“ከጠላቶቻችንም እጅ እንዲአድነን የእግዚብሔርን የቃል ኪዳኑን ታቦት ከሴሎ እናምጣ አሉ፡፡”
በመ/ር ሣህሉ አድማሱ
ታቦት
ታቦት የሚለው ቃል ቤተ አደረ ከሚለው ግሥ የወጣ ነው፡፡ ነቢዩ ሙሴ ታቦትን ከግራር እንጨት እንዲሠራ ከእግዚአብሔር ታዘዘ (ዘፀ.25፥1)
የመጀመሪያው የታቦት አሠራር አራት ማዕዘን ያለው ሣጥን የሚመስል ሲሆን ርዝመቱ 125 ወርዱ 75 ቁመቱ 75 ሳንቲ ሜትር ያህል ነው፡፡
ታቦቱ በወርቅ የተለበጠ፣ መክደኛውም ከወርቅ የተሠራ ነበር፡፡ በላዩም የሁለት ኪሩቤል ስዕል ተቀርጿል፡፡ የታቦቱም አገልግሎት አሥርቱ ቃላት የተጻፉባቸው የሁለቱ ፅላት መኖሪያ ነው፡፡
እግዚአብሔር በታቦቱ አማካኝነት ከእስራኤል ሕዝብ ጋር ይገናኝ ነበር፡፡ (ዘፀ.25፥3) ነቢዩ ሙሴ ታቦቱን አሠርቶ ከመገናኛው ድንኳን አኖረው፡፡ የእስራኤልም ሕዝብ ታቦቱን እየያዙ ይጓዙ ነበር፡፡ ዮርዳኖስን ሲሻገሩና የኢያሪኮን ቅፅር ሲዞሩ ካህናቱ ታቦቱን ተሸክመው ከፊት ከፊት ይሄዱ ነበር፡፡ (ኢያ.3፥6)
የእግዚአብሔር ታቦት በኤሊ ዘመን!!
በኤሊ ዘመን ሁለቱ የኤሊ ልጆች አፍኒንና ፊንሐስ ከእግዚአብሔር የቃል ኪዳን ታቦት ጋር ነበሩ፡፡ የእግዚአብሔር የቃል ኪዳን ታቦት ወደ ሰፈር በገባ ጊዜ እስራኤል ሁሉ ታላቅ እልልታ አድርገዋል፡፡
ይሁን እንጂ ፍልስጥኤማውያን የእልልታውን ድምፅ በመስማታቸው ከእስራኤላውያን ጋር ተዋጉ፡፡ ከእስራኤል ሰላሳ ሺህ እግረኞች ወደቁ፡፡ የእግዚአብሔርም ታቦት በፍልስጥኤማውያን ተማረከች፡፡ ሁለቱም የኤሊ ልጆች አፍኒንና ፊንሐስ በእግዚአብሔር ቁጣ ተቀሰፉ፡፡
ካህኑ ኤሊ ያን ጊዜ የዘጠና ስምንት ዓመት ሽማግሌ ነበር፡፡ ዐይኖቹም ማየት እስኪሳናቸው ድረስ ፈዝዘው ነበር፡፡ የታቦተ እግዚአብሔርን መማረክ እና የልጆቹን የአፍኒንና የፊንሐስን መሞት ሲሰማ ከተቀመጠበት ወንበር ወድቆ ሞተ፡፡ ምራቱ የፊንሐስ ሚስት አርግዛ ልትወልድ ተቃርባ ነበር፡፡ የእግዚአብሔር ታቦት እንደተማረከች፣ ባልዋና አማትዋ እንደሞቱ በሰማች ጊዜ ባልዋና አማትዋ ስለሞቱ ክብር ከእስራኤል ለቀቀ ስትል የልጇን ስም ኢካቦድ ብላ ጠራችው፡፡
ፍልስጥኤማውያን የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳኑን ታቦት ከአቤኔዘር ወደ አዛጦን ይዘውት ሄዱ፡፡ በዚያም ወደ ዳጎን (ጣኦት/ቤት አስገቡት፤ በዳጎንም አጠገብ አኖሩት፡፡
ይሁን እንጂ በማግስቱ ዳጎን /ጣኦቱ/ በእግዚአብሔር ታቦት ፊት በግምባሩ ወድቆ ነበር፡፡ እንደገና ቢአነሱትም በድጋሚ በግምባሩ ወደቀ፡፡ እጆቹም፣ እግሮቹም ተሰባበሩ፡፡ የእግዚአብሔርም እጅ በአዛጦን ሰዎች ላይ ከበደች፡፡ በእባጭም መታቸው፡፡ በዚያን ጊዜ የአዛጦን ሰዎች የእስራኤል አምላክ የእግዚአብሔር ታቦት በእኛ ዘንድ አይቀመጥ አሉ፡፡ የእግዚአብሔር ታቦት ከአዛጦን ወደ ጌት ተመለሰች፡፡
የጌትም ሰዎች በእባጭተ መቱ፡፡ ከዚያም የእግዚአብሔር ታቦት ወደ አስቀሎና ተመለሰች፡፡ የአስቀሎናም ሰዎች በእባጭ ተመቱ፡፡ የከታመይቱም ዋይታ እስከ ሰማይ ደረሰ፡፡
በዚሁ ሁናቴ የእግዚብሔር ታቦት በፍልስጥኤማውያን ከተሞች ለሰባት ወራት ያህል ተቀመጠች፡፡
የእግዚአብሔር ታቦት ከፍልስጥኤም ወደ ቤትሳሚስ!!
