የብፁዕ አቡነ መቃርዮስ ሐዋርያዊ ጉዞና የሱማሌ ጅግጅጋ አብያተ ክርስቲያናት ፈተናዎች

                      በመምህር ሣህሉ አድማሱ
የኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሆነው በቅዱስ ሲኖዶስ የተሾሙት ብፁዕ አቡነ መቃርዮስ ህዳር 7 ቀን 2011 ዓ.ም ከጅግጅጋ ከተማ 170 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በሚገኘው በደጋ ሀቡር ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡
ብፁዕነታቸው በአጽራረ ቤተክርስቲያን የእሳት ቃጠሎ የደረሰበትን የደጋ ሀቡር ቅዱስ ጊዮርጊስን ፅላት በተዘጋጀው መቃረቢያ ባርከው ያስገቡ ስለሆነ በማግሥቱ ህዳር 8 ቀን 2011 ዓ.ም የቅዳሴ ቤቱ በዓል በላቀ ድምቀት ተከብሯል፡፡
በዚሁ ደብር የቅዱስ ሚካኤል ፅላት በተደራቢነት ገብቶ ህዳር 12 ቀን 2011 ዓ.ም በዓሉ ተከብሯል፡፡
በጅግጅጋ መልእልተ አድባራት ደብረ መዊዕ ቅዱስ ሚካኤል ደብር ከሥርዓተ ቅዳሴው በኋላ በርካታ ምዕማንንና ካህናት በተገኙበት ለብፁዕነታቸው እጅግ የደመቀ አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡
በማግሥቱ ሰኞ ህዳር 10 ቀን 2011 ዓ.ም ከጅግጅጋ ከተማ በ70 ኪ.ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘውን የውጫሌ ቅድስት ሥላሴ ቤተክርስቲያን ጎብኝተዋል፡፡
ማክሰኞ ህዳር 11 ቀን 2011 ዓ.ም በጅግጅጋ ከተማ ዙሪያ የሚገኙትንና በአጽራረ ቤተክርስቲያን የእሳት ቃጠሎ የደረሰባቸውን የአቡነ ተክለሃይማኖትን፣ የቅድስት አርሴማን፣ የቅዱስ ጊዮርጊስንና የቅድስት ኪዳነ ምሕረትን አብያተ ክርስቲያናት ብፁዕነታቸው እየተዘዋወሩ ጎብኝተዋል፡፡
የእሳት ቃጠሎ የደረሰባቸው አብያተ ክርስቲያናት መልሰው በቅርብ ጊዜ እንደሚታነፁም ሊቀ ጳጳሱ አቡነ ማቃርዮስ በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ ምዕመናን የዕርዳታ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ብፁዕ አቡነ ማቃርዮስ ህዳር 12 ቀን 2011 ዓ.ም በጅግጅጋ መልእልተ አድባራት ደብረ መዊዕ ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያናት ለተሰበሰበው በርካታ ምእመናን አባታዊ የማጽናኛ ትምህርት ሰጥተዋል፡፡
በዚሁ ደብር በብፁዕነታቸው አስተባባሪነት ከብር 500,000 ሺህ ያላነሰ ገንዘብ ገቢ ተመዝግቧል፡፡
በአጽራረ ቤተክርስቲያን ካህን ባለቤቷ ለተገደለበት ለወ/ሮ አልማዝ (የሁለት ህፃናት እናት) ብር 30,000፣ የመደፈር ጥቃት ለደረሰባት አንዲት ታዳጊ ወጣት ብር 14,000 ብፁዕነታቸው አስተባብረው ከምዕመናን ዕርዳታ ተደርጎላቸዋል፡፡
በጅግጅጋ መልእልተ አድባራት ደብረ መዊዕ ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ግቢ ውስጥ በብፁዕነታቸው፣ በተለያዩ የወንጌል መምህራንና በሰባክያን አማካኝነት ከህዳር 7 እስከ ህዳር 12 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ የቆየ የስብከተ ወንጌልና የዝማሬ አገልግሎት ከተሰጠ በኋላ የብፁዕነታቸው ሐዋርያዊ አገልግሎት ተጠናቋል፡፡
ደከመኝን ሰለቸኝን የማያውቁት ታታሪው ሊቀጳጳስ ብፁዕ አቡነ መቃርዮስ በሱማሌ ጅግጅጋ ሀገረ ስብከት የአንድ ሳምንት የሐዋሪያዊ ጉዞ ቆይታቸው ጉዳት የደረሰባቸው ምዕመናን በጸሎት ያሰቧቸው ሲሆን በአማጽያኑ ቤታቸው ለፈረሰ እና ንብረታቸው ለተዘረፈ ምዕመናን ከክልሉ መንግሥት ባለስልጣናት ጋር በመነጋገር የካሳ ክፍያ እንደሚፈጸምላቸው ተናግረዋል፡፡
በዐዲስ አበባ ከተማ የሚሰበሰበው የእርዳታ ገንዘብም ጅግጅጋ ከተማ በሚከፈተው የዐቢይ ኮሚቴ አካውንት እንደሚገባ ብፁዕነታቸው በአፅንዖት ገልጸዋል፡፡
በተመሳሳይ ዜና የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በየገዳማቱና አድባራቱ ከሚሰበሰበው እርዳታ ውጭ ከአካውንቱ 4,000,000 ብር እርዳታ አድርጓል፡፡