የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ክቡር መልአከ ሕይወት አባ ኃይለገብርኤል ነጋሽ(ቆሞስ) በወቅታዊ ጉዳይ ላይ መግለጫ ሰጡ
“አምጣነ ብነ ዕለተ ንግበር ሠናየ ለኵሉ ወፈድፋደሰ ለሰብአ ሃይማኖት”
“እንግዲያስ ጊዜ ካገኘን ዘንድ ለሰው ሁሉ ይልቁንም ለሃይማኖት ቤተሰዎች መልካም እናድርግ፡፡” ገላ.6፡10
መልካም ማድረግ ከበጎ አስተሳሰብ፣ ከመልካም ስብእና ይመነጫል፡፡ በዚህ ዘመን ዓለማችን በኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ 19) ምከንያት በተረበሸችበት ወቅት፤ በበሽታው ምክንያት ለተጎዱ፣ ቀን ለጎደለባቸው፣ ወገኖች ሁሉ የበኩላችንን ድጋፍ ማድረግ ለሰው ልጆች ሁሉ የተገባ ግብረ ገባዊ (ሞራላዊ) ግዴታ ነው፡፡
ሀገራችን ኢትዮጵያም በዚህ ወረርሽኝ ምክንያት ሊመጣ ከሚችለው አስከፊ ችግር ለመዳን ጥንቃቄ የተመላበትን ተግባር በጎ አድራጊዎችን በማስተባበር እያከናወነች ትገኛለች፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንም ለዚህ ጉዳይ በቋሚ ሲኖዶስ ውሳኔ የሦስት ሚሊየን ብር ድጋፍ እና ትምህርት ቤቶቿንና ኮሌጆቿ ለህሙማን ማቆያ ዝግጁ ማድረጓ ይታወሳል፡፡
ከዚህ ድጋፍ በተጨማሪ የበሽታውን ተስፋፊነት ለመግታት በታላቅ መንፈሳዊ አምልኮ የምታከብረውን ዐቢይ ጾምና ዐበይት በዓላት ምእመናን በቤታቸው ተወስነው ጸሎታቸውን እንዲያደርሱ በመወሰን፤ በውስን አገልጋዮች መንፈሳዊ አገልግሎቱ እንዲመራ አድርጋለች፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ውሳኔ ምእመናን ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን ጋር ያደርጉት ከነበረው የዕለት ተዕለት ግንኙነት ሲቋረጥባቸው ከሚፈጠርባቸው የመንፈሳዊ ሐዘንና ቁጭት ስሜት በተጨማሪ፤ በምእመናን አስተዋጽዖ የሚገለገሉት በሀገረ ስብከታችን የሚገኙ ከ200 በላይ ገዳማትና አድባራትን እንዲሁም በአብያተ ክርስቲያኑ የሚያገለግሉ ካህናትንና ቤተሰቦቻቸውን ለከፋ አደጋ የሚዳርግ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡
በመሆኑም ሀገረ ስብከታችን ይህንን ክፉ በሽታ እግዚአብሔር እንዲያስወግድልን ከመጸለይ ጋራ በዚህ ወቅት ከማናቸውም ሥራ ቅድሚያ በመስጠትና ሙሉ ጊዜውን በመሰዋት በበሽታው ምክንያት ሊመጣ የሚችለውን ችግር ለመቅረፍ የሚያስችል ዝግጅት በማድረግ ከሀገረ ስብከትና ከአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት የተዋቀረ ኮሚቴ በመሰየም ገንዘብና ደረቅ ምግቦችን የመሰብሰብ ተግባር ለማከናወን አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት አጠናቋል በዚህም መሰረት ደረቅ ምግቦችና የንፅህና ቁሳቁሶች በጊዜያዊነት የሚሰበሰቡባቸው አብያተ ክርስቲያናት፦
- ቦሌ ደብረ ሳሌም መድኃኔ ዓለምና ቅዱስ ዮሐንስ ካቴድራል፣
- ደ/ም/ሰአሊተ ምሕረት ቅድስት ማርያም ካቴድራል፣
- ደብረ ጽጌ ቅዱስ ዑራኤል ቤተክርስቲያን፣
- ደብረ ብሰራት ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን በመሆናቸው የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናን ቅዱስ ጳውሎስ እንደተናገረ በቤተክርስቲያናችንና በአገልጋዮቿ የተጋረጠውን ይህንን ከፍተኛ አደጋ ልንሻገረው የምንችለው በጋራ ስንረባረብ ነውና በአብያተ ክርስቲያናቱ በመገኘት ደረቅ ምግቦችንና የንፅህና መገልገያ ቁሳቁሶችን እንድትለግሱ እንዲሁም በብፁዕ ወቅዱስ አባታችን መልካም ፈቃድ ለዚህ አገልግሎት ብቻ እንዲውል በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተከፈተው ዝግ የሂሳብ ቁጥር 1000328711404 የአቅማችሁን ርዳታ እንድታደርጉ እየገለጽን፤ መምህራን፣ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች፣ መንፈሳዊ ማኅበራት ይህን የተቀደሰ ዓላማ በማስተዋወቅና በማስተባበር እንድትተባበሩ መንፈሳዊ ጥሪያችንን በቤተ ክርስቲያናችን ስም እናስተላልፋለን፡፡
“ወረሲ ኀዋኅወ ቤተ ክርስቲያንከ ቅድስት ርኅዋተ ለነ በምሕረት ወአሚን”
የቅድስት ቤተ ክርስቲያንህንም ደጆች በምሕረትና በሃይማኖት እንዲከፈቱ አድርግልን።
መልአከ ሕይወት አባ ኃይለ ገብርኤል ነጋሽ(ቆሞስ) የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅና የአዲስ አበባ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የቦርድ ሰብሳቢ
ሚያዝያ 16/2012 ዓ/ም
አዲስ አበባ
ኢትዮጵያ