የየካ አባዶ ምሥራቀ ፀሐይ ቅዱስ ሚካኤል እና 24 ካህናተ ሰማይ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ቅዳሴ ቤት ተከበረ!!
በመ/ር ሣህሉ አድማሱ
በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በየካ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ሥር የሚገኘው እና ለአስራ አራት ተከታታይ ዓመታት ያህል ሲገነባ የቆየው የየካ አባዶ ምሥራቀ ፀሐይ ቅዱስ ሚካኤል እና አርባእቱ እንስሳ ብፁዕወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ፣
ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፣ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራአስኪያጅ መምህር ጎይቶም ያይኑ፣ የየካ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት የሥራ ኃላፊዎች፣ የገዳማትና አድባራት አስተዳደሪዎች፣ የደብሩ ካህናትና የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች እና በርካታ ምዕመናን በተገኙበት እሁድ ህዳር 10 ቀን 2010 ዓ.ም በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ተባርኮ የቅዳሴ ቤቱ በዓል በታላቅ ድምቀት ተከብሯል፡፡
ይህ ታሪካዊና ዘመናዊ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ተባርኮ የቅዳሴ ቤቱ በዓል በተከበረበት ወቅት የህንጻውን ግንባታ ሥራ በማፋጠን ትልቁን የማስተባበር ድርሻ ሲያከናውኑ የቆዩ መሆናቸው የሚነገርላቸው የደብሩ አስተዳዳሪ መልአከ ፀሐይ አባ ሀብቴ ባቀረቡት ሪፖርት እንደተገለፀው የየካ አባዶ ምሥራቀ ፀሐይ ቅዱስ ሚካኤል እና 24 ካህናተ ሰማይ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን በ390 ካሬ ሜትር ስፋት ላይ ያረፈ ባህል ተኮር እና ታሪካዊ ሕንጻ ነው፡፡
ከዋናው ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ጋር የ25 ሜትር ርቀት ባለው ድልድይ የተያያዘ ሕንጻ ቤተልሔም ተሠርቶ የግንባታ ሥራው የተጠናቀቀ ስለሆነ ከሕንጻ ቤተ ክርስቲያኑ ጋር ተባርኮ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል፡፡
ለሕንጻ ቤተ ክርስቲያኑ አጠቃላይ ግንባታ ሥራ ከ8 ሚሊዮን 4 መቶ ሺህ ብር ያላነሰ ገንዘብ ወጪ ሆኗል፡፡ ቤተ ክርስቲያኑ ከ63 ሺህ ካሬ ሜትር ስፋት በላይ የይዞታ ቦታ ቢኖረውም በአንድ አንድ ግለሰቦች የይዞታ ይገባኛል ጥያቄ እየተነሳ አለመግባባት ሲከሰት ቆይቷል፡፡
ይሁን እንጂ በደብሩ ቀጣይ የሥራ ዕቅድ መሠረት ችግሮቹ ሙሉ በሙሉ ተወግደው የአረጋውያን መርጃ ማዕከል፣ የአብነት ትምህርት ቤት እና የልማት ተቋማት ሥራዎች እንደሚከናወኑ የደብሩ አስተዳዳሪ በሪፖርታቸው አብራርተዋል፡፡
በመጨረሻም ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ የቅዳሴ ቤቱን በዓል ለማክበር ለተሰበሰበው በርካታ ምዕመናን ባስተላለፉት አባታዊ መልእክት ይህንን ታላቅ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን በገንዘብ፣ በሐሳብና በጉልበት ተባብራችሁ ለፍጻሜ ያደረሳችሁ ሁላችሁም እንኳን ደስ አላችሁ!!
በኦርቶዶክሳዊ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓተ ቀኖና መሠረት ይህንን ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን በጸሎትና በቅዱስ ቅብአት ባርከነዋል፤ ቀድሰነዋል፡፡ ከልዩ ልዩ ሕንጻዎች ተለይቶ የእግዚአብሔር ቤት ሆኗል፡፡ ከዛሬ ጀምሮ ልጆቻችሁ ይጠመቁበታል፤ ቅዱስ ሥጋው ይፈተትበታል፤ ክቡር ደሙ ይቀዳበታል፣ ቦታው ህፃናት የሚማሩበት፣ አረጋውያን የሚጦሩበት ማዕከል እንዲሆን እንመኛለን በማለት ቅዱስነታቸው አባታዊ ትምህርት ሰጥተው እና ቃለ ምዕዳን አስተላልፈው የበዓሉ መርሐ ግብር በጸሎት ተጠናቋል፡፡