የጥቅምት 2010ዓ.ም. የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ተጠናቀቀ
ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ መደበኛ ስብሰባ በዓመት ሁለት ጊዜያት እንዲሆን በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 5 ንዑስ አንቀጽ 164 በተደነገገው መሠረት ምልዓተ ጉባኤው ከጥቅምት 6 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ የመንበረ ፓትርያርኩን አጠቃላይ ሰበካ መንሳዊ ጉባኤና ዓመታዊውን የቅዱስ ሲኖዶስ መደበኛ ስብሰባ ለ15 ቀናት ሲያካሒድ ሰንብቷል፡፡
በዚሁ መሠረት ቅዱስ ሲኖዶስ የመክፈቻውን ሥርዓተ ጸሎት ካደረሰ በኋላ ወሳኝ በሆኑ የአጀንዳ ነጥቦች ተወያይቶ የሚከተሉትን ውሳኔዎች አሳልፎአል፡፡
1. ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ በጉባኤው መክፈቻ ያደረጉት ታሪካዊ ንግግር የቤተ ክርስቲያናችንን ሁለንተናዊ ሕይወት የቃኘ፣ ለሀገራችንና ቤተ ክርስቲያናችን ዕድገትንና የሰላም አስፈላጊነትን በስፋት የገለፀ በመሆኑ ጉባኤው በሙሉ ድምፅ ተቀብሎታል፡፡
2. የሠላሳ ስድስተኛውን የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንሳዊ ጉባኤ የገራ መግለጫ አንዳንድ ማሻሻያ በማድረግ የጋራ መግለጫው የ2010 በጀት ዓመት ተግባር ሆኖ ያገለግል ዘንድ ምልዓተ ጉባኤው ተስማምቷል፡፡
3. የቤተ ክርስቲያናችን እምነትና ሥርዓተ አምልኮ እስከ አሁን ደረስ ተከብሮና ተጠብቆ እንደኖረ ሁሉ አሁንም ከመንበረ ፓትርያርክ እስከ አህጉረ ስብከት የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ያለው የመንፈሳዊና የማኅበራዊ አገልግሎት መዋቅር በበለጠ ተጠናክሮ ይቀጥል ዘንድ መመሪያ ተሰጥቷል፡፡
4. በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ሒሳብና በጀት መምሪያ ተዘጋጅቶ የቀረበው የ2010 ዓ.ም. በጀት የክፍያው ጣሪያ ተጠብቆ ሥራ ላይ እንዲውል ምልዓተ ጉባኤው ተስማምቷል፡፡
5. የአንድ ሀገር ዕድገትና መሠረታዊ ፍላጎት ግቡን ሊመታ የሚችለው የሃይማኖቱና የሞራል ስሜቱ የማይወቅሰውን በሚሠራ፣ በመልካም ስነ ምግባር በታነፀ፣ የሥራን ክቡርነት በተረዳና እግዚአብሔርን መፍራት የጥበብ መጀመሪያ መሆኑን ባስተዋለ ትውልድ ተደግፎ ሲገኝ ስለሆነ፣ ኅብረተሰቡ ይህኑ በመረዳት
• በትዕግሥትና በመቻቻል፣
• በመካባበርና በመናበብ፣
• በመደማመጥና በመግባባት መንፈስ በአንድነት ተባብሮ እንዲሠራ ቅዱስ ሲኖዶስ ጥሪውን አስተላፏል፡፡
6. የነገድ፣ የሃይማኖትና የጾታ ልዩነት ሳይኖር ለጋራ ህልውና ለጋራ ልማትና ለጋራ ብልጽግና ለሀገራችን ኢትዮጵያና ለጎረቤት አህጉር ብሩህ ተስፋ ሰንቆ እንደሚመጣ የተነገረለት የዓባይ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት ኢትዮጵያዊነቱን እያስመሰከረ ስለመጣ አሁንም የፕሮጀክቱ ሥራ አሁንም የፕሮጀክቱ ሥራ ተጠናክሮ ለውጤት እስከሚበቃ ድረስ ሁሎችም ኢትዮጵያውያን አስፈላጊውን ድጋፍ በመለገስ እንዲተባበሩ ቅዱስ ሲኖዶስ ያሳስባል፡፡
7. ትውልድ ሁሉ የሙያና የስነ አእምሮ ብቃቱን አሳድጎ ሥራ የመፍጠር ክሂሎቱን እንዲያረጋግጥ ቅዱስ ሲኖዶስ ጥሪውን አስተላልፏል፡፡
8.ዕቅድን በተግባር ለማረጋገጥ
• ሠርቶ ለማግኘት
• ውሎ ለመግባት
• አድሮ ለመነሣት
• ዘርቶ ለማምረት
• ነግዶ ለማትረፍና በነፃነት ለመኖር ሰላም ያስልጋል፡፡
ስለዚህ ሀገራችን ኢትዮጵያ ለአፍሪካ አህጉር የነፃነት ምልክት እንደሆነች ሁሉ የሰላምና የጸጥታም ምልክት መሆን አለባት፤ ከዚህ አንፃር ሰሞኑን በተለያየ ምክንያት በወገኖቻችን መካከል የተከሰተው ግጭት ተወግዶ ሙሉ ሰላምን የማስፈኑ ሥርዓት ተፋጥኖ እንዲረጋገጥ፣ ከዚህም ጋር በግጭቱ ምክንያት ለተጎዱ ወገኖቻችን ከመንበረ ፓትርያርክ እስከ አህጉረ ስብከት የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ድረስ ባለው መዋቅር ብር 6,000,000 (ስድስት ሚሊዮን) የገንዘብ ድጋፍ እንዲደረግ፡፡ እንዲሁም ከጥቅምት 27 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ በመላ አገሪቱ ባሉት ገዳማትና አድባራት ለሁለት ሱባዔ ማለትም ለ14 ቀናት ያህል ጸሎተ ምሕላ እንዲደረግ ተወስኗል፡፡
