የአ/አ/ሀ/ስ/ዋና ስራ አስኪያጅ መልአክ ሕይወት አባ ኃይል ገብርኤል ነጋሽ ለቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ተገዢ ልንሆን ይገባል አሉ

በሀገራችን ኢትዮጵያ የተከሰተው የኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝ በሕዝባችን ላይ የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ ከወዲሁ ካህናትና ምዕመናን በጸሎት እንዲተጉ፣ ከመንግሥት እና ከጤና ባለሙያዎች የሚሰጠውን ትምህርት በተግባር ላይ እንድናውል ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ መወሰኑ ይታወቃል።

የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ስራ አስኪያጅ መልአክ ሕይወት አባ ኃይል ገብርኤል ነጋሽ መጋቢት 22/2012 ዓ.ም ከቅዳሴ መልስ በኋላ በደብረ ፅጌ ቅዱስ ዑራኤል ቤተ ክርስቲያን የሰርክ ጉባኤ ላይ በድንገት በመገኘት የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ተግባራዊነት ምን ደረጃ ላይ እንዳለ መልከታ አድርገዋል።

የደብረ ፅጌ ቅዱስ ዑራኤል ቤተ ክርስቲያን የሰርክ ጉባኤ እንደ ወትሮው ግቢው በሰው የተጨናነቀ በመሆኑ ከወቅቱ ሁኔታ ጋር የተገናዘበ አለመሆኑ መርዳት ተችሎአል ።

በቦታው የደብሩ የሥራ ኃላፊዎች ያልተገኙ በመሆኑ የተላለፈውን የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ተከታትሎ ከመፈጸምና ከማስፈጸም አኳያ በግልጽ ከፍተት መኖሩን ያሳያል ።

ክቡር መልአክ ሕይወት አባ ኃይል ገብርኤል ነጋሽ (ቆሞስ) የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ስራ አስኪያጅ በቦታው ላይ ተገኝተው አባታዊ መመርያ ያስተላለፉ ሲሆን፣የሕዝበ ክርስቲያኑ ጤንነት እንዲጠበቅ እና ከመጣው መቅሰፍት እንድንጠበቅ ከሚመለከታቸው አካላት የሚሰጡትን ትምህርቶች በአግባቡ በሥራ ላይ ማዋል እንደሚገባ ሰፊው መክረዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርሰቲያን በቁጥር ሰፊ ምዕመናንና ካህናት ያሏት ጥንታዊትና ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን ናት፣ ዛሬ በሀገራችን የተጋረጠውን ፈተና በፆምና በጸሎት በመትጋት እንዲሁም ከጤና ባለሙያዎች የሚሰጡትን ትምህርቶች በበጎ መልኩ በመውሰድ ልንጠቀምበት ይገባል ብለዋል ።

ወጣቶች የሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎችም ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚመጡትን ምዕመናን በተቀመጠው የጥንቃቄ ርቀት መሠረት በመግቢያና በመውጫ አካባቢዎች የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ በማቅረብ ሕዝበ ክርስቲያኑን እንዲያገለግሉ ክቡር ዋና ስራ አስኪያጁ አባታዊ መልእክት አስተላልፈዋል።

                                           በሀገረ ስብከቱ ሕዝብ ግኑኝነት ዋና ክፍል