የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት መግለጫ አወጣ
መነሻውን ከሀገረ ቻይና ያደረገውና መላው ዓለምንና ሀገራችንን ኢትዮጵያን ከማስጨነቁና የብዙ ወገኖቻችንን ሕይወት ከመቅጠፉም ባሻገር ለከፍተኛ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ቀውስ ምክንያት እየሆነ የሚገኘውን የኮረና ቫይረስ ወረርሽኝ አስመልክቶ የሀገረ ስብከታችን ዋና ሥራ አስኪያጅ መልአከ ሕይወት ቆሞስ አባ ኃ/ገብርኤል ነጋሽ የሚዲያ አካላት በተገኙበት ወቅታዊ መግለጫ በጽ/ቤታቸው ሰጡ፡፡
በመግለጫውም ላይ የበሽታውን ስርጭት ለመቀነስም ሆነ ራሳችንን ከጥቃቱ ለመከላከል በዓለም ጤና ድርጅት /WHO/ አማካኝነት የቀረቡትን ሙያዊ ምክረ ሐሳቦች የየሀገራቱ መንግሥታት ተቀብለው በመተግበር ላይ መገኘታቸውን አውስተው፤ከዚህም ሳይንሳዊ ጥንቃቄ ጋር በማሰናሰል በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን የበላይ አካል ቅዱስ ሲኖዶስ የሚሰጡ ወቅታዊ መመሪያዎችን የማክብርና የማስከበር እንዲሁም የመፈጸም ግዴታ አለብን ካሉ በኋላ የበሽታው ስርጭት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሄዱን ያስቆመው አንዳች ምድራዊ ኃይል ስለሌለ አጀንዳውን ለሰማዩ አምላክ ለመስጠት እንገደዳለን፡፡ እርሱ ሁሉ ማድረግ የሚችል ኃያል አምላክ ነውና፡፡
ስለሆነም በሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት ሥር የሚተዳደሩት ሁሉም አድባራትና ገዳማት ይህንን መንፈሳዊ ጥሪና መመሪያ ሰምተው ምኅላን ከማድረግ፤ ሕዝበ ክርስቲያኑን ከማረጋጋት በተጨማሪ አድባራትና ገዳማቱ ባሉበት አካባቢ የጸሎተ ዕጣን ሥርዓት አድርገው አጥቢያቸውን ያጥኑ ዘንድ ይገባል በማለት ጠበቅ ያለ መመሪያ አስተላልፈዋል፡፡
በተያያዘ ዜናም የሰጡትን መግለጫ ወደ ተግባር በመቀየር በአዲስ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ሥር በሚገኘውና ወርኃዊ ክብረ በዓሉ በሚታሰብበት መካነ ሰማእት ቅዱስ ቂርቆስ ቤተ ክርስቲያን በዛሬው ዕለት ማለትም መጋቢት 15 ተገኝተው የጸሎተ ዕጣን ሥርዓቱን አስጀምረዋል፤ አባታዊ ቡራኬም ሰጥተዋል፡፡
መ/ር ሽፈራው እንደሻው የሀገረ ስብከቱ ዘጋቢ
Photo credit by Wasihun Teshome from AAD Media