የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ፯ኛ ዓመት በዓለ ሢመት በደማቅ ሁኔታ ተከበረ

ዛሬ የካቲት 24 ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ፣ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነት የየመምሪያው ኃላፊዎች፣ የየድርጅቱ ኃላፊዎች፣ የመንፈሳዊ ኮሌጆች ኃላፊዎች፣ የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የየክፍሉ ኃላፊዎች፣ የአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች፣ ሊቃነ መናብርት፣ የሰንበት ትምህርት ቤት አባላትና  ምእመናን በተገኙበት የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ፯ኛ ዓመት በዓለ ሢመት በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ከቴድራል   በደማቅ ሁኔታ ተከብሯል።

ካህናቱ ‘‘አልቦ ዘየአብዮ ለማትያስ ወዘይሤንዮ ለላኅይከ፣ ወበእንተዝ አፍቀራከ አብያተ ክርስቲያናት’’ እያሉ በያሬዳዊ ዜማ በዓሉን አድምቀውታል ።

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖትም አነ ኃረይኩክሙ ወሤምኩክሙ- እኔ መርጬ ሾምኳችሁ (ዮሐ 17፡16) በሚል ተነስተው ሹመት በፍላጎትና በልምምድ የሚመጣ ወይም የሚገኝ ሳይሆን በእግዚአብሔር ፈቃድና ምርጨ የሚሰጥ ሀብተ ጸጋ ነው ሲሉ ምርጫና ሹመት የእግዚአብሔር ስጦታ መሆኑ፣ ፍጡራን በእግዚአብሔር ምርጫና ሿሚነት ብቻ የሚሾሙና የሚሻሩ መሆናቸውን አጽንኦት ሰጥተው አብራርተዋል።

ስለ ካህንና መመረጥ ጥቂት ካሉም በኋላ ‘‘አንድ የኃይማኖት አባት ራስን ከመካድ ጣራ ከደረሰ ተልእኮውን ከመፈጸም የሚገታው ኃይል በምድር ላይ ፈጽሞ አይኖርም። ምክንያቱም ለክርስቶስ ጽዋዔ መስቀል ሲባል በዚህ ዓለም ያለውን ሕይወቱንና ጥቅማ ጥቅሙን በሙሉ እንደ እድፍ ቆጥሮአልና’’ ብለዋል።

በመጨረሻም  በብፁአዓን ሊቃነ ጳጳሳትና በምሁራን የተዘጋጀ  የመሪ ዕቅድ ትግበራ እንዳለ ጠቁመው ይህንን ደግሞ በዚህ ዓመት ወደ ትግበራ የሚገባበት በመሆኑ ለቤተክርስቲያን አስተዳደር ትልቅ የምስራች መሆኑን አብስረው ሁሉም የቤተክርስቲየያን አባላት ለትግበራው ንቁ ተሳትፎና አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ አባታዊ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

 ከቅዱስነታቸው መልእክት እንደተረዳነው አንድ የኃይማኖት አባት ራስን ከመካድ ጣራ ከደረሰ ተልእኮውን ከመፈጸም የሚገታው ኃይል በምድር ላይ ፈጽሞ አይኖርም ብለዋል።  ምክንያቱ ሲጠቅሱም ለክርስቶስ ጽዋዔ መስቀል ሲባል በዚህ ዓለም ያለውን ሕይወቱንና ጥቅማ ጥቅሙን በሙሉ እንደ እድፍ ቆጥሮአልና የሚል ነበር። ይህ ሓሳብ በመጀመሪያ ለቤተክርስቲያን አባቶችና መሪዎች የተሰጠ አደራ እንደመሆኑ መጠን የዛሬ አባቶችም ይህንን አደራ ሊያስቀጥሉት ይገባል። ለመጀመሪያ አባቶች የተሰጠ ተልእኮ ዛሬ ላሉት ለቤተክርስቲያን መሪዎችና አባቶችም ይሠራል። ቤተ ክርስቲያን በየጊዜው የሚሻሻል ሌላ አዲስ መልእክት የላትምና። ይህንን ስንል የአሠራር ለውጥ አይኖርም ማለት አይደለም፣ ተልእኮው ግን ለቤተክርስቲያን መሥራችና ራስ ለሆነው ለክርስቶስ ራስን በማስገዛት ቤተክርስቲያንን በሚገባ ማገልገል ነው። የአግልግሎቱም ማእከል ዓለም ሁሉ በክርስቶስ አምኖ በቃሉ ጸንቶ እንዲኖር መትጋት ነው።   ቃሉም  ’’ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ’’ (ማር 16፡15) ይላልና። ስለዚህ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ለዚህ አገልግሎት በመፋጠን ያሏትን አማንያን በቃሉ በማጠንከር፣ ቃሉን ያልሰሙትን  ደግሞ ቃሉን በማሰማት ተልእኮዋን ሊያስፈጽሙ  ይገባል እንላለን።

ለብፁዕ ወቅዱስ  አባታችን መልካም በዓለ ሢመት ይሁንሎት ስንል መልካም ምኞታችንን እንገልጻለን።

                   መ/ር ኪደ ዜናዊ የሀ/ስብከቱ ዘጋቢ