‹‹ልጄን ከግብፅ ጠራሁት››

                                                                                                                       ከሊቀ ብርሃናት ኢሳይያስ ወንድምአገኘሁ
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህች ምድር ላይ የፈጸማቸው ድርጊቶች ሁሉ እንደ እንግዳ ደራሽ እንደ ውኃ ፈሳሽ በድንገት የተፈጸሙ ሳይኑ አስቀድሞ በኅሊና አምላክ የነበሩ፣ ትንቢት የተነገረላቸውና ሱባዔም የተቆጠራላቸው በመሆናቸው ሁሉም ጊዜአቸውንና ወቅታቸውን ጠብቀው የተፈጸሙ ናቸው፡፡
ለምሳሌ ያህል ስለጽንሰቱ፣ ስለ ልደቱና ስለ ጥምቀቱ፤ ስለሕማሙ፣ ስለስቅለቱና ስለሞቱ እንዲሁም ስለትንሣኤውና ስለዕርገቱ … ወዘተ ማለት ከጽንሰቱ እስከ ዕርገቱ ከዚያም በላይ ስለዕለተ ምጽአቱ ያሉት ሁሉ በትንቢተ ነቢያት የተነገሩ ናቸው፡፡ በዚህም መሠረት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእናቱ ጋር ወደምድረ ግብፅ ስለመሰደዱ እና በዚያም ስለፈጸማቸው ተግባራት አስቀድሞ ነቢያት ተናግረው እንደነበረ በቅዱሳት መጻሕፍት ተጽፎ ይገኛል፡፡
ወደ ግብፅ ስለመውረዱ ነቢዩ ኢሳይያስ  “ናሁ እግዚአብሔር ይነብር ዲበ ደመና ቀሊል ወይመጽእ ውስተ ምድረ ግብፅ ….” (እግዚአብሔር በፈጣን ደመና ተቀምጦ ወደግብፅ ይመጣል)፡፡ የሚለው የትንቢት ቃል ለጊዜው እግዚአብሔር በኤርሚያስ አድሮ የግብፅን ጣዖታት የሚያጠፋ መሆኑን የሚገልጥ ሲሆን ፍፃሜው ግን እግዚአብሔር አምላክ በረቂቅ ምሥጢርና በመንፈስ ቅዱስ ልዩ ግብር ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋን ከነፍሷም ነፍስን ነሥቶና በፍጹም ተዋሕዶ ሰው ሆኖ በተወለደ ጊዜ በወቅቱ በእስራኤል በመንግሥት ዙፋን ላይ ነግሦ በነበረው ጨካኝና ርጉም ሄሮድስ ምክንያት እናቱ ድንግል ማርያም ልጇ ኢየሱስ ክርስቶስን ይዛ ዮሴፍና  ሰሎሜን አስከትላ ወደ ምድረ ግብፅ መሰደዷን የሚያመለክት ነው፡፡ (ኢሳ. 19÷1) “ፈጣን ደመና” የተባለች እመቤታችን ቅድስት ማርያም ናትና፡፡ ቅዱስ ኤፍሬምም እመቤታችን በደመና እንደምትመሰልና ደመናም ተብላ እንደምትጠራ “አንቲ ዘበአማን ደመና እንተ አስተርአይኪ ለነ ማየ ዝናም” (ማየ ዝናምን ቋጭራ የታየች እውነተኛ ደመና አንቺ ነሽ”)፡፡ በማለት ድንግል ማርያምን በደመና ጌታችን ኢየሱስ ከርስቶስን ደግሞ በማየ ዝናም መስሎ የተናገረው ቃል ትልቅ ማስረጃ ነው፡፡ እሱ ራሱ ኢየሱስ ክርስቶስም “እነ ውእቱ ማየ ሕይወት፡፡ (የሕይወት ውኃ እኔ ነኝ)” በማለት እውነተኛ ሕይወት ውኃ እሱ ራሱ እንደሆነ አረጋግጦ ተናግሮአል፡፡
