አንጋፋው የአዲስ አበባ ሀገረ-ስብከት የ2009 ዓ/ም የሥራ አፈጻጸም ሪፖርቱን ለ36ኛው አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አቀረበ
የ36ኛው አጠቃላይ መንፈሳዊ ጉባኤ ጥቅምት 06/2010 ዓ/ም ቅዱስ ፓትሪያርኩ፡ብጹአን ሊቃነ-ጳጳሳት ፤የየመምሪያውና የድርጅት ኃላፊዎች፡የየአህጉረ-ስብከቶች ስራ አስኪያጆችና ልዑካን እንዲሁም በአዲስ አበባ ሀገረ-ስብከት ስር የሚተዳደሩ አድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎችና ምክትል ሊቃነ መናብርት በተገኙ በት የሚቀርበው ዓመታዊ ሪፖርት የተሰማበትና ስለሚቀጥለው የ2010 በጀት ዓመት እቅድ የተደመጠበት የ3ኛው ቀን ውሎ እንሆ ብለናል፡፡
የሶስተኛው ጠቅላላ መንፈሳዊ ጉባኤ በብጹእ ወቀዱስ አባታችን ጸሎት ከተጀመረ በኋላ በካናዳ ሀገረስብከት ብጹእ አቡነ ማትያስ ትምህርተ ወንጌል ተስጥቷል፡፡ በመቀጠልም የስድስት አህጉረ -ስብከቶች ዓመታዊ የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ከቀረበ በኃላ አናጋፋውና የጠቅላይ ቤተክህነት የጀርባ አጥንት እንደሆነ የሚታወቀው የብፁእ ወቅዱስ ፓትሪያርኩ ልዩ ሀገረ ስብከት የሆነው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በታላቅ ጭብጨባና የሞራል ድጋፍ በመታጀብ የ2009 ዓ/ም ዓመታዊ የሥራ አፋጻጸም ሪፖርቱን በክቡር መምህር ጎይቶም ያይኑ የሀገረ ስብከቱ ዋና ስራ አስኪያጁ አማካኝነት አጠቃላይ ሪፖርቱ ቀርቧል፡፡
በሪፖርቱ እንደተገለጸው የሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት የዓመቱ የስራ አፈጻጸም ዘመን ከሌሎቹ የስራ ዘመናት በተለየ መልኩ ከፍተኛ የሚባል የስራ ክንውን የተፈጸመበት ዘመን ነው፡፡በበጀት ዓመቱ ሃገረ-ስብከቱ ያከናወናቸው ዋና ዋና የሥራና የአገልግሎት ተግባራት መካከል የተወሰኑትን እንመለከታለን፡፡
መልካም አስተዳደርን በተመለከተ፡-በዚህ አገላለጽ መልካም አሰተዳደር ማለት በየትኛውም የቤተክርስቲያኒቱ አገልግሎት ዘርፍ ላይ ለተቀመጡ አገልጋዮች እንዲሁም በሃገረ-ስብከቱ ስር ለሚኖሩ ምእመናን የሚገባውን ክብር በመስጠትና ለሚፈጠሩት ችግሮች አፋጣኝ የመፍትሔ እርምጃ በመስጠት ፍትህን ማስፈን ማለት ነው፡፡አዲስ አበባ ሃገረ ስብከትም በስሩ የሚየስተዳድራቸው ገዳማትና አድባራት በመኖራቸው በእነዚህ አድባራትና ገዳማት የሥራ ኃላፊዎች በሚፈጠራው የአሰራር ክፍተት የተነሳ በርካታ አቤቱታ አቅራቢዎች የሃገረ-ስብከቱን ጽ/ቤት እንደመስከረም ንብ ወረውና አቤቱታ በማሰማት ለጽ/ቤቱ ተጨማሪ ስራና ችግር ሆነው ቆይተው እንደነበር ይታወቃል፡፡ሆኖም ግን በሃገር-ስብከቱ ጠንካራ የአስተዳደር ጉባኤ መሰረት ችግሩ የተፈጠረበት ቦታ ድረስ በመሄድ የችግሩን መንስኤ በማጣራት የችግሩ አቀንቃኝ በሆኑ አካላት ላይ የማያዳግም አስተዳድራዊ እርምጃ ወስዷል ለአድባራትና ለገዳማቱም ከፍተኛ ሰላምና መረጋጋትን አስፍኗል፡፡በመቀጠልም ድጋሚ እንደዚህ ዓይነት ችግሮች እንዳይፈጠሩ የአቅም ግንባታና የአገልጋይነት ስነ-ምግባር ስልጠናዎችን በሚገባ መስጠቱን ገልጧል፡፡ከዚህም ባሻገር ሁሉም አድባራትና ገዳማት በበጀት ዓመቱ መጨረሻ የተጓዙበትን የጉዞ መስመር ወደኋላ መለስ ብለው እንዲመለከቱና እንዲፈትሹ ጠንካራና ደካማ ጎናቸውንም በመገምገም ለቀጣይ የሥራ ዘመን የመፍትሔ አቅጣጫዎችን የሚነድፉበት መድረክም አዘጋጅቷል፡፡ እንደዚህ አይነቱ አስራር ወይም ውይይት በሃገረ-ስብከታችን ብሎም በቤተክርስቲያናችን ከአሁን በፊት በሰፊው ያልታየና ያልተተገበረ ቢሆንም ጽ/ቤታችን ግን በክቡር ስራ አስኪያጁ መምህር ጎይቶኦም ያይኑ ሃሰብ አመንጭነትና መመሪያ ሰጭነት በሰባቱም ክፍለ ከተሞች ከአስተዳዳሪዎች እስከ ዲያቆናት ድረስ የዘለቀ የግምገማና የውይይት ፕሮግራም ተደርጓል፡፡ከዚህም የተነሳ ከበርካታ አስተዳዳደሪዎችና አገልጋዮች እንደሁም በየጊዜው የሀገረ-ስብከቱን የአሰራር ለውጥ በሚከታተሉ ቀናዒ የቤተክርስቲያን ልጆች ምስጋና ለጽ/ቤቱ ተችሮታል፡፡
የፐርሰንት አሰባሰብ ሂደት፡- የፐርስት አሰባሰብ ከአማንያን የአስራት በኩራትና በቤተክርስቲያን ከሚሰበሰቡ ልዩ ልዩ ገቢዎች ሀገረ ስብከቱ የሚገኘው ከመቶ ሃያ ፐርሰት ሲሆን የዚህ የፐርሰት አሰባሰብ ከሌሎች ዓመታት ልዩ የሚያደርገው በሀገረ ስብከቱ የየክፍሉ ኃላፊዎች አስተባባሪነት ሰባቱም ክፍለ ከተሞች በእጅጉ በመድከም ከ1992 ዓ/ም ጀምሮ አስከ 2008 ዓም ያልተከፈሉ አንዳንድ ውዝፍ ፐርሰት በተደረገው እንቅስቃሴ አስደናቂ ውጤት ተገኝቷል፡፡ይኸውም የአድባራቱና የገዳማቱ ዓመታዊ ገቢ ከሚሊዮን ወደ ቢሊዮን የተሸጋገረበትና የሀገረ ስብከቱ ድርሻ በ55 ፐርስት እድገት አሳይቶ 202,304 593.60 መሰብሰብ ተችሏል፡፡ክቡር ስራ አስኪያጁ አበክረው እንደተናገሩት ውዝፍ የሚለው ቃል ስመ አጠራሩ እንዲጠፋና ወደፊትም ከዚህ በተሻለ መልኩ ሃገረ ስብከቱ ማግኘት ያለበትን የፐርሰት ገቢ በወቅቱ እንደሚሰበስብ ቃል በመግባት ሀገረ ስብከቱ ቆርጦ ተነስቷል ብለዋል ፡፡ የበጀት ዓመቱ የፐርሰት አሰባሰብ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር 55,593,805 ልዩነት አምጥቷል ፡፡ለመንበረ ፓትሪያርኩም 35,104,279.42 በማስገባት ከፍተኛ እድገት አስመዝግቧል፡፡ለዚህም ነው ታሪካዊ የበጀት ዓመት የሚል ስያሜ የተሰጠው ፡፡በዐዋጅ ነጋሪ ገጽ 17 በኦዲትና እንስፔክሽን መምሪያ የቀረበው የኦዲት ውጤትና በጠቅላይ ቤተክህት ብጹዕ ዋና ሰራ አስኪያጁ ሪፖርት የተደመጠው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የ2009 ዓ/ም የበጀት ሪፖርት ሳይሆን ከ2007-2008 ዓ/ም መሆኑንና የ2009 ዓ/ም የኦዲት ውጤት ምንም ዓይነት ስህተትም ይሁን ግድፈት ያልተገኘበት በመሆኑ በኦዲትና እንስፔክሽን ቁጥጥር መምሪያው፤ በብጹእ ዋና ስራ አስኪያጁና በሃገረ ስብከቱ ዋና ስራ አስኪያጅ በድጋሚ ተስተባብሎ በጉባኤው ፊት እንዲስተካከል ተደርጓል፡፡
