የፍኖተ ሎዛ ቅድስተ ማርያም ወአቡነ አረጋዊ ቤ/ክ/ተዘግቶ የነበረውን የአሰተዳደር ሠራተኞች ቢሮ በክብር የሀገረ ስብከቱ ዋና ስራ አስኪያጅ መመሪያ ሰጭነት ተከፈተ

ባለፈው አንድ ወር አካባቢ በደብሩ ካህናትና በደብሩ ጽ/ቤት አስተዳደር ሠራተኞች መካከል አለመግባባት ተፈጥሮ የነበረ ሲሆን የደብሩ ካህናት በቦታው አለ ያሉትን ችግር በዝርዝር ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ባቀረቡት መሠረት ክቡር መልአክ ሕይወት አባ ኃይል ገብርኤል ነገሽ(ቆሞስ) የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ስራ አስኪያጅ በአስቸኳይ አጣሪዎች ወደ ደብሩ የላኩ ቢሆንም ቀደም ብሎ የታሸገው ቢሮ ሳይከፈት እና የሀገረ ስብከቱ መመሪያ ሳይተገበር ቆይቷል።

ዛሬ ጠዋት መጋቢት 24/2012 ዓ.ም የሀገረ ስብከቱ ዋና ስራ አስኪያጅ በደብሩ በመገኘት ስለ ወቅታዊ ጉዳይ ኮቪድ-19 አስመልክቶ ለሁሉም ጊዜ አለው፣ አሁን ዓለም ያለበት ሁኔታ በጣም አስቸጋሪ እንደሆነ በመግለጽ እንዃንስ ተጣልተን በፍቅርም ዘመኑን መሻገር ከቻልን ጥሩ ነው ብለዋል ።

ከእኛ በላይ አቅም ያላቸው፣ ብዙ ሀብትና ዕውቀት ያካበቱ ሀገሮች ሊቋቋሙት ያልቻሉት ችግር ተከስቶ፣ ሁላችንም ፊታችን ወደ ፈጣሪ መልሰን በያለንበት ሆነን ማረን እያልን ወደ ፈጣሪ ማልቀስ የሚገባን ሰዓት እንጂ የምንጣላበት ወቅት አይደለም በማለት መክረዋል ።

በደብሩ ችግር አለ ተብሎ አቤቱታ እንደ ቀረበ፣ ውለን ሳናድር በአስቸኳይ አጣሪ ልከናል፣ በሚቀርበው ግኝት / ሪፖርት ተመስርተን አስፈላጊውን ማስተካከያ እናደርጋለን፣ ውግንናችን ለእናት ቤተ ክርስቲያን ነው ብለዋል።
የአስተዳደር ሠራተኞች ቢሮ ማሸግና ስራ ማደናቀፍ ተገቢ እንዳልሆነ የገለጹት ዋና ስራ አስኪያጁ፣ በእሸጋው የተሳተፉ አካላት ድርጊቱ ትክክል አልነበረም በማለት የታሸጉ ቢሮዎችን አስከፍተዋል።

በተደረሰው የጋራ ስምምነት መሠረትም ዓርብ መጋቢት 25/2012 ዓ.ም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ የሀገር ስብከቱና የክፍለ ከተማው ተወካዮች እና የሚመለከታቸው የደብሩ የሥራ ኃላፊዎችና ሥራተኞች በተገኙበት የሙዳየ ምጽዋት ቆጠራ ይካሄዳል።

የደብሩ ሠራተኞችም በዚህ ፈታኝ ወቅት በደብራችን በመገኘት ችግራችንን ስለ ሰሙን እናመሰግናለን በማለት ክቡር ዋና ስራ አስኪያጁን አመስግነዋል።

ፍኖተ ሎዛ ቅድሰተ ማርያም ወአቡነ አረጋዊ ቤተ ክርስቲያን ተመስርታ ለምዕመናን አገልግሎት መስጠት ከጀመረች ከ13 ዓመታት በላይ ሆኗታል።

                             የዘገባው ምንጭ የሀገረ ስብከቱ ሕዝብ ግኑኝነት ዋና ክፍል ነው