የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ክቡር መልአከ ሕይወት አባ ኃይለገብርኤል ነጋሽ(ቆሞስ) የ2012 ዓ.ም የትንሣኤ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን !
እንኳን ለ2012 ዓ.ም. ለጌታችንና ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ትንሣኤ በሰላም አደረሳችሁ !
“እንደ ተናገረ ተነሥቶአልና” ማቴ. 28፡6
ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለአዳም በሰጠው ተስፋ ፣ ለነቢያት በገለጠው ምሥጢር ፣ ለጠቢባን ባሳየው ሱባዔ ዘመኑ ሲደርስ እንደ ተወለደ፣ በዘመኑም ራሱን ለሞት አሳልፎ ሰጥቷል ። ለደቀ መዛሙርቱ ለጆሮአቸው ባይጥምም እሞታለሁ በማለት ልባቸውን ሲያዘጋጅ ፣ የመከራ ወዳጆች እንዲሆኑም ሲያሰናዳ ቆይቷል ። እርሱ አስቀድሞ የሚናገረው ፈርቶ ወይም ያውቃል እንዲሉት ሽቶ ሳይሆን የአማንያንን ልብ ከክህደት ፣ ኅሊናቸውን ከፍርሃት ፣ አእምሮአቸውን ከድንገተኛ ነገር ለመጠበቅ ነው ። ሰው ግን ከደስታ በኋላ መከራ ፣ ከቀን በኋላ ሌሊት እንደሚመጣ ይዘነጋልና ከደቀ መዛሙርቱ ፊታውራሪ የነበረው ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ምሎ ጌታውን ካደ ። እንዲሁ ቢክድ በተሻለ ነበር ፣ ምሎ ግን አላውቀውም አለ ። ዓለም ያወቀውን ፣ ፀሐይ የሞቀውን ክርስቶስን ማወቅ የሚያስጠይቅ አልነበረም ። ሐዋርያው ጴጥሮስ ግን ያለ አንቀጽ ፈራ ፣ ያለ ፍርድ ካደ ። ጌታችን ግን አስቀድሞ የተናገረው የአማንያንን ልቡና ለመጠበቅና በክፉ ቀን እንዳይከፉ በጸሎት ለማትጋት ነበር ።
ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተናገረው ሞቱን ብቻ ሳይሆን ትንሣኤውንም ነው ። ሞት ባይነገርም ሥጋ የለበሰ ሁሉ ያውቀው የለም ወይ( ይባል ይሆናል ። እነሣለሁ ማለት ግን በየትኛውም ዘመን የተነሡ ነገሥታትና ጠቢባን ያልተናገሩት ነው ። እነሣለሁ ብለው የተናገሩም ቃል ብቻ ሁነው ቀርተዋል ። ዛሬም መዘበቻ ሁነው ይነሣሉ ። ጌታችን መነሣቱ ግን እውነት ነው ። ሐዋርያው ጳውሎስ በ1ኛ ቆሮ. 15፡4 ላይ እንደ ተናገረው አስቀድሞ ለኬፋ ታይቷል ። ኬፋ የተባለው ጴጥሮስ ነው ። ክርስቶስ በርግጥ ባይነሣ ኑሮ ጴጥሮስ የቁልቁሊት ተሰቅሎ አይሞትም ነበር ። እውነት ላልሆነ ነገር የሚሞት የለምና ። ሐዋርያው ጴጥሮስ በሰማዕትነት እንደ ተሰየፈ በታሪክ ተጽፎአል ። የእርሱ ሰማዕትነት የክርስቶስን ትንሣኤ እውነተኛነት ያረጋግጣል ። ተቃዋሚ የነበረው የጥንቱ ሳውል የአሁኑ ጳውሎስም ክርስቶስ ባይነሣ ኑሮ ረቢ ተብሎ ከሚከበርበት ወንበር ፣ ሳንሄድሪን ከተባለው የአይሁድ ሸንጎ አባልነት ወጥቶ ስደተኛ ሰባኪ ባልሆነ ነበር ። በርግጥም ክርስቶስ ተነሥቷል ።
ቤተ ክርስቲያን ከትንሣኤ ጀምሮ ለቀጣይ ሃምሳ ቀናት ወራቱን እንደ አንድ ቀን ቆጥራ ፣ በትኩስነት ትንሣኤን ታከብራለች ። በእነዚህ ቀናትም ሰላምታዋ ፡-
“ክርስቶስ ተንስአ እሙታን
በዐቢይ ኃይል ወስልጣን
አሰሮ ለሰይጣን
አግአዞ ለአዳም