9. በውጭ ሀገር ከሚኖሩት አባቶች ጋር ቀደም ሲል ተጀምሮ የነበረው ዕርቀ ሰላም አሁንም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ አሳልፎአል፡፡
10. በቃለ ዓዋዲው የቤተ ክርስቲያናችን መተዳደሪያ ደንብ መሠረት የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታዮች የሆኑት ወጣቶች በየአጥቢያ ቤተ ክርስቲያናቸው በሰንበት ትምህርት ቤት ተደራጅተው በየሰበካ ጉባኤው አመራር ሰጭነት እንዲማሩ ምልዓተ ጉባኤው አመራርን ሰጥቷል፡፡
11. በምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት የሚገኘው የዝዋይ ሐመረ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል ገዳም የካህናት ማሠልጠኛ ተቋም ወደ ኮሌጅ ደረጃ ማደግ ያስችለው ዘንድ ከክፉሉ ሊቀ ጳጳስ የቀረበውን ፕሮፖዛል ጉባኤው ተቀብሎ አጽድቆታል፡፡
12. በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስም መንፈሳዊ ማሠልጠኛ አቋቁመው ለሚንቀሳቀሱ የተለያዩ ማኅበራት የሚያገለግል እስካሁን ድረስ የተዘጋጀ የማኅበራት ማደራጃ ደንብ የሌለ በመሆኑ ለወደፊቱ ሕገ ቤተ ክርስቲያኑንና ቃለ ዓዋዲውን መሠረት ያደረገ የማኅበራት ማደራጃ ደንብ በሕግ ባለሙያዎች እንዲዘጋጅ ጉባኤው ተስማምቶ ወስኗል፡፡
13. በጋሻው ደሳለኝ የተባለ ግለሰብ በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ለበርካታ ዓመታት ለምእመናን ሲያስተላልፍ የነበረው የክህደት ትምህርት በመረጃ ተስብስቦ ችግሩ ለቅዱስ ሲኖዶስ ከቀረበ በኋላ ከ15/02/2010 ዓ.ም. የክህደት ትምህርቱን በማውገዝ ከቤተ ክርስቲያናችን እንዲለይ ተደርጓል፣ በቤተ ክርስቲያናችን ስም እንዳያስተምር ተወግዟል፡፡
14. በተመሳሳይ መልኩም በአሜሪካን ሀገር በዋሽንግተን ዲ.ሲ. የሚያገለግሉት አባ መዓዛ ክርስቶስ በየነ እያስተማሩ ያለው የክህደት ትምህርት ለቅዱስ ሲኖዶስ በመረጃ ቀርቦ የተረጋገጠባቸው ስለሆነ ሥልጣነ ክህነታቸው ተይዟል፤ ያሉበትን ቤተ ክርስቲያን ጨምሮ በማናቸውም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት እንዳይሰጡ ታግደዋል፡፡
15. ወልደ አብ በሚል ርእስ፤ ገብረ መድኅን በተባለ ግለሰብ የተጻፈው የክህደትና የኑፋቄ ትምህርት የቅብዓትንና የጸጋን የክህደት ትምህርት የሚያስፋፋ በመሆኑ ካህናትን ከካህናት ምእመናንን ከምእመናን የሚያጋጭ ከመሆኑ ጋር፤ ከቤተ ክርስቲያናችንም አልፎ በሀገራችን ሁከት ለማስነሣት ታስቦ የተዘጋጀ ሆኖ ስለተገኘ፣ መጽሐፉ ከማናቸውም አገልግሎት እንዲለይ ተወግዟል፡፡
16. ለገዳማት መተዳደሪያ እንዲሆን የተዘጋጀው ደንብ ረቂቁ ተስተካክሎ የቀረበ በመሆኑ በሥራ ላይ እንዲውል ጉባኤው ተስማምቷል፡፡
17. ተሐድሶ እየተባለ የሚጠራው የኑፋቄ እምነት ማኅበር እራሱን ኦርቶዶክሳዊ በማስመሰል የቤተ ክርስቲያኒቱን ህልውና እየተፈታተነ ከማስቸገሩ የተነሣ ቅዱስ ሲኖዶስ ቀደም ሲል ፀረ ተሐድሶ ኮሚቴ በየአህጉረ ስብከቱ ተቋቁሞ የመከላከልና ቤተ ክርስቲያኒቱን የመጠበቅ ሥራ እንዲያከናውን ውሳኔን መስጠቱ የሚታወስ ነው፡፡ አሁንም ከቤተ ክርስቲያኒቱ ማዕከላዊ አስተዳደር እስከ አህጉረ ስብከት ባለው መዋቅር የተቋቋመው ፀረ ተሐድሶ ኮሚቴ ተጠናክሮ የመከላከሉን ሥራ እንዲቀጥል ቅዱስ ሲኖዶስ አመራር ሰጥቷል፡፡
ምልዓተ ጉባኤው ከዚህ በላይ በተገለፁትና በሌሎችም መንፈሳዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ አስፈላጊውን መመሪያ ከሰጠ በኋላ ስበስባውን በጸሎት አጠናቆአል፡፡
እግዚአብሔር አምላካችን ለሀገራችንና ለዓለሙ ሁሉ ሰላሙን፣
ለሕዝባችን ፍቅር አንድነቱን ይስጥልን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን!
አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
ጥቅምት 21 ቀን 2010 ዓ.ም.
አዲስ አበባ – ኢትዮጵያ