ነቢዩ ሆሴዕም ጌታችን ከእናቱ ከድንግል ማርያም ጋር ወደ ምድረ ግብፅ ተሰዶ ሦስት ዓመት ተኩል ከቆየ በኋላ ሥልጣኑን የሚቀማው መስሎት ይገድለው ዘንድ በጥብቅ ይሻው የነበረው ጨካኙ ርጉም ሄሮድስ ከሞተ በኋላ በመልአኩ ቃል መሠረት ወደ አገሩ የሚመለስ መሆኑን አስቀድሞ የተናገረው የትንቢት ቃል ከላይ በርእሱ እንደተገለጠው “እምግብፅ ጸዋዕክዎ ለወልድየ” (ልጄን ከግብፅ ጠራሁት) የሚል ነው፡፡ ሆሴዕ 11÷1) ይህንንም ወንጌላዊው ማቴዎስ እነሆ የጌታ መልአክ በሕልም ለዮሴፍ ተገልጦ “ተንሥእ ወንሣእ ሕፃነ ወእሞ ወጒየይ ኃበ ምድረ ግብፅ፣ ወንበር ዝየ እስከ አመ እነግረከ” ሂሮድስ ሕፃኑን ሊገድለው ይሸዋልና ተነሣ ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ ወደ ምድረ ግብፅ ሽሽ እስከምነግርህም ድረስ በዚያው ተቀመጥ አለው፡፡ እሱም ተነሥቶ ሕፃኑንና እናቱን ይዞ ወደ ግብፅ ሄደ ከእግዚአብሔርም ዘንድ “ልጄን ከግብፅ ጠራሁት” ተብሎ በነቢይ የተነገረው ይፈጸም ዘንድ ሄሮድስ እስኪሞት ድረስ በዚያ ኖረ” በማለት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ልጇን ኢየሱስ ክርስቶስን ይዛ ከዮሴፍና ከሰሎሜ ጋር ወደ ግብፅ መሰደዷንና በመልአኩ ቃልም መሠረት ሄሮድስ በሞተ ጊዜ ወደ አገራቸው ወደ ምድረ እስራኤል መመለሳቸውን በቅደም ተከተል በግልጥ ጽፎት ይገኛል፡፡ (ማቴ. 2÷13-15)
ጌታችን እና እናቱ ድንግል ማርያም ወደ ምድረ ግብፅ በተሰደዱ ጊዜ የተጓዙት አድካሚ የሆነ የስደት ጉዞና በየመንገዱ ይደርስባቸው የነበረው ችግር በቀላል የሚገመት እንዳልነበረ መገመት አያዳግትም፡፡ ምክንያቱም እንደ አሁኑ ዘመን መንገዱ ባልሰለጠነበት፣ የየብስና የአየር መገናኛ ባልነበረበት፣ የእንግዶች ማረፊያም በሌለበት፣ ከአንድ ቦታ ተነሥቶ ወደ ሌላው ቦታ በአጭር ጊዜ መድረስ በማይቻልበት ያውም ሄሮድስን ከሚያህል ታላቅ የንጉሥ ባላጋራ ለመሸሽ የሚደረግ ጉዞ በመሆኑ ያ የሽሽት ጉዞ እጅግ በጣም አድካሚና አስቸጋሪ አሰልቺም እንደነበረ መገመት የሚያዳግት አይሆንም፡፡
ከመጀመሪያው ምዕት ዓመት ጀምሮ እስከአሁን ድረስ በምሥራቁም ሆነ በምዕራቡ የክርስትና ዓለም በቃልም ሆነ በጽሑፍ ስለእመቤታችንና ስለጌታችን ስደት የሚያወሱ ብዙ የታሪክ ማስረጃዎች እንደሚገኙ አያጠራጥርም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንም እመቤታችን ልጇን አዝላ ወደ ምድረ ግብፅ ስትሄድና ስትመለስ በዚያውም በምድረ ግብፅ ከአንዱ አውራጃ ወደሌላው አውራጃ ስትንከራተት የደረሰባትን ችግርና ያደረገችውን አሰቃቂ የስደት ጉዞ በተመለከተ በሰፊው የሚያስረዱ የታሪክና የብዙ ተአምራት መጻሕፍት እንዳሏት ይታወቃል፡፡ በዚህ ጉዞ ወቅትም ቅ/ዑራኤል እመቤታችንን እየመራት ወደ ኢትዮጵያ መጥታ በብዙ የታሪክ ቦታዎች እንደደረሰች የሚያወሱ ብዙ መጻሕፍት በሀገራችንና በቤተክርስቲያናችን በተለያዩ አድባራትና ገዳማት ይገኛሉ፡፡ በተለይም በጣና ውስጥ ያሉ እንደ ክብራን ገብርኤል እና እንደ ጣና ቂርቆስ ያሉ ደሴቶች በምሳሌነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
