“ዳግም ምጽአት”
ከሊቀ ብርሃናት ኢሳይያስ ወንድምአገኘሁ
ዳግም ምጽአት የሚለው ምንባበ ቃል በብዙዎች ዘንድ ግልጥና የሚታወቅ መስሎ ቢታይም ቋንቋው ግእዝ እንደመሆኑ መጠን ወደ አማርኛ መተርጎምና መብራራት ስለአለበት ወደ ሐተታውና ጥልቀት ወዳለው ምሥጢሩ ከመግባታችን በፊት ትልቁም ትንሹም የተማረውና ያልተማረውም ሁሉም በግልጥ እንዲረዳው የምሥጢሩ ቋጠሮና ውል ያለውም በዚሁ በርእሱ ላይ ስለሆነ ርእሱን ወደ አማርኛ መተርጎም አስፈላጊና ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው፡፡ በዚህም መሠረት “ዳግም ምጽአት” ማለት የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግመኛ ወደዚህ ዓለም መምጣት ማለት ነው፡፡
በዚህ ዐቢይ ጾም ውስጥ ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው ያሉት ሳምንታት ሁሉም የየራሳቸው ታሪክና ሰፊ ትምህርት እንደአላቸው ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ በዚህ አጭር ጽሑፍ መግለጥ የፈለግነው በጾሙ መካከል ደብረ ዘይት በመባል ስለሚታወቀው ዕለተ ሰንበትና ሳምንት ስለሆነ በውስጡም ታላቅ ምሥጢር ያለው በመሆኑ ስለእሱ በመጠኑ ማብራራት እንሞክራለን፡፡
በመሠረቱ “ደብረ ዘይት” ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለዳግም ምጽአቱ ያስተማረበትና ምሥጢረ ትንሣኤ ሙታንን የገለጠበት ተራራ (ኮረብታ) ነው፡፡ “በስመ ሐዳሪ ይጼዋዕ ማኅደር” (ቤት በባለቤቱ ስም ይጠራል) እንዲሉ ብርሃነ መለኮቱን በገለጠበት ተራራ ስም “ደብረ ታቦር” ተብሎ የጌታችን በዓል እንደሚከበር ሁሉ ስለ ዳግም ምጽአቱና ስለምሥጢረ ትንሣኤ ሙታን ባስተማረበት ተራራ ስምም በዐቢይ ጾም ውስጥ አምስተኛው ሰንበት “ደብረ ዘይት” በመባል ይታወቃል፡፡ በዚሁ ዕለተ ሰንበትና ሳምንቱን ሁሉ ክርስቶስ በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ተቀምጦ ስለዳግም ምጽአቱ ያስተማረው ወንጌል በሰፊው ይተነተናል ይተረካልም፡፡ በዚህ ዕለት የሚነበቡት ምንባቦችና የሚዘመሩት መዝሙራት፤ የሚቀደሰው ቅዳሴና የሚሰበከው ስብከት በአጠቃላይ የሚሰጠው ትምህርትና የሚተላለፈው መልእክት ሁሉ ዳግም ምጽአቱንና ትንሣኤ ሙታንን የተመረለከተ ነው፡፡
