የቦሌ ቅድስት አርሴማና ቅዱስ ገብርኤል ቤተ-ክርስቲያን የመሠረት ድንጋይ በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ተቀመጠ

በዕለቱ የመንበረ ፓትሪያርክ ጠቅላይ ስራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ያሬድ ብፁአን ሊቃነ ጳጳሳት የጠቅላይ ቤተክህነት የየመምሪያው ኃላፊዎች፤የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ክቡር መልአከ ሕይወት ቆሞስ አባ ኃይለ ገብርኤል ነጋሽ የሀገረ ስብከቱ የየዋና ክፍል ኃላፊዎች እና የቦሌ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስኪያጅ ንቡረ ዕድ አባ ዮሐንስ እንዲሁም የክፍለ ከተማው የስራ ኃላፊዎች የመንግሥት ተወካዮች ከአራቱም አቅጣጫ የመጡ የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች የአካባቢው ምዕመናን የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች የተገኙ ሲሆን ደማቅ ሥነ-ሥርዓትም ተከሂዷል፡፡

ይህ የመሠረት ድንጋይ የተጣለበት ቦታ ከአሁን በፊት በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በተወሰደ እርምጃ የሁለት ኦርቶዶክሳውያን ወንድሞች ሕይወት የጠፋበትና የበርካታ ክርስቲያኖችም አካል የጎደለበት እንዲሁም የብዙዎች ምእመናን ልብ የተሰበረበት ሆኖ ማለፉ የታወቀ ነው፡፡

በመርሐ ግብሩ ላይ መልእክት ያስተላለፉት የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ስራ አስኪያጅ እንደገለጹት የቦታው ባለቤት የሆኑትንና ለቤተ ክርስቲያን መሥሪያነት የሰጡትን አቶ ራይድ የተባሉ ግለሰብ ሲሆኑ በእምነታቸው ሙስሊም ከመሆናቸው በላይ በበጎነታቸው ሊመሰገኑ እንደሚገባ ገልጸው በቅድስት ቤተክርቲያን ስምም አመስግነዋል፡፡ ይህ ቦታ የበርካታ ወገኖች ደም ፈሶበታልና ለቤተ-ክርስቲያን መስሪያነት ይገባል በማለት ፈቃድ የሰጡትን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ክቡር ኢንጅነር ታከለ ኡማም ምስጋና ተችሯቸዋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ በዚሁ ቦታ ልጆቻቸውን ላጡ የሰማዕታት ቤተሰቦችም ቦሌ 24 በተባለ ቦታ ለሱቅ አገልግሎት የሚውል የ40/60 ኮንደሚንየም ቤት እንደሚሰጣቸው የከተማ አስተዳድሩ ተወካይ በቦታው ተገኝተው ቃል ገብተዋል፡፡

በመጨረሻም ቅዱስ ፓትርያርኩ ዓለምንና ሀገራችንን ኢትዮጵያን እያስጨነቀ ያለውን የኮረና ቫይረስ እግዚአብሔር እንዲያስታግስልን ከመጋቢት 6 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ እስከ በዓለ ትንሳኤ ድረስ ጸሎተ ምሕላ በሁሉም አድባራትና ገዳማት እንዲደረግ አባታዊ መመሪያ በመስጠትና በማወጅ መርሐ ግበሩ በጸሎት ተዘግቷል፡፡

መ/ር ደምሴ አየለ የሚድያ ክፍል ኃላፊ