አራቱ የሃይማኖት ተቋማት የሁለቱን ሲኖዶሶች እርቀ ሰላም አደነቁ

ሐምሌ 28 ቀን 2010 ዓ.ም በሚሊኒየም አዳራሽ በተካሄደው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሲኖዶሳዊ ዕርቀ ሰላም መርሐ ግብር ወቅት የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች ገንቢ የሆነ መልእክት አስተላፈዋል የእስልምናው መሪ መልእክት

የተከበረው ቅዱስ ቁርዓናችን የሰው ልጅ ክቡር ነው ይላል፤የሰው ልጅ ምንድን ነው? የሰውል ልጅ ከየት ነው የመጣ? የሰው ልጅ ለምንድን ነው የተፈጠረው? የሰው ልጅ ምን ሊሠራ ነው የተፈጠረው? የሰው ልጅ ምን ሊመለከት ነው የተፈጠረው? ምሁር፣ አባት፣ ወጣት፣   ባጠቃላይ የሰው ልጅ ምን ሊሠራ ነው የተፈጠረው? የሰው ልጅ የተፈጥሮ ውበት የተሰጠው ነው፤ የሰው ልጅ ሊወገዝ አይገባውም፤ የሰው ልጅ ሊሰደድ አይገባውም የሰው ልጅ በሰውነቱ ክቡር ፍጡር ነው፤ ፈጣሪ ለሰው ልጅ አንድትን አስቀምጦለታል፤ አንድነት ሀገራዊ ተግባር ነው፤ አንድነት ልማታዊ ተግባር ነው፤ አንድት ሃይማኖታዊ ተግባር ነው፤ አንድት አብሮ በመቀመጥ አይገኝም፤ አንድ ማለት ልባዊ አንድት ነው፤

የዛሬው ቀን የተቀደሰ ቀን ነው፤ የተራራቀው የተቀራረበበት፣ የተጣላው የታረቀበት ዘመን ነው፤ ዕርቁ አካላዊ ዕርቅ እነዳይሆን ልባዊ ዕርቅ መሆን አለበት፡፡

መረዳዳት፣ መተጋገዝ፣ መከባበር ካለ አንድታችን የጠነከረ ይሆናል፤ ለሰላም፣ ለአንድት እንሳተፍ፣ ለልማት እንዘጋጅ፣ መናቆር ይቅር፡፡

የካርድናሉ መልእክት

በዱር፣ በገደል ሲጸልዩልን የነበሩ ባሕታው ጸሎት ሰለተሰማ እንኳን ደስ አላችሁ፡፡

እግዚአብሔር ስለፈቀደ ነው ዕርቀ ሰላሙን ያወረደልን፤ ዕርቅ የእግዚአብሔር ነው፤ አንድነትን የሰጠ እግዚአብሔር ነው፤ በዚህች በምንወዳት ሀገራችን በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በሰማይ ቤት በመንግሥተ ሰማያት ደስታ ይሆናል፤ መላእክት ይደሰታሉ፤ ቅዱሳን ይደሰታሉ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ትደሰታለች፣ የማይደሰተው የክፋትና የጥላቻ ምንጭ የሆነው ዲያብሎስ ብቻ ነው፤ የዚህች የቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን በዚህች በሀገራችን በኢትዮጵያ፣ በውጭ ሀገርም ያላችሁ ለማስታረቅ ብዙ የለፉት ሽማግሌዎች በተለይም ጠቅላይ ሚንስትራችን የሰላም መሣሪያ በመሆን ይህንን ዕርቀ ሰላም ስለመሠረቱልን በቤተ ክርስቲናችን ስም ላመሰግን እወዳለሁ፡፡

እኔ ከዚህ የተማርኩት እኛ ኢትዮጵያውያን ስንጣላ ለመታረቅ ሌላ ሦስተኛ ወገን አያስፈልገንም፤ ዕርቀ ሰላሙ የተፈጸመው ሌላ ሦስተኛ አካል ገብቶ ሳይሆን ርዕስ በርሳችን በጸሎት፣ በፍቅር ኃይል ያደረግነው ስለሆነ እኛ ኢትዮጵያን ለመታረቅ፣ ለሰላም ቅርብ መሆናችንን ያሳያል፤ አሁንም ሰላም በሌለበት አካባቢ፣ ጥላቻ ባለበት አካባቢ በእኛው ጸሎት ዕርቀ  ሰላም፣ በእኛው ጥረት ይህችን የምንወዳትን ኢትዮጵያውን ሰላም ፈጣሪ እንዲያደርግልን መጣር አለብን፡፡

የወንጌላውያን ኅበረት መሪ መልእክት

“ዛሬ እግዚአብሔር ታላቅ ነገር አደረገልን ደስም አለን”