ሰላም እምይእዜሰ
ኮነ ፍስሐ ወሰላም
ክርስቶስ ከሙታን ተነሣ ፣
በታላቅ ኃይልን ሥልጣን ።
ሰይጣንን አሥረ ፣ አዳምን ነጻ አወጣው ፣
ከዛሬ ጀምሮ ሰላምና ደስታ ሆነ” ትላለች ።
የክርስቶስን መነሣት ጥንታውያን አብያተ ክርስቲያናትም “ክርስቶስ ተነሣ” ሲባል “በእውነት ተነሣ” እያሉ ሃምሳውን ቀን ይዘክራሉ ፣ ያውጃሉ ። ክርስትናን ልዩ የሚያደርገው በትንሣኤው ማመናችን ነው ። የክርስቶስን ሞት ሁሉም ይቀበለዋል ። ትንሣኤውን የምናምን ግን እኛ ክርስቲያኖች ብቻ ነን ።
ይህንን በዓለ ትንሣኤ ስናከብር ዓለምን ሁሉ በአንድ ቋንቋ ባናገረው በኮሮና ቫይረስ ምክንያት በቤታችን ተቀምጠን ቢሆንም ከፊት ለፊታችን የሚያንዣብበውን የሞት ፍርሃት በትንሣኤው ድል እየነሣን ነው ። እኛ የትንሣኤ ሠራዊት ነን ። ክርስትናችን የተመሠረተው ድል ላይ ነው ። በክርስቶስ ትንሣኤ በሽታ ብቻ ሳይሆን የሞት መርዝም ተነቅሎልናል ። ስለዚህ የሚመጡ ክስተቶች እምነታችንን እንዳይነኩብን መጠንቀቅ ይገባናል ። ይህ እንደሚሆን ፣ ወረርሽኝም በመጨረሻው ዘመን የምጽአት ዋዜማ ሁኖ ዓለምን እንደሚያስጨንቅ ጌታችን በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 24 ላይ ተናግሯል ። የተናገረውም እንድንጠነቀቅ ነው ። ስለዚህ መጠንቀቃችን አለማመናችን ሳይሆን የጌታችንን ቃል ማመናችን ነው ። መጠንቀቅ ግን ፍርሃት እንዳይሆንብንና ከበሽታ የከፋው ጭንቀት እንዳይቆጣጠረን ማሰብ ያስፈልገናል ። እኛ ብንኖርም ብንሞትም ለክርስቶስ ነንና ። ትንሣኤውም የታመሙ እንደሚነሡ ፣ በበሽታ ስጋት ውስጥ ያሉም ልባቸውን እንዲያበረቱ የሚናገር ድምፅ ነውና ምእመናን በርቱ ።
ይህንን የትንሣኤ በዓል ስናከብር ከበሽታ ቀጥሎ የሚከሰት የኑሮ እጥረት አለና ድሆችን ማገዝ ያስፈልጋል ። ይህ ቀን ትምህርት ሁኖን ከስስት ካልፈታን መቼም ልንማር አንችልም ። ስለዚህ ጎረቤታችሁን ስታስቡ እግዚአብሔርም የተቀሰፈችዋን ምድር በመልካም ያስባታል ።
ካህናትም የእግዚአብሔር እንግዶች ናቸውና በዚህ በበሽታ ዘመን በረሀብ እንዳይጠቁ ምእመናን ልባችሁን አንቅታችሁ ፣ ዓይናችሁን አንሥታችሁ ፣ እጃችሁን ዘርግታችሁ ልታስቡአቸው ይገባል ። ዛሬ ደጁ ሲዘጋ እንደ ተጨነቃችሁ ካህናት ከሌሉ ደግሞ የበለጠ የእግዚአብሔር ቤት ይዘጋልና በጥምቀት ልጅነትን የሚያሰጡን ፣ ኃጢአት ሲጫነን የሚናዝዙን፣ ስንሞት የሚቀብሩን ካህናት በዚህ በበሽታ ዘመን ደመወዝ አጥተው እንዳይቸገሩ በያላችሁበት ሆናችሁ የአብያተ ክርስቲያናቱን የባንክ የሂሳብ ቁጥር በመውሰድ እና በመሳሰሉት አቅማችሁ የፈቀደውን ድጋፍ እንድታደርጉ በሀገረ ስብከታችን ስም ጥሪያችንን እናስተላልፋለን። ያልተነገረላቸው ድሆች ካህናት ናቸውና ምእመናን ይህን ጥሪ ልብ እንድትሉ አደራ እንላለን ።
በዓሉንም የሰላምና የምሕረት ያድርግልን ። የታመሙትን በትንሣኤው ኃይል ከእኛ ጋር አቁሞ ማዳኑን እንዲናገሩ ያብቃልን ።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
መልአከ ሕይወት አባ ኃይለ ገብርኤል ነጋሽ(ቆሞስ)
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