ፍልስጥኤማውያን ለእስራኤል አምላክ ታቦት ክብርን ለመስጠት ስለበደል መስዋዕት የወርቅ ዕባጮች በማቅረብ የወርቁን ዕቃ በሣጥን ውስጥ አድርገው የእግዚአብሔርን ታቦት በሰረገላ ጭነው ከፍልስጥኤማውያን ድንበር ላይ ወደ ሚገኘው ወደ ቤትሳሚስ በሚወስደው መንገድ በማቅናት በኮረብታው ላይ ወዳለው ወደ አሚናዳብ ቤት አስገብተው አስቀመጡት፡፡
የእግዚአብሔር ታቦት በአሚናዳብ ቤት!!
የእግዚብሔር ታቦት በአሚናዳብ ቤት መቀመጥ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ታቦቱን እንዲጠብቅ እስራኤላውያን የአሚናዳብን ልጅ አልአዛርን ቀደሱት፡፡ የእግዚአብሔርም ታቦት በአሚናዳብ ቤት ለሃያ ዓመታት ያህል ተቀመጠች፡፡
የእግዚአብሔር ታቦት ከአሚናዳብ ቤት ወደ ኢየሩሳሌም!!
ነቢዩ ዳዊት የእግዚአብሔርን ታቦት ከአሚናዳብ ቤት ወደ ኢየሩሳሌም አመጣ፡፡ ነቢዩ ዳዊት የእግዚአብሔርን ታቦት ወደ ኢየሩሳሌም ሲያመጣ ኦዛ የተባለ ሰው በድፍረት ታቦቱን በእጁ በመንካቱ ተቀሰፈ፡፡ (2ሳሙ.6) ጠቢቡ ሰሎሞንም አባቱ ዳዊት ከአሚናዳብ ቤት ያመጣውን የእግዚአብሔር የቃልኪዳን ታቦት ራሱ ባሠራው ቤተ መቅደስ አስቀመጠ፡፡ (1ነገ.8)
የእግዚአብሔር ታቦት ከኢየሩሳሌም ወደ ኢትዮጵያ!!
በብሉይ ኪዳን ንግሥተ ሳባ፣ በሐዲስ ኪዳን ንግሥተ አዜብ፣ በክብረ ነገሥት ንግሥት ማክዳ በመባል የምትታወቀው ኢትዮጵያዊት ንግሥት የንጉሥ ሰሎሞንን ዝና በሰማች ጊዜ በግመሎች ላይ ሺቱ፣ ወርቅና እንቁ አስጭና ወደ ኢየሩሳሌም ሂዳ ለንጉሡ ለሰሎሞን ሰጠችው፡፡ ንጉሥ ሰሎሞንም በገዛ እጁ ከሰጣት ሌላ የወደደችውን ሁሉ ስጦታ ለሳባ ንግሥት ሰጣት፤ እርስዋም ከባሪያዎችዋ ጋር ወደ ምድርዋ ተመለሰች (1ነገ.10፥1-13)
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓተ አስተምህሮ መሠረት ንግሥተ ሳባ ከንጉሥ ሰሎሞን ቀዳማዊ ምኒልክን ወለደች፤ ቀዳማዊ ምኒልክም ካደገ በኋላ ወደ እናቱ ወደ ንግሥተ ሳባ ሀገር ወደ ኢትዮጵያ ሦስት መቶ አስራ ስምንት ሌዋውያን እና ካህናትን ይዞ ሲመጣ ታቦተ እግዚአብሔርን (ታቦተ ፅዮንን) ይዞ መጣ፡፡
የእግዚአብሔር ታቦት በአክሱም ፅዮን!!
አክሱም
የአክሱም ከተማ የንግሥተ ሰባ መናገሻ ከተማ ሆና አገልግላለች፤ አክሱም ጥንታዊት፣ ቀዳማዊት፣ የነገደ ኩሽ መዲና፣ በኋላም የሰባውያን መዲና መሆንዋ ተረጋግጧል፤ አክሱም የኢትዮጵያ መናገሻ ከተማ ሆና ከአንድ ሺህ ዓመት በላይ እንደኖረች የታሪክ መዛግብት ይስማማሉ፤ የተመሠረተችውም እንደ ሰንሰለት በተያያዘ ኮረብታ መካከል ነው፤ ከሰሜናዊ ምሥራቅ አንስቶ እስከ ሰሜናዊ ምዕራብ በሚዘልቅ ኮረብታ ተከባለች፤ የአክሱም ከተማ ከክርስቶስ ልደት በፊት ከሁለት ሺህ ዓመተ ዓለም አስቀድሞ እንደተመሠረተች የተለያዩ የታሪክ መዛግብት ይናገራሉ፡፡
የእግዚአብሔር የቃል ኪዳኑ ታቦት ከንጉሥ ሰሎሞን እና ከንግሥተ ሳባ አብራክ የተከፈለው /የተወለደው/ ቀዳማዊ ምንይልክ እና አብረውት ወደ ኢትዮጵያ ከመጡ ሌዋውያን ጋር የንግሥተ ሳባ መናገሻ በሆነው በአክሱም ፅዮን በቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን አስቀምጠዋል፡፡ በዓሉም በየዓመቱ ህዳር 21 ቀን ዓለም አቀፍ በዓል ሆኖ በከፍተኛ ድምቀት ሲከበር ቆይቷል፤ አሁንም በታላቅ ድምቀት እየተከበረ ይገኛል፡፡