የታዕካ ነገሥት በዓታ ለማርያም ገዳም ዓመታዊ በዓልና የገዳሙን መቶኛ ዓመት የምሥረታ በዓል በታላቅ ድምቀት አከበረ
በመ/ር ሣህሉ አድማሱ
በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የታዕካ ነገሥት በዓታ ለማርያም ገዳም የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም በዓተ ቤተ መቅደስ በዓል እና የዳግማዊ አፄ ምኒልክን የዕረፍት መታሰቢያ በዓል በየዓመቱ ታህሳስ 3 ቀን ሲአከብር መቆየቱ ይታወቃል፡፡ በዘንድሮውም ዓመት ታህሳስ 3 ቀን 2010 ዓ.ም ባከበረው የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም በዓተ ቤተ መቅደስ እና የዳግማዊ አፄ ምኒልክ የዕረፍት መታሰቢያ በዓል በተጨማሪ ገዳሙ የተመሠረተበትን የመቶኛ ዓመት በዓል ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ፣ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፣
ብፁዐን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነት የየመምሪያ ኃላፊዎች፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መምህር ጎይቶኦም ያይኑ፣ የገዳማትና የአድባራት አስተዳዳሪዎች፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን የሰንበት ት/ቤት ወጣቶችና በርካታ ምዕመናን በተገኙበት በታላቅ ድምቀት ተከብሯል፡፡ ገዳሙ በተመሠረተበት ዕለት ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ምኒልክ (ወስመጥምቀተ አስካለማርያም) ከሕንጻው አናት ላይ በመቆም ታላቅ ዕልልታ በማሰማት ደስታዋን እንደገለጸች ታውቋል፡፡
የዘንድሮውን በዓል አከባበር ለየት የሚያደርገው ነጋሪት ተጎስሟል፡፡ ዕንቢልታ ተነፍቷል፣ በገና ተደርድሯል፤ የቅዱስ ያሬድ ድርሰት የሆነው እና በየዓመቱ በሊቃውንቱ በዜማ፣ በዝማሜ እና በወረብ ሲቀርብ የቆየው ንዒ ርግብ… ስምኪ ወለትዬ አስካለ ማርያም የሚለው ያሬዳዊ ቃለ እግዚአብሔር መሳጭ በሆነ ጣዕመ ዜማ ተዘምሯል፡፡
የበበት ንግሥተ ነገሥታት አስካለ ማርያም በአፉሃ… የሚል ያሬዳዊ ግሥ በገዳሙ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች በወረብ ተዘምሯል፡፡
ከዚያም የገዳሙ ሰበካ ጉባዔ ምክትል ሊቀ መንበር የሕንጻውን የምሥረታ በዓል መቶኛ ዓመት በዓል አስመልክተው ባቀረቡት ሪፖርት ሕንጻው ከዕድሜ ብዛት የተነሳ እየፈረሰ መሆኑን እና እድሳቱ በአስቸኳይ መታደስ እንዳለበት ሲገልፁ የገዳሙ ሀብት በደርግ ሥርዓት መወሰዱ፣ ያካባቢው ምዕመናን በመልሶ ማልማት አካባቢውን በመልቀቃቸው፣ ለአብነት ት/ቤቱ መታደስ የገንዘብ እጥረት ማጋጠሙን አብራርተዋል፡፡
ስለ ሕንጻው ቅድመ እድሳት የገዳሙ ኮሚቴ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሥነ ሕንጻ ምሁራን ጋር ውይይት ማካሄዱንም በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡
በተጨማሪም በአንድ የሥነ ሕንጻ ምሁር ስለ ህንጻው የመፍረስ አደጋ ሙያዊ አስተያየት ተሰጥቷል፡፡ ጥገናውም በልዩ ትኩረት የሚካሄድ ነው ተብሏል፡፡
ሕንጻው የሀገር ቅርስ በመሆኑ እና በሕንጻው ውስጥ የነገሥታት አጽም የሚገኝበት በመሆኑ ሁሉም የበኩሉን ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባው የሥነ ሕንጻ ምሁሩ መልእክታቸው አስተላልፈዋል፡፡
ከዚህ በመቀጠል ብፁዕ አቡነ ናትናኤል የቀሌም ወለጋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በዓሉን አስተመልክተው በሰጡት ትምህርት የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ወላጆች ሐና እና ኢያቄም በንጽሕና በቅድስና በመጸለያቸው ዓለምን የምታስታርቅ ልጅ ወለዱ፡፡ እመቤታችንም ኑሮዋን ከመላእክት ጋር አደረገች፡፡
እግዚአብሔርን በቤተ መቅደስ በመኖር አገለገለች በማለት የታሪኩን ቅደም ተከተል በተገቢው መንገድ በመዘርዘር ሰፋ ያለ ትምህርት አስተምረዋል፡፡ በመጨረሻም ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ አቅድም አእኩተቶ (ሮሜ.8) በሚል ርዕስ ጀምረው በዚህ በተቀደሰው እና ታሪካዊ በሆነው አውደምሕረት የተገኘነው ሁላችንም እግዚአብሔር ይባርከን ይቀድሰን፡፡ በዓሉ ታላቅ በዓል ነው፡፡ ይህን በዓል፤ በደመቀ ሁኔታ አክብረነዋል፡፡
ቤተ መቅደስ በተሠራበት ቦታ ሁሉ እግዚአብሔርን ስናመሰግን እንኖራለን፡፡
ኢትዮጵያ የሃይማኖት ሀገር ናት፡፡ ከአባቶቻችን የወረስነውን የቀና ሃይማኖታችንን አፅንተን ልንጠብቅ ይገባናል፡፡ ህልውናውን አምላክነቱን አዳኝነቱን መጋቢነቱን እንድናውቅ ያደረግን አምላክ አነሣሥቶን ነው ወደ ቤተ መቅደስ የመጣነው፡፡ ሥፍር ቁጥር የሌለው ሕዝብ ያላት ሀገር ኢትዮጵያ ናት፡፡ ይህም መታደል ነው፡፡ ኢትዮጵያ በዓልም የተደነቀች ሀገር ናት፡፡ ቱሪስቱ የሚመጣው ወደ ኢትዮጵያ ነው፡፡ የዛሬ በዓል የሚታወቀው እመቤታችን ወደ ቤተ መቅደስ የገባችበት ዕለት በመሆኑ ነው፡፡
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ሥጋ ለብሶ ዓለምን ለማዳን ስላሰበ ከእመቤታችን ተወለደ በማለት ሰፋ ያለ ትምህርትና አባታዊ ቃለ ምዕዳን በመስጠትና በዕድሜ ብዛት ለመፍረስ የተቃረበውን ሕንጻ ጥገና እንዲደረግ አባታዊ ጥሪ በማስተላለፍ የበዓሉ ፍጻሜ ሆኗል፡፡