ስለዚህ በምድረ ግብፅ እመቤታችንን ያስተናግዱ እንደነበሩት እንደ ደብረ ቁስቋም ያሉ ቦታዎች እንደሚከበሩ ሁሉ በኢትዮጵያም ያሉ የታሪክ ቦታዎች እንደዚሁ ሊከበሩና እንክብካቤም ሊደረግላቸው ይገባል፡፡ የጥንቶቹ አባቶችና እናቶች በተለይም ነገሥታቱ ከኢትዮጵያም አልፈው በውጭ አገር ያሉትን የእምነትና የታሪክ ቦታዎችን ይረዱና ይደግፉ አንደነበር ግልጥ ነው፡፡ አቴጌ ምንትዋብ የተባሉት የኢትዮጵያ ንግሥት እመቤታችንን ከመውደዳቸው የተነሣ ቅድስት ድንግል ማርያም ከስደት ስትመለስ በዚያ አርፋ ብዙ ተአምራት የፈፀመችባትን በምድረ ግብፅ የምትገኘውን ደብረ ቁስቋም የተባለችውን ገዳም ይረዷትና ይደግፏት  እንደነበር ከታሪክ ማኅደር መረዳት ይቻላልና እኛም ታሪካውያን ቦታዎችን በመንከባከብና በማክበር ረገድ የቀድሞ አባቶችን አርአያ ልንከተል ይገባናል፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የእመቤታችን ድንግል ማርያምን የስደቷን መታሰቢያ ከመስከረም 26 እስከ ኅዳር 5 ቀን ባሉት ዕለታት በየዓመቱ በየትኛውም አገር ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የስደቷን ነገር በሚያወሱ ልዩ ልዩ መዝሙራት እና ምስጋናዎች  እያከበረች ኖራለች፡፡ ወደፊትም እስከዕለተ ምጽአት ያለማቋረጥ ትቀጥላለች፡፡
ከመስከረም 26 እስከ ኅዳር 5 ቀን ያለው ይህ ወር ክረምት አልፎ ደመናው ተገፎ ፀሐይ በድምቀት የምትታይበት ምድሪቱ ሁሉ በአበባ የምታሸበርቅበት ወቅት በመሆኑ ወሩ “ወርኅ ጽጌ ማኅሌቱም ማኅሌተ ጽጌ” በመባል ይታወቃል፡፡ በዚሁ አንፃር “በትር ትወጽእ እምሥርወ እሴይ ወየዐርግ ጽጌ እምጒንዱ …” ትርጓሜውም “ከእሴይ ሥር በትር ትወጣለች አበባም ከግዱ ይወጣል”፡፡ በማለት ነቢዩ ኢሳይያስ ቀደም ሲል ስለ እመቤታችን የተናገረው ትንቢት እውነተኛ ትርጉሙን እንዳገኘ መረዳት ይቻላል፡፡ (ኢሳ. 11÷1)፡፡
ከላይ እንደተገለጠው በወርኅ ጽጌ ውስጥ በየሳምንቱ እኹድ ከማታ እስከጧት ሌሊቱን በሙሉ በሚቆመው ማኅሌተ ጽጌ እመቤታችን ድንግል ማርያም ልጇ ኢየሱስ ክርስቶስን በጀርባዋ እያዘለች በእጆቿም እየታቀፈች ከቅዱስ ዮሴፍና ከሰሎሜ ጋር ያደረገችውን አሰቃቂ የስደት ጉዞ፤ ረኃቡንና ጥሙን (ጥማቱን)፤ ከዐይኗ የፈሰሰውን መራር ዕንባና ከቦታ ወደ ቦታ ስትዘዋወር ይደርስባት የነበረውን ከባድ ኃዘን የሚገልጡ የኃዘን መዝሙሮች ይዘመራሉ ይጸነጸናሉ፤ ይመረገዳሉ በመጨረሻም ወረቦቹ በየጊዜው እየተወረቡ ይሸበሸባሉ፡፡ የመዝሙራቱና የማኅሌተ ጽጌው በተለይም ሰቆቃወ ድንግል በሚባለው ክፍል የማኅሌቱና የመዝሙራቱ  ምሥጢራቸው የሚያሳዝን ቢሆንም ምስጋናው እጅግ በጣም ደስ የሚያሰኝ ነው፡፡ ከዚህም ጋር ወርኃ ጽጌውን በሙሉ በጾምና በጸሎት የሚያሳልፉ አባቶችና እናቶች እንዳሉ ግልጥ ነው፡፡ ይልቁንም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ አባቶችንና እናቶች ብቻ ሳይሆኑ ወጣቶችም በብዛት ሲጾሙት ይታያሉ፡ ወርኃ ጽጌን የሚጾሙ ሰዎች የሚጾሙት በቤተክርስቲያን መመሪያና ትእዛዝ ሳይሆን በየግል ፈቃዳቸው በእመቤታችን ላይ የደረሰውን ስደትና መከራ በማሰብ የሚጾሙት ጾም በመሆኑ ‹‹የፈቃድ ጾም›› በመባል ይታወቃል፡፡ ምክንያቱም በሕገ ቤተ ክርስቲያን የተደነገጉት ሰባት አጽዋማት ብቻ ሲሆኑ በወርኃ ጽጌ የሚጾመው ጾም በፍትሐ ነገሥት አንቀጽ 15 ላይ ከተደነገጉት አጽዋማት ጋር ቁጥር የሌለው በመሆኑ ነው፡፡ ቢሆንም “እድልው ለጾም” ለጾም አድሉ በሚለው ቃል መሠረት ወቅቱ ለእመቤታችን ያላቸውን ፍቅርና መንፈሳዊ ስሜት የሚገልጡበት በመሆኑ ዋጋ እንደሚያገኙበት አያጠራጥርምና ለምን ጾሙ ተብለው ሊወቀሱ አይችሉም፡፡
የእመቤታችንና የጌታችን ስደት ምንን ያመለከታል?
1.እመቤታችን ለጊዜው ልጇ ወዳጇ ኢየሱስ ክርስቶስን ይዛ የተሰደደችው ጌታችንን ከርጉም ሄሮድስ ለማሸሽና ከሞት ለማዳን እንደሆነ ይታወቃል፡፡
2.የጌታችን ስደት ግን ነቢያት የተናገሩት ትንቢት መፈጸም ስላለበት ያንን ለመፈጸምና በስሙ መከራ ለሚቀበሉና ለሚሰደዱ ሁሉ አርአያና አብነት ለመሆን ነው፡፡
3. ወደ ምድረ ግብፅ የተሰደዱት የአባቶቹ እስራኤላውያን ስደት ለእሱ ስደት ምሳሌ ስለነበረ ያንን ለመፈጸምና ተግባራዊ ለማድረግ ነው፡፡
በመሠረቱ ስደት የሚያስከትላቸው ችግሮች እጅግ ብዙዎች በመሆናቸው በሃይማኖትና በፖለቲካ ምክንያት ሕይወትን ለማዳን ካልሆነ በቀር ስደት ፈጽሞ የሚመረጥ ነገር አይደለም፡፡ በሃይማኖት ምክንያት ለሚሰደዱ ግን ከርስቶስ ራሱ አርአያና ምሳሌ ሆኖ ከእናቱ ከድንግል ማርያም ጋር ከመሰደዱም በላይ “ስለጽድቅ የሚሰደዱ ብፁአን ናቸው መንግሥተ ሰማያት የእነሱ ናትና” በማለት ያስተማረው ትምህርት በአንቀጸ ብፁዓን ተጽፎ ስለሚገኝ ሃይማኖትን ላለመካድ የሚደረግ ስደት ዋጋ እንዳለው የታወቀ ነው፡፡
በአሁኑ ጊዜ ግን ብዙዎቹ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ስደታቸው በሃይማኖት ምክንያት ከሚመጣ ችግር ለመዳን ወይም በፖለቲካ ችግር ብቻ ሳይሆን እንጀራ ፍለጋ በሚል ሰንካላ ምክንያት በተቃራኒው ፈጣሪያቸውን እየካዱና ስመክርስትናቸውን እየለወጡ ከክርስትና እምነት ውጭ ወደሆኑ አገሮች የሚሰደዱት ስደት በብዙ መከራና ችግር ላይ እየጣላቸውና ሕይወታቸውንም ጭምር እያጡ ስለሆነ በተለይም ለክርስቲያኖቹ ባለፈው ጊዜ በሊቢያ በረሃ እንደተደረገው በሃይማኖታቸው ምክንያት በባዕድ አገር ብዙ ችግር እንዳይደርስባቸው በሃይማኖት አባቶች በመምህራንና በወላጆች በቂ ትምህርት ሊሰጣቸው ይገባል፡፡