የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ/ የኢትዮጵያና የሩሲያን ግንኙት ለማጠናከር እንደምትሰራ ገለፀች
በኢትዮጵያና ሩሲያ መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር እንደምትሰራ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ገለፀች።
ብፁዕ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘ ኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘ አክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለኃይማኖት በሩሲያ ያደረጉትን ጉብኝት አጠናቀው ተመልሰዋል።
ፓትርያርኩ በጉብኝታቸው ከመላው ሩሲያ ቅዱስ ፓትርያርክ ክሪል ጋር ተወያይተዋል።
በዚህ ወቅትም ቅዱስ ክሪል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በአባቶችና በእናቶች ጥንካሬ ተጠብቃ ለዓለም ዓርአያ ሆና የምትጠቀስ መሆኗን ገልፀዋል።
በቅዱስነታቸው የተመራው የልዑካን ቡድን ወደ ሩሲያ ማቅናቱ ቀድሞ ለነበረው ጠንካራ ግንኙነት ጉልበት እንደሚሆንም አንስተዋል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በበኩላቸው፥ በሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት መካከል የነበረው የሁለትዮሽ ግንኙነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል የተለያዩ ስልጠናዎች እንዲመቻቹ ጠይቀዋል።
ፓትርያርኩ በጉብኝታቸው ከሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ጋርም ውይይት አድርገዋል።
ቅዱስነታቸው ቤተክርስቲያኗ እየተቀዛቀዘ የመጣውን የሁለቱን ሃገራት ግንኙነት ዳግም ለማጠናከር እየሰራች መሆኗን ጠቁመዋል።
የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ በበኩላቸው፥ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርቲያን ጥንታዊና ታሪካዊ መሆኗን ጠቅሰው ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር የረጅም ጊዜ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንደነበራቸው ተናግረዋል።
ግንኙነቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ልዩ ልዩ ስልጠናዎች ይዘጋጃሉ ብለዋል።
በማህበራዊ ዘርፍ ልማት በጋራ ለመስራትና የተቋረጠውን የትምህርት ዕድል መቀጠል በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መምከራቸውን የተለያዩ ዘገባዎች ያመላክታሉ።