ቃሉን የተናገረው መዝሙረኛው ዳዊት ነው፤ ይህ ደስታ የእናንተ ብቻ አይደለም፤ የሁላችንም ደስታ ነው፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በማናችንም ሕይወት ውስጥ ትልቅ ሥፍራ አላት፤ ከ2000 ዓመት በላይ የቆየው ታሪካችን ኢትዮጵያን የገጠማት ፈተና ሁሉ ኢትዮጵያን የሚጣሉት እጃቸውን በኢትዮጵያ ላይ ሲያሳርፉ እግዚአብሔር ሀገራችንን እና ይህችን ቤተ ክርስቲያን ጠብቆ ለዚህ ሰዓት አድርሷታል፡፡

ዛሬ ከልብ የመነጨ ሽንገላ የሌለበት ደስታ በራሴ ስም እና በኢትዮጵያው ወንጌላውያን አማኞች ኅበረት ስም አቀርብላችኋለሁ፤

ሁላችንም ለዚህች ሀገር ሰላም፣ አንድት፣ ፍቅር በጋራ መሥራት አለብን፤ እግዚአብሔር ፊቱን ወደ እኛ እንዲመልስ ሀገራችን በብሔር፣ ሀገራችን በሃይማኖት፣ በተለየ ነገር ተከፋፍላ እርስ በርስ የምንጠላላ፣ የምንበላላ ሳይሆን በአንድነት ለዚህች ሀገር ክብርና ልዕልና የምንቆም የእግዚአብሔር ልጆች ልንሆን ይገባናል፡፡

አንድነት ኃይል ነው፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሁላችንም ታሪክ ናት፤ ወደድንም ጠላንም የኢትዮጵያ ታሪክ የኢትዮጵያ ኦርቶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ነው፤ እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ይባርክ፡፡

የሙሉ ወንጌል መሪ መልእክት

አስቀድሜ ለእግዚአብሔር አብ፣ ለእግዚአብሔር ወልድ፣ ለእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ምስጋና አቀርባለሁ፡፡

በጾታ፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖት ሳንለያይ ተከባብረን፣ ተቀባብለን፣ በአንድት እንደ ዜጎች ለአንዲት ኢትዮጵያ ልማትና ለአንድነት በፍቅር፣ በሰላም፣ ተሳስበን ለምንሰለፍበት ዘመን እንኳን አደረሰን፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንከ ከጥንት ጀምሮ አንድነቷን ጠብቃ፣ ሃይማኖቷን ጠብቃ እውነተኛውን ወንጌል በማስተማር የሁላችንም እናትናት፡፡

ጌታችን፣ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እርስ በርሳችሁ ፍቅር ካላችሁ ደቀ መዛሙርቴ መሆናችሁን (ሰዎች ሁሉ) ዓለም ያውቃል ብሏል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንም በዚህ ቃል በጣም ታላቅ ስለሆነች በጣም ተደስቻለሁ፡፡ የተወደዱና የተከበሩ ጠቅላይ ሚነኒስትራችን ይቅርታን፣ ፍቅርን፣ መከባበርን፣ መደመርን፣ እየሰበኩ ሁላችንም ተከባብረን እንድንኖር፣ አንድናድግ፣ ከልብ ለሚገኙት ራዕያቸው ለዚህች የተከበረች ጥንታዊ፣ ታላቅ ቤተ ክርስቲያን ከልባቸው በማሰብ፣ በተፈጠረው አለመግባበትና ክፍተት  የፈጠረውን መራራቅ ለማቅረብ ስላደረጉት አስተዋፅኦ በከፍተኛ አክብት ምስጋናችንን እናቀርባለን፡፡

ከእንግዲህ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከትንት ጀምሮ ሞዴል ቤተ ክርስቲያን እንደመሆንዋ መጠን ይህንን ፍቅርና ባህላዊነት በመካከላችሁ የተፈጠረውን ለዘለቄታው እግዚአብሔር ጠብቆ ምድሪቱን በበረከት እንዲሞላት ይህን ልባዊ ፍቅርና ደስታ እግዚብሔር ያስጥልልን፡፡ ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር፤ ክብር ለእግዚአብሔር ለአምላካችን ይሁን፡፡

የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት መልእክት

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አባቶች መካከል ከ27 ዓመታት በላይ የዘለቀው መለያየት በፍቅር፣ በዕርቅ ተፈትቶ አንድነት በሚበሠርበት መርሐ ግብር ላይ መገኘት በመቻሌ በኢትዮጵያ ፌደራላዊ መንግሥት ስም የተሰማኝን ደስታ ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡

