የተስፋ ልዑክ ዐቢይ ኮሚቴ ሪፓርትን በተመለከተ የሀገረ ስብከቱ ምላሽ

ዓለም አቀፋዊ የኮሮና ወረርሽኝን ተከትሎ ስርጭቱን ለመቀነስና ለመግታት ከዚህ ቀደም ምእመናን በቤታቸው በጸሎት እንዲተጉ በቋሚ ሲኖዶስ የተወሰነውን ውሳኔ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በቀን 5/9/2012 ዓ.ም. ባደረገው ስብሰባ በድጋሚ ተመልክቶ በጉዳዩ ላይ መክሮ እና አፈጻጸሙን ገምግሞ ወረርሽኙን ለመከላከል በሚያስችል መልኩ በባለሙያዎች የሚሰጠውን ጥንቃቄ በማድረግ ምእመናን በአምልኮተ እግዚአብሔር እንዲሳተፉ ወስኗል፡፡
ቋሚ ሲኖዶስ የወረርሽኙን ሥጋት ተከትሎ ምእመናንን ለመታደግ በሚል ሥርዓተ አምልኮው በውሱን አገልጋዮች እንዲፈጸምና የሰላም ልዑክ ግብረ ኃይል ከአጥቢያ እስከ ጠቅላይ ጽ/ቤት ድረስ እንዲዋቀር በወሰነው መሠረት የሀገረ ስብከታችን ጽ/ቤትም ግብረ ኃይል በማቋቋም ክትትል ሲያደርግ ቆይቶ፤ ከክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት፣ ከገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎችና በተለያዩ መንገዶች ከምእመናን በቀረቡ ጥየቄዎች መሠረት፤ ምእመናን በቤተ ክርስቲያን ተገኝተው ሥርዓተ አምልኮታቸውን እንዲፈጽሙ ማድረግ እንዲቻል ከመፍትሔ አሳቦች ጋር ማሳሰቢያ ማቅረቡ የሚታወስ ነው፡፡
ከዚህ ጋራ በተያያዘ ዐቢይ የተስፋ ልዑክ ግብረ ኃይሉ ለምልዓተ ጉባዔው ባቀረበው ሪፖርት የሀገረ ስብከታችን ጽ/ቤትን ለማሳጣት ሐቅ የጎደላቸው ሐሳቦችን ማንጸባረቁ ሐራ ተዋሕዶ ከተባለ ድረ ገጽ ላይ ተለጥፎ መታየቱ ጽ/ቤታችንን አሳዝኗል፡፡ የሀገረ ስብከታችን ጽ/ቤት ከተስፋ ልዑክ ግብረ ኃይል የሥራ እንቅስቃሴ ጋራ በተያያዘ፡-
✥ ከጠቅላይ ጽ/ቤቱ የቋሚ ሲኖዶስ ውሳኔ በጽሑፍ ሳደርሰው ግብረ ኃይል አቋቁሟል፤
✥ በክፍላተ ከተማ እና በአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ግብረ ኃይል እንዲቋቋም አድርጓል፤
✥ በጠቅላይ ጽ/ቤት የተላለፈውን የሥርዓተ አምልኮ መፈጸሚያ መመሪያ እንዲሠራጭ አድርጓል፤
✥ ኮሚቴው ከጉዳዩ ጋራ በተያያዘ በተደጋጋሚ በመገናኘት መክሯል፤ ውሳኔዎችንም አሳልፏል፤
✥ የኮሚቴው ዓባላት በተለያዩ አድባራት ለምሳሌ በታዕካ ነገሥት በዓታ ለማርያም፣ በጎላ ጽ/ጽዮን ቅዱስ ሚካኤል፣ በቤላ ቅዱስ ዮሐንስ፣ በሐመረኖኅ ኪዳነ ምህረት ገዳም ወዘተ የመስክ ምልከታ በማድረግ መምህራንን፣ ተማሪዎችንና ካህናት ለመታደግ በባለሙያ የተደገፈ ሥልጠና (ማብራሪያ) ሰጥቷል፤
✥ በቴሌቪዥን የስብከት አገልግሎት የሚሰጡ መምህራነ ቤተ ክርስቲያን ለማወያየት በተዘጋጀው የምክክር መድረክ አመቻችነቱን ሚና ተጫውቷል፤
