ሰበር ዜና በ22 አካባቢ ለ2 ወጣቶች ሞት ምክንያት የሆነው ቦታ ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ተሰጠ
በአዲስ አበባ 22 አካባቢ በመንግሥት ታጣቂዎች ምእመናን በግፍ የተገደሉበትና በፈረሰው ቤተ ክርስቲያን ላይ አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ቤተ ክርስቲያን እንዲሰራበት ከአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ቤተ ክርስቲያን ፈቃድ ተሰጥቷል ።
ይህን ምክንያት በማድረግ በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ስራ አስኪያጅ በክቡር መልአከ ሕይወት ቆሞስ አባ ኃይለ ገብርኤል ነጋሽ የተመራ የሀገረ ስብከቱ አስተዳደር ጉባኤ በቦታው ላይ ተገኝቶ አካባቢውን ዞሮ ተመልክቷል።
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱማ ወእጬጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖትና የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ምክትል ከንቲባ ክቡር እንጂነር ታከለ ኡማ በቤተ ክርስቲያኒቱና በምእመናኑ ጥያቄ መሠረት ቦታው ለቤተ ክርስቲያኒቱ መንፈሳዊ አገልግሎት መስጫ እንዲሆን በማድረጋቸው ከፍ ያለ ምስጋና ይገባቸዋል ።እንዲሁም ቦታው ለቤተ ክርስቲያኒቱ እንዲሆን ከፍተኛ መስዋዕት ለከፈሉ የአካባቢው ወጣቶች፣ ምእመናንና ካህናት ምስጋና ይገበዋል ።
በወጣው መርሐ ግብር መሠረት በነገው ዕለት እሁድ መጋቢት 6/07/2012 ዓ.ም ከቀኑ 9:00 ሰዓት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጬጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፣ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ስራ አስኪያጅ ክቡር መልአከ ሕይወት ቆሞስ አባ ኃይለ ገብርኤል ነጋሽ፣ የሀገረ ስብከቱ አስተዳደር ጉባኤ አባላት ፣ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና የአዲስ አበባ ምእመናን በተገኙበት የመሠረት ድንጋይ ይቀመጣል ተብሎ ይጠበቃል።
በሀገር ስብከቱ አይቲና ዶክሜንቴሽን ክፍል