ወደተነሣንበት ርእስ እንመለስና “ዳግም ምጽአት” ወይም የክርስቶስ ዳግመኛ መምጣት ስንል ምን ማለታችን ነው? ዳግመኛ ይመጣል በምንልበት ጊዜም የመጀመሪያው ምጽአቱ መቼ ነበር? የሚሉ ጥያቄዎች ሊነሡ ይችላሉ፡፡ መልሱም እንደሚከተለው ይሆናል፡፡ አባታችን አዳም አትብላ የተባለውን ዕፀበለስ በመብላት የእግዚአብሔርን ቃል በመጣሱና ሕግ በማፍረሱ ምክንያት ከገነት በተባረረና የሞት ሞት አደጋ በገጠመው ጊዜ እግዚአብሔር ራሱ “ከልጅ ልጅህ ተወልጄ ሰው ሆኜ አድንሃለሁ” በማለት በገባለት ቃል ኪዳን መሠረት በኃጢአት ምክንያት ከነበረው ክብሩ ተዋርዶ ምድረ ፋይድ ወርዶ የነበረውን የሰው ልጅ ለማዳንና ወደነበረው ክብሩ ለመመለስ ሲል ከሰማይ ወደምድር በመውረድ ወደዚህ ዓለም መጥቶ ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋን ከነፍሷም ነፍስን ነሥቶ ሰው ሆኖ ለመወለድ ወደዚህ ዓለም የመጣው አመጣጥ የመጀሪያው ምጽአቱ እሱ ነው፡፡ አመጣጡ ግን በብዙ ሁኔታዎች ይለያል፡፡ ይኸውም መጀመሪያ ሰው ሆኖ ዓለምን ለማዳን በመጣ ጊዜ ከቅድስት ድንግል እናቱ ነፍስና ሥጋን ተዋሕዶ ሰው በመሆኑ ምክንያት በሰዎች ሁሉ ላይ ይደርስ የነበረውን ውርደት ገንዘብ አድርጎ በበረት ተወልዶአል፤ በዚህም ዓለም 33 ዓመት ከሦስት ወር በመኖር በምድር ላይ ተመላልሶአል፡፡ በለበሰው ሥጋም ተርቦአል፣ ተጠምቶአል፣ ብዙ ፀዋትወ መከራዎችንም ተቀብሎና በመስቀል ላይ ተስቅሎ በመሞቱ የሰውን ልጅ ሞት በሞቱ ሽሮአል፡፡ ከሞት ከተነሣ በኋላም በታላቅ ክብርና ምስጋና ወደ ሰማይ ዐርጓል፡፡
በዳግም ምጽአቱ ግን “የሰው ልጅ በክብሩ በሚመጣበት ጊዜ ከእርሱም ጋር ቅዱሳን መላእክት ሁሉ በዚያን ጊዜ በክብሩ ዙፋን ይቀመጣል” ተብሎ እንደተጻፈ (ማቴ 25÷31) አመጣጡ እንደዚህ አይደለም፡፡ የዳግም ምጽአቱ አመጣጥ በታላቅ ክብርና በመለኮታዊ ግርማ በቅዱሳን መላእክት ታጅቦ በክብር ዙፋን ላይ ተቀምጦ በጻድቃንና በኃጥአን ላይ እውነተኛ ፍርድን ለመፍረድና ለሁሉም እንደ እምነቱና እንደሥራው ዋጋ ለመክፈል እንደቀድሞው በትኅትና ሳይሆን በግርማ መለኮት የሚመጣ ስለሆነ በተለይ በሕጉ ፀንተው ላልኖሩና ቃሉን ላልጠበቁ ሰዎች እጅግ አስፈሪና አስደንጋጭ ነው፡፡
የሚቀጥለው ጥያቄ ደግሞ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደብረ ዘይት ተቀምጦ ሳለ፣ ስለ ዳግም ምጽአቱ በነገራቸው ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ “ማዕዜ ይከውን ዝንቱ ወምንትኑ ተአምሪሁ ለምጽአትከ ወለኅልፈተ ዓለም” (ማቴ. 24÷3) የመምጣትህና የዓለም መጨረሻ መቼ ይሆናል? ምልክቱስ ምንድነው? ብለው ደቀ መዛሙርቱ ሐዋርያት ለብቻቸው ሆነው እንደጠየቁት ሁሉ እያንዳንዱ ሰው ዳግም ምጽአቱና የዓለም መጨረሻ መቼ ይሆን? ብሎ ሊያስብና ሊጠይቅ ይችላል፡፡ የዚህም መልስ ክርስቶስ ራሱ “ስለዚያች ቀንና ሰዓት ግን ከእግዚአብሔር ከራሱ በቀር የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ ማንም ማወቅ አይችልም” ሲል እንደ አስተማረው ዕለቱ፣ ጊዜውና ሰዓቱ መቼ እንደሚሆን ስለማይታወቅ “ስለዚህ እናንተ ደግሞ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ” (ማቴ 24÷44) በማለት ጌታችን በነገረን ቃ መሠረት በሕገ ወንጌሉ ጸንቶ ንስሐ ገብቶና ራስን አዘጋጅቶ መኖር ብቻ ነው፡፡ ሞትም ለሰው ልጆች ዕለተ ምጽአት ስለሆነና ከሞትም በኋላ ንስሐ ስለማይኖር በዚህች ምድር ላይ በሕይወት እያለን ተዘጋጅተን መኖር ያስፈልገናል፡፡
ዳግም ምጽአቱ መጀመሪያ ዓለምን ከጥፋት ለማዳን ከመጣው አመጣጥ የሚለይበት አንዱ ምክንያትም የጊዜው ጉዳይ ነው፡፡ ወደዚህ ዓለም መጥቶ አዳምንና ዘሩን ሰው ሆኖ እንደሚያድን ለራሱ ለአዳም ቃል በገባለት ጊዜ “በሐሙስ ዕለት ወበመንፈቃ ለዕለት እትወለድ እምወለተ ወለትከ” በማለት አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን ሲፈጸም እንደሚመጣ ዘመኑንና ጊዜውን አረጋግጦ ነግሮት ነበርና በዚሁ መሠረት ትንቢት እየተነገረለት ሱባኤም እየተቆጠረለት ቆይቶ ጊዜው ሲደርስ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ገብርኤል በተናገረው ቃለ ብሥራት መሠረት ወደዚህ ዓለም መጥቶ ከቅድስት ድንግል ማርያም በነሣው ነፍስና ሥጋ ሰው ሆኖ ተወልዶአል፡፡ ሐዋርያው ቅ/ጳውሎስም “ነገር ግን የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን ልጁን ላከ” በማለት የጻፈውም ይህንኑ መሠረት አድርጎ ነው (ገላ. 4÷4)፡፡
ቅዱሳን ሐዋርያት “ዳግም ምጽአቱ” መቼ እንደሚሆን ማወቅ ፈልገው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደብረ ዘይት ተቀምጦ ሳለ ለብቻቸው ቀርበው “ንገረን የመምጫህ ቀን መቼ ነው? ምልክቱስ ምንድነው?” በማለት በጠየቁት ጊዜ ምልክቶቹን ሲነግራቸው ጊዜውን፣ ዕለቱንና ሰዓቱን እንዳልነገራቸው ቅዱስ ማቴዎስ በወንጌሉ ጽፎት እያነበብነው እንገኛለን (ማቴ. 24÷3-51)፡፡ “ጌታችሁ በየትኛው ቀን እንደሚመጣ አታውቁምና ተዘጋጅታችሁ ኑሩ” በማለት የሰጣቸውን የማስጠንቀቂያ ቃልም ከቅዱሳት መጻሕፍት በማንበብ ሁኔታውን መረዳት እንችላለን፡፡ አመጣጡም እንደሌባ በድንገት