የሃይማኖት ተቋማት ዕርቁ የተሣካ እንዲሆን፣ ሰላም እና ልማት በሀገራችን እንዲረገጥ፣ የሀገራችን ታሪክና ቅርስ እንዲጠበቅ ያደረጉት አስተዋጽኦ እጅግ ከፍተኛ ነው፤ ይህንን አስተዋጽኦ ዘመኑ እና ትውልዱ በሚጠይቀው መንገድ እንዲሠራ የሃይማኖት ተቋማት ጠንካራና አንድት የጠበቀ ተቋማት ሆኖ መገኘት አለበት፡፡

መከፋፈልና መለያየት የእምነት ተቋማቱ ለሚያገለግሉት ሕዝብና የተጠናከረ የሃይማኖት ተቋማት ሳይኖር ጠንካራ ኢትዮጵያን ለመገንባት ደግሞ እጅግ አስቸጋሪ ነው፤ የማይታሰብም ነው፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥነ ጽሑፍና ሥነ ዜማ፣ ሥነ ስዕል በማበልጸግና በመጠበቅ ያበረከተችው ሚና የተመሰከረ ነው፤ ሕዝቦች መካከል የጸና ኅብረት ለሀገሪቱ ነፃነት ለ1000 ዘመናት ተጠብቆ እንዲዘልቅ ሀገራችንን ለመውረር የመጡትን ቅኝ ገዢዎች  በሐላፊነት ስሜት እንዲከላከል በሚደረግበት ወቅት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሚና ተጫውታለች፤ እነ አቡነ ጴጥሮስና አቡነ ሚካኤል ለነፃነታችን የከፈሉትን መስዋዕትነት መቼም አንዘነጋውም፡፡

የአፍሪካ ሕዝቦች በቅኝ ግዛት ሥር በወደቁበት ጊዜ ቤተ ክርስቲያንም ለነፃነት አርማችን ቆማለች፤ አፍሪካውያን መስዋዕት የሚከፍሉበት ተቋማት በማቋቋም የጥቁር ሕዝቦች ታለቅታቸው መገለጫ አድርገዋታል፡፡

በኢየሩሳሌም የክርስቶስ የመቃብር ቅዱስ ቦታ በአውሮፓውያ ብቻ የተያዘ እንዳይሆን የጥቁሮች ወኪል በመሆን ርሥት ያተረፈችው ይህችው ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡

የነቢዩ መሐመድ ተከታዮች በመከራ ወደ ሀበሻ  እንዲገቡ በነቢዩ በተነገራቸው  መሠረት ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ከሕዝቡ ጋር በመሆን የተቀበሏቸውና ያስተናገዷቸው፣ ጠላቶቻቸው ሲጠየቁ ኢትዮጵያውያን ከእነርሱ ጋር ተባብረው ከሀገራችን አሳልፈን አንሰጥም በማለት የዚህች ቤተ ክርስቲያን ደጋፊ እንደነበሩ ታሪክ ይነግረናል፤ ይህም በኢትዮጵያ ክርስቲያን እና ሙስሊሞች መካከል ያለው ሊፈታ የማይችል የተሣሰረው ወንድማማችነት ዘመናትን የዘለቀ መሆኑ የሚታወቅ ነው፤ ይህ ዘመናትን የዘለቀ ወንድማማችነት ነፋስ በነፈሰ ቁጥር  የሚበጠስ አይደለም፤

ይህች ታላቅ ቤተ ክርስቲያን ስትከፋፈልና ስትዳከም ሁላችንንም ያሳዝነናል፤ የቤተ ክርስቲያኒቱ መጠናከር ደግሞ ለሁሉም ዜጎች ጠቃሚ ነው፤ ለዚህ ነው ባለፉት ዓመታት መለያየት ሲከሰት ብዙዎች ሲያዝኑ የነበረው፤ መከፋፈሉ ተወግዶ አንድነቱ ሲፀና ብዙዎቻችን ዕኩል የተደሰትነው ለዚህ ነው፤ እያንዳንዳችን ጠንካራ መሆን አለብን፤ ባንዳችን ላይ የሚደርሰው ችግርና መከራ በሁላችንም ላይ እንደደረሰ የሚቆጠር ነውና፤ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን አባቶች ችግራቸውን ፈትተው ሰላም ማምጣታቸው ጥቅሙ ብዙ ነው፤ ባንድ በኩል የራሳቸውን ችግር መፍታታቸው የተረጋገጠ ነው፤ ይህም እኛ ኢትዮጵያውያን የራሳችንን ችግር ራሳችን መፍታት እንደምንችል ማሰያ ነው፤ በሌላ በኩል ለሁለት አሥርት ዓመታት  የቆየ ችግር በሰዓታት ብቻ መፍታት ቀናነትና ፍላጎት ካለ የማይፈታ ችግር አለመኖሩን ያሳያል፤

