የአ/አ/ሀ/ስ/ ዋና ስራ አስኪያጅ መ/ሕ/ አባ ኃይል ገብርኤል ነጋሽ በተለምዶ 22 ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በመሠራት ላይ ያለው የቦሌ ቅድስት አርሴማና ቅዱስ ገብርኤል ህንፃ ቤተ ክርስቲያን ጎበኙ
ይህ ቦታ ከወራት በፊት የሁለት ኦርቶዶክሳውያን ወንድሞች ሕይወት የጠፋበትና የበርካታ ክርስቲያኖችም አካል የጎደለበት እንዲሁም የብዙ ምእመናን ልብ የተሰበረበት ቦታ የነበረ ሲሆን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቤተ ክርስቲያኒቱ እና የምእመናኑ ጥያቄ ተቀብሎ ቤተ ክርስቲያን እንዲሠራ በፈቀደው መሠረታ ሁለቱ ኦርቶዶክሳውያን ወንድሞች ሕይወት በጠፋበት ቦታ የቅድስት አርሴማና የቅዱስ ገብርኤልህንፃ ቤተ ክርስቲያን እንዲሰራ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቀነ ጳጳስ ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት መሠረት ድንጋይ መቀመጡ ይታወቃል።
በዚሁ መሠረት ሥራው ሲሰራ ቆይቶ ዛሬ ሚያዝያ 27/2012 ዓ.ም የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ስራ አስኪያጅ መልአክ ሕይወት አባ ኃይል ገብርኤል ነጋሽ ከሀገረ ስብከቱ የሥራ ኃላፊዎች ጋር በመሆን በማለዳው በቦታው ላይ በመገኘት የህንፃ ቤተ ክርስቲያኑ ያለበትን ሁኔታ ምልከታ አድረገዋል።
ክቡር ዋና ስራ አስኪያጁ በመሥራት ላይ የሚገኘው ህንፃ ቤተ ክርስቲያኑ ከጎበኙ በኋላ “ክብርና ምስጋና ለእግዚአብሔር ይሁን የወንድሞቻችን ደም ፍሬ አፍርቷል ” ብለዋል።
የአካባቢው ምዕመናን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለሠሩት ሥራ አመስግነው ጸሎት አድርገውላቸዋል።
በጉብኝቱ ማጠቃለያ ላይ ዓለም ክፉ ፈተና እንዳጋጠማት በማውሳት ሁሉም ከዚህ ደዌ ራሱን እንዲጠብቅ፣ ያለው ለሌለው እንዲያካፍል፣ በመተጋገዝና በመረዳዳት ወደ ፈጣሪ ከልብ በመመለስ እንዲጸልይ አጽንኦት በመስጠት ጉብኝቱ አጠናቋል።
የዘገባው ምንጭ ፦ የሀገረ ስብከቱ ሕዝብ ግኑኝነት ዋና ክፍል ነው