እንደሚሆን “ነገር ግን ይህን ዕወቁ ባለቤት ሌባ የሚመጣበትን ሰዓት ቢያውቅ ኖሮ ተግቶ በጠበቀ ነበር” እያለ በምሳሌ ከማስረዳቱም በላይ “ስለዚህ እናንተም ተዘጋጅታችሁ ኑሩ፤ የሰው ልጅ በምን ሰዓት እንደሚመጣ አታውቁምና” በማለት የተናገረውን ቃል ቅዱስ ማቴዎስ አሁንም እሱ ራሱ በጻፈው በዚሁ ወንጌል ዘግቦት ይገኛል (ማቴ 24÷43-44)፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስለዳግም ምጽአትና ስለዓለም መጨረሻ፤ ስለትንሣኤ ሙታንም ሁል ጊዜ የምታስተምር ቢሆንም በተለይ በዐቢይ ጾም ውስጥ “ደብረ ዘይት” በመባል በሚታወቀው ዕለተ ሰንበትና ሳምንቱን በሙሉ የበለጠ ትኩረት ሰጥታ እያስተማረች ኖራለች ወደፊትም እስከ ዕለተ ምጽአቱ ድረስ ትቀጥላለች ዕለተ ምጽአቱ (ዳግም ምጽአቱ) መቼ እንደሚሆን ዕለቱ፣ ቀኑና ሰዓቱ በግልጥ ባይታወቅም እግዚአብሔር ባቀደውና በወሰነው ጊዜ እንደሚሆንና መሆኑም እንደማይቀር፣ የታመነ ነው፡፡ ለዚህም ብዙ ማስረጃዎች አሉ፡፡ ከማስረጃዎቹም ጥቂቶቹ የሚከተሉት ናቸውና እንመልከታቸው፡፡
1. ቅዱሳን፣ ነቢያት ስለዳግም ምጽአቱና ስለትንሣኤ ሙታን አስቀድመው የተናገሩት ትንቢት መፈጸም ስላለበትና የማይቀር መሆኑም ስለሚታመንበት ነው፡፡ ከነዚህም መካከል ልበ አምላክ የተባለው ነቢዩ ዳዊት “እግዚብሔርስ ገሐደ ይመጽእ፤ ወአምላክነሂ ኢያረምም፤ እሳት ይነድድ ቅድሚሁ” (“እግዚአብሔር በግልጥ ይመጣል፤ አምላክችን ዝም አይልም፤ እሳት በፊቱ ይነዳል”) በማለት የተናገረው ትንቢት በምሳሌነት ይጠቀሳል፡
2.ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ በዓለም መጨረሻ ዳግመኛ እንደሚመጣ ያስተማረው ትምህርት በቂ ማስረጃ ነው፡፡ (ማቴ 24÷30፤ 26÷64፤ ዮሐ. 14÷3)፡፡
3. ጌታችን በምድር ላይ ሊያደርግ የሚገባውን ሁሉ ፈጽሞ በመስቀል ላይ ጸዋትወ መከራዎችን ሁሉ ተቀብሎ ከሞተና ከመቃብር ከተነሣ በኋላ ወደ ሰማይ በዐረገ ጊዜ ሐዋርያት ወደሰማይ ትኩር ብለው እየተመለከቱ ሳሉ ነጭ ልብስ በለበሱ ሁለት ሰዎች የተመሰሉ መላእክት እናንተ የገሊላ ሰዎች ሆይ ወደ ሰማይ እየተመለከታችሁ ስለምን ቆማችኋል? ይህ ከእናተ ወደ ሰማይ የወጣው (ያረገው) ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲያርግ እንዳያችሁት ሁሉ እንዲሁ ይመጣል” በማለት ስለዳግም ምጽአቱ መስክረዋል፡፡
