ብፁዕ ዶክተር አቡነ አረጋዊ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የቅዱስ ፓትርያርኩ ረዳት ጳጳስ ሆነው በመመደባቸው ደማቅ አቀባበል ተደረገላቸው

                                                                                    በመ/ር ሣህሉ አድማሱ

ብፁዕ ዶ/ር አቡነ አረጋዊ በሀገረ ስብከቱ አዳራሽ ተገኝተው ንግግር ሲያደርጉ

ከብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤት ለብፁዕ ዶክተር አቡነ አረጋዊ የመንበረ ፓትርያርክ ውጭ ጉዳይ የበላይ ሓላፊ ባአድራሻቸው በተጻፈላቸው የሹመት ደብዳቤ እንደተገለጸው ቅዱስ ሲኖዶስ በወሰነው መሠረት ብፁዕነታቸው ከሐምሌ ወርህ 2010ዓ/ም ጀምሮ እስከ ጥቅምት ወርህ 2011 ዓ/ም ድረስ ሀገረ ስብከቱን በጊዜአዊነት ረዳት ጳጳስ ሆነው ይመራሉ፡፡ በአቀባበል ሥርዓቱ ወቅት የእንኳን ደስ አለን መልእክት ያስተላለፉት የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ መምህር ይቅርባይ እንዳለ እንዳብራሩት የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትን በሚመለከት ጉዳይ አጣሪዎች ተመድበው እስከ አሁን እያጣሩ ነው ያሉት፤በሀገረ ስበከቱ ጉዳይ ቤተ ክርስቲያንዋ ከፍተኛ ተጽዕኖ ሥር ከመውደቋም በላይ በተለያዩ ስብሰባዎች ስሟ በክፉ ሲነሣ ስለነበር ቅዱስ ፓትርያርኩ ይህን ተገንዝበው መመሪያ ሰጥተውበት እኛን ዋና ሥራአስኪያጅና ምክትል ሥራአስኪያጅ አድርገው ልከውናል፡፡መዋቅሩ ተሟልቶ ሥራ እንድንጀምር ረዳት ጳጳስ አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበት ብፁዕ ዶክተር አቡነ አረጋዊ ዘመናዊ የአስተዳደር ሲስተም ከመንፈሳዊ ሲስተም ጋራ አቀናጅተው ይሠራሉ ተብሎ የታመነባቸውና በብዙ ቦታዎች ላይ ውጤታማ የሆኑ ሥራዎች እየሠሩ እስከአሁን የደረሱ አባት ስለሆኑ እዚህ በመመደባቸው የሀገረ ስብከቱን ጽ/ቤትንና የአዲስ አበባ ሊቃነ መናብርትን ወክዬ እንኳን ደህና መጡ ለማለት እወዳለሁ፡፡

በመቀጠልም የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዘርፈ ብዙ ችግሮችን ያዘለ ስለሆነ ይህንን አሠራር ከሥር ጀምሮ ቀርፎ ጥሩ ውጤት ላይ ለማድርስ ከቅዱስ ፓትርያርኩ መመሪያ እየተቀበልን ከብፁዕ ዶክተር አቡነ አረጋዊ ጋር አብረን እየታዘዝን በቃለ ዓዋዲው ላይ ተጽፎ እንደሚገኘው መቅጠር ፣ማዛወር ፣የደመወዝ ማሻሻያ መስጠት ፣ዕድገት መስጠት ክልክል ነው ያለውን በሙሉ ግዴታ ጠብቀን የምንቀበል መሆኑን ቃል እንገባለን፡፡አድባራትና ገዳማት ደመወዝ መጠየቅ መብታቸው ሆኖ እያለ ደመወዝ ሲጠይቁ በመኸል የሚገቡ ደላሎች መኸል ገብተው ያንድ ወር ፣የሁለት ወር ደመወዝ ጭማሪ ልቀቁ እየተባሉ መከራቸውን ሲያዩ የነበሩትን ካህናትና ዲያቆናት ከዚህ ችግር የምናላቅቀው ጉዳዩን ለረዳት ጳጳሱ እና ለቅዱስ ፓትርያርኩ በማቅረብ ከምንፈታው በስተቀር ወደ ፖሊስና ወደፍርድ ቤት መሄድ አይጠበቅብንም ብለዋል፡፡

ብፁዕነታቸውን ለመቀበል በሀገረ ስብከቱ አዳራሽ የተገኙ የሀገረ ስብከቱ ገዳማትና አድባራት ሠራተኞች

የቅዱስ ፓትርያርኩ ረዳት ጳጳስ የሆኑት ብፁዕ ዶክተር አቡነ አረጋዊ አያይዘው በስተላለፉት ትምህርታዊ መልእክት ሀገራችን ኢትዮጵያ ከሕገ ልቡና ጀምሮ እስከሙሴ ሕግ ፣ከጊዜም በኋላ ዐዲስ ኪዳንን በመቀበል በመማርና በማስተማር ስመ እግዚአብሔርን ስትጠራ የቆየች መሆንዋን ጠቅሰው የመልካም አስተዳደር ጥያቄ የወቅቱ ዐቢይ ጉዳይ ነው፡፡የማንኛውም ማኅበረሰብ መብት የሚጠበቀው ፍትሐዊነትን ፣እኩልነትን ማስፈን ሲቻል ነው፡፡ይህንን ማድረግ የሚቻለው በቤተ ክርስቲያን የመልካም አስተዳደርን መርሆ ማስረጽ ሲቻል ነው፡፡ካህናትንና ምዕመናንን በዕኩል ዐይን ማየት እና የአሠራር ሲስተም መዘርጋት እንደሚገባ በማውሳት ሰፋ ያለ ትምህርታዊ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡

በመጨረሻም ቅዱስነታቸው በሰጡት ማብራሪያ እኛ ራሳችንን ከተቆጣጠርን ችግር ሊገጥመን አይችልም፡፡የሚከሰንና የሚወቅሰን ሊኖር አይችልም፡፡ረዳት የማይፈልግ የለም፡፡ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ለተወሰኑ ዓመታት ረዳት ጳጳስ ሳይሰየም ቆይቷል፡፡እሱም ሆን ብሎ የተደረገ ሳይሆን አንድ አንድ ችግሮችና አጋጣሚዎች ስለከለከሉን ነው፡፡ምንጊዜም ቢሆን ረዳት ያስፈልጋል ፡፡መጽሐፉም ለእመ ወድቀ አሐዱ ያነሥኦ ካልኡ ነው የሚለው በማለት ቅዱስነታቸው መልእክታቸውን አስተላልፈው ስብሰባውን በጸሎት አጠናቀዋል፡፡

 

የብፁዕ ዶ/ር አቡነ አረጋዊ  የመንበረ ፓትርያርክ የውጭ ጉዳይ የበላይ ሐላፊና በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ረዳት ጳጳስ የትምህርትና የአገልግሎት ታሪክ

ትምህርት

  •  ፊደል፤ ንባብ፤ ዲዊትና ቅዲሴ ከመርጌታ ሙሴ ብፅአ ጊዮርጊስ ተምረዋል።
  • ቅኔ፥ ከግጨው መንክር ምንዝሮ ተክለ ሃይማኖት ፤ ሐዲሳት፤ ከመጋቤ ሐዲስ ወልደ ሰንበት ግምጃ ቤት ማርያም ተምረዋል።
  • 1ኛና 2ኛ ከፍተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በአፄ ፋሲል፤ መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ደግሞ በዳግማይ ደብረ ሊባኖስ አዘዞ ሃይማኖት ት/ቤቶች ተምረዋል።
  • ከሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ በቲኦልጂ ዱፕልማ፥
  • ከቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ በቲኦለጂ ዱግሪ፤ከኖርዌይ ስታሻንገር ስፔሻሊይዝድ ዪኒቨርስቲ የማስተርስ ዱግሪ፥ከፕሪቶርያ ዩኒቨርስቲ በፍሌስፍና የፒኤችዲ ድግሪ አግኝተዋል።

ቋንቋ

  • ከእንግሊዚኛ በተጨማሪ የኖርዌይ፤ የስዊዴንና የዳንማርክ ቋንቋዎችን ይናገራሉ።

ገ  ክህነት

  • ዲቁና በ1968 ዓ.ም. ከብፁዕ አቡነ እንዴርያስ (ቀዲማዊ) በወቅቱ የሰሜን ጎንደር ሊቀ ጳጳስ ተቀብለዋል፥
  • ምንኵስና በ1984 ዓ.ም. በታዋቂውና ጥንታዊው ገዳም ጎንድ ተክለ ሃይማኖት ተቀብለዋል፥
  • ቅስና ከብፁዕ አቡነ ያዕቆብ (ኤርትራዊ) በወቅቱ የሰሜን ጎንደር ሊቀ ጳጳስ ተቀበለዋል፥
  • ቁምስና ከብፁዕ አቡነ ገብርኤል በወቅቱ የምዕራብ ሸዋ ሊቀ ጳጳስ ተቀብለዋል።

  • በሆለታ ደብረ ገነት ቅድስት ኪዳነ ምሕረት፤ በሆለታ ገነት ደብረ ኤዶም ቅዱስ ገብርኤል ፤ በሆለታ ገነት ደብረ ሣህል መድኃኔ ዓለም፤ በወሊሶ ጻድቁ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ አብያተ ክርስቲያናት በአስተዳዳሪነት ሠርተዋል።
  • የወልመራ ወረዳ ቤተ ክህነት ምክትል ሊቀ ካህናት ሆነው በቅንንነት አገልግለዋል።
  • በኖርዌይ ስታሻንገር መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪና የሕፃናትና ቤተሰብ መምሪያ የቦርድ ምክትል ሰብሳቢ በመሆን መርተዋል።
  • የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅደስ ማኅበር የቦርድ አባል፤ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት የቦርድ አባል በመሆን አገልግለዋል፡፡
  • በቤተ ክህነት ጠቅሊይ ጽ/ ቤት በስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ሐሊፊ፤
  • በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ በመጀመሪያ የሪሰርችና ምርምር ሐላፊና አካዲሚክ ዲን፤ ም/ ዋና ዲን በመሆን አገልግሎት ሰጥተዋል።
  • የቅድስት ልደታ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ የቦርድ አባል በመሆንም ሠርተዋል።
  • በዓለም አቀፍ ተሳትፎ ደግሞ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕድ ቤተ ክርስቲያንን በመወከል የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ማእከላዊ ኮሚቴ አባል፤ የመላው ኦርየንታል ኦርቶዶስ አብያተ ክርስቲያናትን በመወከል የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል በመሆን ሠርተዋል።
  • የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ምክትል ሥራ አስኪያጅ ሆነው በቅንነት አገልግለዋል፡፡

ንጭ፡የተሿሚ ጳጳሳት አጭር የሔይወት ታሪክ ሐምሌ 2009 ዓ.ም በትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ድርጅት የታተመ

የዝግጅት ክፍላችንም ለዶክተር ብፁዕ አቡነ አረጋዊ መልካም የሥራ ዘመን እንዲሆንላቸው ይመኝላቸዋል፡፡የብፁዕነታቸው ቡራኬ አይለየን፡፡