✥ የቀጥታ ሥርጭት የሚደረግባቸውን አድባራት ልየታና ግንኙነት በመፍጠር የበኩሉን ሚና ተጫውቷል፤
✥ የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ክቡር መልአከ ሕይወት ቆሞስ አባ ኃይለ ገብርኤል ነጋሽ ወርኀዊ በዓላት በሚከበርባቸው አድባራት በአካል በመገኘት ምእመኑ እንዲጠነቀቅ መልእክት አስተላልፈዋል፣ ክትትል አድርገዋል፤ መመሪያውን ባልተገበሩ አካላት ላይም መዋቅሩን የጠበቀ ማስተካከያ እንዲሰጥ መመሪያ አስተላልፈዋል፤
✥ ወረርሽኙ ያመጣውን ተጽዕኖ ለመከላከል ከሀገረ ስብከቱ ግብረ ኃይል ቅርጫፍ የሆነ ርዳታ አሰባሳቢ ኮሚቴ በማዋቀር ወደ ሥራ ገብቷል፤
ይሁን እንጂ “በዚህ ደብር ብዙ ሕዝብ ተሰብስቧል እንዲበተኑ አድርጉ፣ አስተዳዳሪውን አግዱ” በማለት በሽታው ካመጣው አለመረጋጋት ተጨማሪ ሽብር ለመፍጠር በሚመስል መልኩ ሲተላለፍ የነበረው የግለሰቦች “መመሪያ” ባለመተግበሩ ብቻ፤ ሀገረ ስብከቱን እንደ ሥራ አደናቃፊ ቆጥሮ እንዲሁም ዋና ሥራ አስኪያጁ ካለባቸው ከፍተኛ የሥራ ሓላፊነት አንጻር በየዕለቱ ለረጅም ሰዓታት በሚደረጉ ስብሰባዎች አልተገኙም ብሎ ሪፖርት ማድረግ የሀገረ ስብከቱን ስም ለማጉደፍ የሚደረግ ስልታዊ ጥቃት ሆኖ ተመልክተነው እጅግ አሳዝኖናል፡፡
የሀገረ ስብከቱ የተስፋ ልዑክ ግብረ ኃይል የየዕለት ሁኔታዎች በመመልከት ከሆሳዕና ጀምሮ እስከ ትንሣኤ የነበሩ በዓላት በልዩ ፈቃድ ምእመናን ተገኝተው እንዲከበሩ ሲያደርግ የነበረውን ጥረት ወደ ጎን በመተውና ባለመቀበል፤ የምእመናን ጩኸት ሲበረታ ደግሞ ጥያቄውን የራስ በማድረግ የተደረገው እንቅስቃሴ ራስን ከተጠያቂነት ለማዳን እንጂ ለምእመኑ ጥያቄ ታስቦ እንዳልነበር እየታወቀ፤ አሁንም የራስን መልካም ስም ለመገንባት እና በተስፋ ልዑኩ በኩል የሚታየውን ከወሬ ያላለፈ የማስፈጸም አቅም ውሱንነት ለመሸፈን ሲባል የሀገረ ስብከቱን ስም ሪፖርት በሚመስል ጽሑፍ ማጉደፍ ለቀና ሐሳብ በፈቃደኝነት ከተሰባሰቡ ሰዎች የሚጠበቅ አለመሆኑን ልናስገነዝብ እንወዳለን፡፡
በመጨረሻም ሀገረ ስብከታችን የተስፋ ልዑክ ግብረ ኃይሉን በአዲስ መልክ በማጠናከር እቅስቃሴውን የጀመረ ሲሆን፤ አሁንም ቤተ ክርስቲያናችን ልዕልናዋና ክብሯ ተጠብቆ መንፈሳዊ አግልግሎቷን እንድታከናውንና ተልዕኮዋን ለማስቀጠል የምንሠራ መሆናችንን እየገለጽን፤ እርስ በእርስ በመተቻቸትና ስም በማጉደፍ ሳይሆን፤ በቅንነት፣ በፍቅርና በመተሳሰብ ላይ የተመሠረተ የተጠራንለትን አገልግሎት እንድፈጽም መንፈሳዊ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡
የሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት
አዲስ አበባ
ግንቦት 6 ቀን 2012 ዓ.ም.