ከዚህ በተጨማሪ የችግሩ አካል መሆናችንን አውቀን የመፍትሔው አካል መሆን ስንመኝ እንደተራራ ገዝፎ የነበረው ችግርን መፍታት እደምንችል አሳይቶናል፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እና ሌሎችም የእምነት ተቋማት በውስጣቸው የተፈጠሩ ችግሮችን እየፈቱ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ከውስጣቸው በማስወገድ ለሌሎቻችን እንዲተርፉ እየጠበቅናቸው ነው፤ የሀገራችን ችግሮች ባፋጣኝ ፈትተን የላቀች፣ የበለፀገችና የሰለጠነች ኢትዮጵያን ለመገንባት እንድንችል በዕውቀት የረቀቀ፣ በሥነ ምግባር ያደገ፣ በሀገር ፍቅር ስሜት የሚሠራና በማንነቱ የሚኮራ ትውልድ ማፍራት ይኖርብናል፡፡

ለዚህም ደግሞ ዋናውን ሥራ መሥራት ያለባቸው የሃይማኖት ተቋማት ናቸው፤ አንድ ሆነው ለፍትሕ መከበር የሚቆሙ፤ አንድ ሆነው ለዜጎች መብት መከበር የሚሠሩ፣ አንድ ሆነው ከተበደሉት ጋር የሚቆሙ አንድ ሆነወ ለልማት የሚሰለፉ፣ አንድ ሆነው የስልጣኔ ብርሃን የሚያበሩ አባቶች ያስፈልጉናል፡፡

ሀገራችን በሰው ሠራሽም ሆነ በተፈጥሮ የጋራ ትግል በደረሰ ቁጥር ሌሎችን መለመን አንድናቆም የሃይሞት ተቋማት ጠንካራ የጋራ ተቋማት በመመሥረት መስተማር ይኖርባቸዋል፤ ከ98 ከመቶ በላይ ኢትዮጵያውያን ሃይማኖተኞች መሆናቸውን የተለያዩ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ 98 ከመቶ የሆነውን የሀገራችንን ኃይል ማንቀሳቀስ የሚችሉት ደግሞ የሃይማኖት ተቋማት ናቸው፡፡ ታዲያ ይህንን ኃብት ማንቀሳቀስ እየቻልን ለምንድን ነው እጃችንን ወደ ውጭ የምንዘረጋው? የእምነት ተቋማት እራሳቸውን ጠንካራ ተቋም አድርገው፣ ጠንካራ የሥራ ስልት መመሥረት ይኖርባቸዋል፤ ደረጃቸውን የጠበቁ ትምህርት ቤቶችን፣ የጤና ተቋማትን፣ የአረጋውያን መጦሪያ ማዕከላትን፣ የሕጻናት ማሳደጊያዎችን፣ የስደተኞች መጠለያዎችን፣ እናንተ የሃይማኖት ተቋማት ካልገነባችሁ ሥራውን ለማን ነው የምንሰጠው? የራሱን ችግር በሰለጠነም ንግድ መፍታት የሚችል ተቋም መመሥረት የማይችል ውጫዊ ችግር የለም፤ በየአካባቢው የሚከሠቱ ችግሮችን መፍታት፣ በሕዝቦች መካከል በመከባበርና በመተማመን ላይ የተመሠረተ አንድነት እንጂ መሠረት በማድረግ ሕዝቡን የሚመግቡ ተቋማትን በመመሥረት ከእናንተ የሚሻል የለም፤ በተለይም ደግሞ ሀገር ተረካቢ ትውልድ በአደንዛዥና በሱስ እንዳይጠመድ በማይጠቅም መጤ ባህል እንዳይወስድ በብልሹነትና በዋልጌነት እንዳይጠቃ ከእናንተ የተሻለ ሊያስተምረው፣ ሊመክረውና ሊያቆመው የሚችል ማንም የለም፤ ባጠቃላይ በዚህ የራሳችን በዓል ላይ የምናስበው ብዙ ነውለ ያንዱ ተስፋ ለሌላው ተስፋ፣ አንዱ ዕድል ለሌላው ዕድል ያመቻቻል፤ ያገኘነውን ይዘን ያላገኘነውን ለማግኘት መትጋት ይኖርብናል፤ ሴቶቻችን ከፈተናዎቻችን የላቁ ናቸው፡፡

በጨለማው ላይ ከምንቆዝም በብርሃኑ እንሥራ፤ በችገሮቻችን ላይ ከምናማርር በፀጋዎቻችንና በድሎቻችን ላይ እንረባረብ ጥቁር በፈተናዎቻችን ከምናዝን ይልቅ በዕሴቶቻችን ለመጠቀም እንትጋ፤ ሁላችንም የምንችለውን ድርሻችንን እንወጣ፤ ሁላችንም በዕኩልነት፣ በነፃነትና በፍቅር የምንኖርባት ኢትዮጵያውን እንገንባት፤ አሁንም በድጋሚ እንኳን ለዚህ አንድነትን መልሰን ላጸናንበት በዓላችን ሁላችንንም አደረሰን እላለሁ፡፡