የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መ/ር ይቅርባይ እንዳለ በርካታ ባለጉዳዮችን ተቀብለው አስተናገዱ
በመ/ር ኪዱ ዜናዊ እና በመ/ር ወንድምአገኝ ደጀኔ
ሐምሌ 11 ቀን 2010 ዓ.ም የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መ/ር ይቅርባይ እንዳለ በሀገረ ስብከቱ ሥር የሚገኙትን ባለጉዳዮችን በተለይም በቀጠሯቸው መሠረት የተገኙትን ባለጉዳዮች ሲያስተናግዱ ውለዋል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ወደ ሀገረ ስብከቱ የመጡት ባለጉዳዩች በሁለት መልኩ የሚታዩ ሲሆን በጋራ ሆነው የቤተ ክርስቲያንን ጉዳይ ይዘው የመጡና በግል ጉዳይ የመጡ ይገኙበታል፡፡ ዋና ሥራ አስኪያጁ በመጀመሪያ በጋራ ስለ ቤተክርስቲያን ጉዳይ የመጡትን ባለጉዳዮች በቅድሚያ ያስተናገዱ ሲሆን በመቀጠልም በቀጠሮ በግል ጉዳይ የመጡትን በሚገባ አስተናግደዋል፡፡ ያለ ቀጠሮ የመጡትን ደግሞ ሐሳባውን ከተቀበሉ በኋላ ለሌላ ቀን ቀጠሮ በማስያዝ ሸኝተዋቸዋል፡፡ የቤተ ክርስቲያንን ጉዳይ ይዘው ወደ ሀገረ ስብከቱ ከመጡት ባለጉዳዮች ከተሰነዘሩት ሐሳቦች መካከል የመልካም አስተዳደር እጦት፣ ያለመግባባት ችግር፣ ያለመናበብ ጉዳይ ያለጨረታ የሚከራዩ የቤ/ክ ይዞታዎች፣ የቤተክርስቲያንን ይዞታ አስጠብቆ አለማኖር የአገልጋዮች መበደል፣ የቤተክርስቲያን ሱቆች ያለአግባብ ማከራየት ወዘተ የሚሉት ይገኛሉ፡፡
እንዲሁም በግል ጉዳይ ከመጡት ባለጉዳዮች መካከል የደሞዝና አበል አለመከፈል፤ በግል መበደል፣ የደሞዝ ጭማሪ አለማግኘት፣ ያለ አግባብ መታገድ፣ የሚሉት ይገኙበታል፡፡ ዋና ሥራ አስኪያጁም ሁሉም ባለጉዳዮች በአግባቡ ካስተናገዱ በኋላ በሰጡት ማብራሪያ እያንዳንዱ ችግር በጊዜውና በወቅቱ እንደሚፈታ ገልጸው አንዳንድ ችግሮች ደግሞ ጥናት የሚያስፈልጋቸው በመሆኑ በመረጃና በማስረጃ አስደግፈው መፍትሔ እንደሚሰጣቸው አሳስበዋል፡፡ ዋና ሥራ አስኪያጁ እንደገለጹት አሁን ሀገረ ስብከቱ አጣሪ ኮሚቴዎች አጣርተው ከጨረሱ በኋላ በዋነኝነት የታገዱትን የሚመደቡ ሲሆን በመቀጠልም ዝውውርን፣ ሽግሽግን፣ አዲስ ቅጥርን በተመለከተ አሁን ሳይሆን በሚቀጥለው አዲስ ዓመት እንደሚጀመር ገልጸዋል፡፡