረሳቸው የአገልግሎት ቦታ መሰማራታቸውን የቤተ ክርስቲያን የታሪክ መዛግብትና ሊቃውንት አባቶቻችን ያስረዳሉ፤ የመንፈስ ቅዱስን መውረድ ማለትም በዓለ ጰራቅሊጦስን ተከትሎ ከአገልግሎት በፊት በቅዱሳን ሐዋርያት የተጾመ ጾም በመሆኑ የሐዋርያት ጾም ተብሎ ተጠራ፡፡
በቅዱሳት መጻሕፍት ተመዝግቦ እንደምናገኘው የተሰጡትን ታላቅ አደራ ከመሥራታቸው በፊት የእግዚአብሔር ዕርዳታ የሚጠየቅበት መንፈሳዊ ልምምድ በቀደሙት አባቶቻችን ዘንድም የተለመደ እንደነበር እንመለከታለን ፡፡ ለምሳሌ ያክል ሊቀ ነቢያት ሙሴ ከእግዚአብሔር የተቀበለውን ሕገ-ኦሪት ለሚመራቸው ሕዝቦች ከማስተማሩ በፊት ጾሟል (ዘጸ.19)፤በንጉሡ በአርጤክስስ ቤተ መንግሥት ጠጅ አሳላፊ የነበረው ነህምያ የፈረሰውን የአባቶቹን ከተማ የኢየሩሳሌም ቅጥር መልሶ ለመሥራት በተነሣ ወቅት ጾምና ጸሎት ይዟል(ነህ 2÷11-20፤ ነህ 9) ዓለምን ለማዳን የመጣው ጌታችንና መድኃኒታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ የሆነውን ወንጌል ከመስበኩ በፊት ጾም አስፈላጊ መሆኑን ለማስረዳትና ለእኛ አርአያነቱን ሊያስተምረን እንደ ጾመ ጾሙን ከአጠናቀቀና የዲያብሎስን ፈተና ድል ካደረገ በኋላ መንግሥተ ሰማያት ቀርባለትና ንስሓ ግቡ (ማቴ 4÷1-3 ) ሲል እናገኛለን ፡፡
❖ እንዴት እንጹም
ብሉይን ኪዳንን ከሐዲስ ኪዳን አጣምራ የያዘችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንም ቅዱሳት መጻሕፍትን በመመርመርና ታሪክን በመፈተሽ የቅዱሳን ሐዋርያትን ጾም ከሰባቱ የአዋጅ አጽዋማት መካከል አንዱ ሆኖ በአዋጅ እንዲጾም በቀኖናዋ ሠርታለች፡፡ በቅዱሳን ሐዋርያት ላይ ያደረው ጸጋ መንፈስ ቅዱስና ሀብተ መንፈስ ቅዱስ በእኛም ላይ እንዲያድር፤ ከቅዱሳን ሐዋርያቱ በረከት እንድንሳተፍ፤ አገልግሎታችን በስኬት እንዲቃና እና ወርኃ ክረምቱ በሰላም ያልፍልን ዘንድ እንዴት እንጹም የሚለው ሐሳብ ወሳኝ ጥያቄ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ቃል እንዴት መጾም እንዳለብን ደግሞ ከታች በተዘረዘሩት መልኩ እንድንጾም ታዝዘናል፡፡
✞ ከልብ ንስሓ በመግባት (ኢዩ 2÷12)
✞ ከምጽዋትና ከጸሎት ጋር የሆነ (ማቴ. 6÷1-15)
✞ እግዚአብሔር ደስ በሚሰኝበት መንገድ (ኢሳ 58÷4-8
✞ ከግብዥነት ሕይወት በጸዳ መልኩ (ማቴ 6÷16-18)
ወድ አንባብያን ሆይ የጾምን ዓላማና ትርጉሙን ከመረዳት ጀምሮ ከላይ የዘረዘርናቸውን መንፈሳዊ ሥርዓቶች በተገባ መልኩ አሟልተን ከጾምን ነቢዩ ኢዮኤል እንደተናገረው በጾምን እንቀደሳለን፤እግዚአብሔርም በደላችንን እና መተላለፋችንን ይቅር ይለናል፤ በከባድ ወቅታዊ ሁኔታ እና በጽኑ ፈተና የታጠረችውን እና በአስፈሪ ጨለማ ውስጥ የወደቀችውን ምድራችንንም ይታደጋል፤ ቸርነትና ምሕረቱም በሀገራችን ይበዛል፡፡ ከጸሎትና ከምጽዋት ጋር በሚገባ ጾመን ከራሳችንን እና ከእግዚአብሔር አምላካችን ጋር የምንታረቅበት ሱባኤ ያድርግልን፤ የቅዱሳን አባቶቻችን ሐዋርያት በረከትና ጸሎትም አይለየን እያልኩ ማቴ 6÷1-18 እና ኢሳ 58÷1-14 ያሉትን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ታነቡ ዘንድ እጋብዛለሁ፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር ፡፡
መ/ር ሽፈራው እንደሻው ከሀገረ ስብከቱ ሚዲያ ክፍል