4. ቅዱሳን ሐዋርያት በየመልእክቶቻቸው ሊቃውንትም በየመጻሕፍታቸው ስለዳግም ምጽአቱና ስለትንሣኤ ሙታን ጽፈዋል፡፡ ከእነሱም መካከል ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ሰማያት፤ የሚንዋወጡበትና የሚያልፉበት ቀድሞ የነበረው ፍጥረት ሁሉ በእሳት ነበልባል የሚቀልጥባት፤ ምድርና በእሷ ላይ ያለው ፍጥረት ሁሉ የሚቃጠልባት የእግዚአብሔር ቀን እንደሌባ በድንገት እንደምትመጣ በመግለጥ (2ኛ ጴጥ. 3÷10) ስለዓለም መጨረሻና ስለ ዳግም ምጽአት በሰፊው ያስተማረ ሲሆን ቅዱስ ጳውሎስም ወደ ተሰሎንቄ ሰዎች በጻፈው መልእክቱ “ወንድሞች ሆይ ስለዘመናትና ስለወራት ምንም እንዲጻፍላችሁ አያስፈልጋችሁም” ካለ በኋላ “የጌታ ቀን ሌባ በሌሊት እንደሚመጣ እንዲሁ ይመጣ ዘንድ ራሳችሁ አጥብቃችሁ አውቃችኋልና” በማለት በብዙ ምሳሌ መስሎ አስተምሮአል፡፡
5. ጌታችን በደብረ ዘይት ተቀምጦ ሳለ ለደቀ መዛሙርቱ የነገራቸው የዳግም ምጽአቱ ምልክቶች በየጊዜው እየታዩና በድርጊትም እየተፈጸሙ በመሆናቸውና ይህም ዳግም ምጽአቱ እየተቃረበ መሆኑን በግልጥ ስለሚያመልክት ዕለተ ምጽአት እና የዓለም መጨረሻ ጊዜው መቅረቡን ያስረዳል፡፡
ለምሳሌ ሕዝብ በሕዝብ ላይ ነገሥታትም በነገሥታት ላይ እየተነሡ በመላው ዓለም ጦርነት እየተካሄደ መሆኑና የጦርነትም ወሬ በየዜና ማሠራጫው ሁሉ በአስጊ ሁኔታ እየተነገረና “ጆሮን ጭው” የሚያደርግ ወሬ ዘወትር እየተሰማ ነው፡፡ የጦርነቱም ፍጥጫና ፉክክር በቀላል መሣሪያ ሳይሆን ዓለምን በቅጽበት ማጥፋት የሚችል የኑክልየር መሣሪያ በታጠቁ ኃይሎች መካከል መሆኑ ደግሞ በእውነትም የዓለም መጨረሻ ጊዜ ቀርበአል የሚያሰኝ ነው፡፡
ቀደም ሲል በ1ኛውና በ2ኛው የዓለም ጦርነት ከዚያም ወዲህ በተለያዩ አገሮች በየጊዜው በተደረጉ ጦርነቶች ያለቀውን እና በጦርነቱ የተጎዳውን ሕዝብ ብዛት ለታሪክ ጸሐፊዎች እንተውና በአሁኑ ጊዜ አልቃኢዳ፣ አይኤስ፣ አልሸባብ … ወዘተ እየተባሉ በሚጠሩ አጥፍቶ ጠፊዎችና አሸባሪዎች እንዲሁም ስለሰው ሕይወት ደንታ በሌላቸው የሥልጣን ጥመኞችና ዘረኝነት በተጠናወታቸው ኃይሎች በሚተኮሱ ጥይቶች በየቀኑ እንደቅጠል የሚረግፈው ሕዝብና በጦርነቱ ምክንያት አካላቸውን እያጡ በከባድ ችግርና በስቃይ ውስጥ የሚገኙት ሰላማውያን ወገኖችም በዓለም ውስጥ ቁጥራቸው እየበዛ መታየቱና በአጠቃላይ የዓለም ሕዝብ ፍቅርና ሰላም አጥቶ በሽብር ውስጥ መሆኑ እነዚህና የመሳሰሉት ዘግናኝ ነገሮች ሲታዩና ሲሰሙ የዓለም መጨረሻ ጊዜ የደረሰ መሆኑን የሚያመለክቱ እውነተኛ ምልክቶች ስለሆኑ እያንዳንዱ ሰው ከኃጢአት ርቆና ንስሐ ገብቶ ወደ እግዚአብሔር በመመለስ ራሱን ከጥፋት ያድን ዘንድ ተዘጋጅቶ መኖር ይገባዋል፡፡
“ወስብሐት ለእግዚአብሔር”