በአዲስ መልክ የተሠራው የጉራራ ኪዳነ ምሕረት ህንጻ ቤተ ክርስቲያን ተመረቀ

በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በየካ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት የሚገኘው የጉራራ ምስራቀ ፀሀይ ቅድስት ኪዳነ ምህረት እና የቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ግንቦት 29/2012ዓ.ም ቅዳሴ ቤቱ ተፈጽሞ ተመርቋል።

በምረቃው ሥነስርዓት ላይ የምዕራብ ሐረርጌ ሀገረ ስብከተ ሊቀ ጳጳሰ ብፀዕ አቡነ እንጦስ ፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ስራ አስኪያጅ መልአከ ህይወት አባ ኃይል ገብርኤል ነጋሽ ፣ የደብሩ ካህናትና የአካባቢው ምዕመናን በተገኙበት ተመርቋል።
ብፁዕ አቡነ እንጦንስ በዕለቱ ባስተላለፉት መልዕክት እግዚአብሔር የፈቀደለት ሰው ብቻ ነው ቤቱን የሚሠራው እናንተ ዕድለኞች ናችሁ ስለተፈቀደላቸው የእግዚአብሔር ቤት ሠርታችዋል ደስ ይበላችሁ ትጉና ጸልዩ በማለት ሰፊ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በመቀጠል ክቡር መልአከ ሕይወት አባ ኃይል ገብርኤል ነጋሽ የደብሩ ካህናትና ምዕመናን ላደረጉት አስተዋፅኦ፣ ለሥራቸው ትጋት አመስግነው፣ በማያያዝም ቀሪ ሥራዎች እንዲጠናቀቁ በማሳሰብ በማናቸውም ሁኔታ አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ከደብሩ ጎን መሆኑን ገልጸዋል።

የጉራራ ደብረ ፀሀይ ቅድስት ኪዳነ ምህረት እና ቅዱስ ገብርኤል ህንጻ ቤተ ክርስቲያን መሠረት የተጣለው 2006 ዓ.ም ቢሆንም በመሐል አለመግባባት ተፈጥሮ ሥራው ላይ ጫና ተፈጥሮ ቆይቶ የነበረ ሲሆን በክቡር መልአከ ሕይወት አባ ኃይል ገብርኤል ነጋሽ የአዲሰ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ስራ አስኪያጅ ብርቱ ጥረትና ክትትል ችግሩ ተፈቶ በእግዚአብሔር ፈቃድ ግንቦት 29/2012 ዓ.ም ህንጻ ቤተ ክርስቲያኑ ተመርቋል።