ስልጠናና ዓውደ ጥናት፡-እንኳን በአንድ ተቋም ውስጥ ለሚሰሩ ሰራተኞችና አገልጋዮች ይቅርና በግለሰብ ደረጃም ቢሆን የአመለካከትና የአስተሳሰብን አቅም ከፍ ለማድረግና አዳዲስ ስራዎችን ለመገንዘብ የሚጠቅም ሁነኛ መፍትሔ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ይህንን ሃሳብ በጥልቅ የተረዳው የአዲስ አበባ ሃገረ ስብከት ጽ/ቤት የሃገረ ስብከቱን አሰራር ለማዘመንና ለማስተካከል በገንዘብ አያያዝ ወይም (double entry) የህግ ጉዳዮችን፤የመልካም አስተዳደርንና ኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮን በተመለከተ እና በመሳሰሉት የተለያዩ ርአሰ ጉዳዩች ዙሪያ ለ5 ተከታታይ ቀናት ስልጠናና ዓውደ ጥናትን በሚመለከታቸው አካላት እንዲስጥ አድርጓል፡፡ በዓውደ ጥናቱም መጨረሻ ቀን ብጹእ ወቅዱስ ፓትሪያርኩ እንደዚህ ዓይነት ስልጠናዎችና ዓውደ ጥናቶች መቀጠል እንዳለባቸው አበክረው ተናግረዋል አባታዊ መመሪያም አስተላልፈዋል፡፡
ንብረትንና አጠባበቁ፡- ከአሁን በፊት እንደምናውቀው በርካታ አድባራትና ገዳማት ቋሚና ተንቀሳቃሽ የነበሩ ንብረቶችን በመጠበቅና በመንከባከብ እንብዛም አጥጋቢ አልነበሩም፡፡የዚህም ግዴለሽነት አመለካከት ከሙዳዬ ምጽዋት ያልዘለለ ገቢ እንዳይገኝ አድርጓል ቤተክርስቲያንም በድሏል፡፡በ2009 ዓ/ም የበጀት ዓመት ግን ከአሁን በፊት የነበረውን የቸልተኝነት አሰራር በመቀየር በክቡር ስራ አስኪያጁ መሪነትና የሀገረ ስብከቱ አስተዳደር ጉባኤ አባላት ተባባሪነት የመስክ ጉብኝት በማድረግ አልፎ አልፎም ልዑካንን በመላክ በአንዳንድ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ያለውን የንብረት አጠባበቅና የልማት እንቅስቃሴ ማለትም የቦታና የሱቅ ኪራዮች የወቅቱን ገበያ በተመለከተ እንዲከራዩ የኪራዩን ዘመን ለአንድ ዓመት ብቻ እንዲፈጸምና እንደሁኔታው የሚታደስ እንዲሆንና ግልጽ የሆነ ጨረታ በማውጣት የሀገረ ሰብከቱና የክፍለ ከተማ ተወካዮች በተገኙበት እንዲፈጸም ተደርጓል፡፡ በማያያዝም ከቤተክርስቲያን ጥቅም ይልቅ የግል ጥቅማቸውን የሚያስቀድሙ ጥቅመኞች ላይ የማዳግም አስተዳደራዊ እርምጃ ወስዷል፡፡በተጨማሪም ይዞታነቱ በቤተክርስቲያን እጅ ሆኖ ነገር ግን በካርታና ፕላኑ ላይ ያልተካተተ በርካታ የቤክርስቲያንን ንብረት ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ጋር በመሆን ሀገረ ስብከቱ ለ25 አብያተ ክርስቲያናት መፍትሔ ስጥቷል በሀገረ ስብከቱ ህንጻ ላይ ለሁለት ዓመታት ያክል ተከራይቶ የኪራይ ገንዘብ ሳይከፍ የቆየው የባሮክ ዲያግኖስቲክ ላብራቶሪ በዚሁ በጀተ-ዓመት ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ አድርጓል፡፡
በሰባቱ ክፍላተ ከተሞች የተደረገ ዓመታዊ ውይይት
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በስሩ ሰባት ክፍላተ ከተማ ያሉት ሰፊ ሀገረ ስብከት ሲሆን ከእነርሱ ጋር በመናበብና ያጋጠሙ ችግሮችንም በጋራ በመወያየት ማእከላዊ የፋይናንስ ሥርዓት እንዲዘረጋ የስብከተ ወንጌል አገልግሎት እንዲጠናከር መልካም አስተዳደር በቤተክርስቲያናችን እንዲስፋፋና ሰበካ ጉባኤውም እንዲጠናከር በማድረግ የ2009 ዓ/ም የበጀት ዓመት ለውጥ ያመጣና ለቤተክርስቲያናችንም ሁለንተናዊ እድገት ያስመዘገበ ወቅት መሆኑን ከሪፖርቱ ተደምጧል፡፡
በሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት የተደረገ የሥራ አፈጻጸም ግምገማ፡- በየትኛውም ተቋምና ድርጅታዊ አሰራር በተወሰኑ የጊዜ ክፍልፋዮችና የዓመቱን መጨረሻ የሥራ አፈጻጸምን አስመልክቶ ግምግማ ይደረጋል ፡፡በግምገማው ውስጥ ጠንካራ ጎናቸው ከፍተኛውን ጣሪያ ለነኩ ሰዎች ሽልማት ሲጎናጸፉ ዓመቱን በውጤት አልባነት ላሳለፉት ደግሞ ተግሳጽና ተሻሻል የሚል ተቋማዊ ሃሳብ ይሰነዘርባቸዋል፡፡የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤትም የቤተክርስቲያኒቱ አንጋፋ ተቋም እንደመሆኑ መጠን የሥራ ዘመኑን አስመልክቶ የግምገማ መድረክ አዘጋጅቷል፡፡ በግምገማው ላይ አመርቂ ውጤት ላስመዘገቡ የክፍለ ከተማ ኃላፊዎች ምስጋና ሲቸራቸው በተለያየ መልኩ የተጣለበቸውን አደራ ችላ ያሉትን ደግሞ እንዲያሻሽሉና በትጋት እንዲያገለግሉ ጠንካራ ማሳሰቢያ ተሰጥቷቸዋል፡፡በግምገማው ወቅት ክቡር ሥራ አስኪያጁ እንደተናገሩት ከዕለት ወደ ዕለት የአማንያን ቁጥር እየቀነሰ በመምጣቱና አስጊ በመሆኑ የስብከተ ወንጌል አገልግሎት በእጅጉ ሊስፋፋ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡እንዲሁም ሌሎችና ተመሳሳይ ችግሮችን በማንሳትና በመወያየት ከእልባት ላይ ተደርሷል፡፡
ልዩ ልዩ ክንዋኔዎችን አስመልክቶ
በመብራት መጥፋት የተነሳ በሀገረ ስብከቱ ውስጥ የስራ መቆራረጥ እንዳይከሰትና ከህንጻው ዲዛይን ጋር የሚመጣጠን አውቶማቲክ ድምጽ አልባ ጀኔሬተር ተግዝቷል፡ቤተክርስቲያናችን የገንዘብ አያያዝ ሥርዓቷን ለማዘመንና የባንክ አክስዮን ባለድርሻ እንድትሆን ቅዱስ ፓተሪያርኩና ብጹዓን አባቶች በሰጡት ፈቃድ መስረት ዳሎል በተሰኘው ባንክ የመሰራችነት ቅድሚያውን ቤተክርስቲያን ስለተጋራች የሃገረ-ስብከቱ ጽ/ቤት የ25 ሚሊዮን የአክስዮን ድርሻ በመግዛትና እንዲሁም አድባራቱና ገዳማቱ እንዲሳተፉ ከሚገኛውም የአክስዮን ትርፍ ተቋዳሾች እንዲሆኑ፤ከፍተኛ ጥረት አድርጓል እያደረገም ይገኛል፡፡ከዚህም በተጨማሪ የአገልጋዮችን መብት ለማስከበር ከጡረታ ክፍያ ጋር የተያያዘ ሥርዓት ለመዘርጋት የአዲስ አበባ ሃገረ-ስብከት ጽ/ቤት የጡረታ የአከፋፈል ደንብ በባለሙያ በማስጠናት የጥናቱንም ውጤት ለአድባራትና ገዳማት በማቅረብ የእነርሱን አዎንታዊ ምላሽ ካዳመጠ በኋል በሙሉ ድምጽ የጸደቀውን ይህን የጡረታ አከፋፈል ደንብ በ2010 የበጀት ዓመት በሃገረ ስብከቱ ራሱን የቻለ የባንክ ሂሳብና ዘርፉን የሚያስተባብር የጡረታና ሪከርድ ክፍል ተከፍቶ ወደ ትግበራ ለመግባት በዝግጅት ላይ የሚገኝ መሆኑንም ተገልጸዋል፡፡ የቤተክርስቲያን ተቀዳሚ ተግባር የስብከተ ወንጌል ማስፋፋትና ሰዎችን ወደጌታ ማምጣት ቢሆንም ተጓዳኝ በሆነ መልኩም የተቸገሩትን የመርዳት፡አዳዲስ ለሚቋቋሙም የመቋቋሚያ ድጋፍ የማድረግ መለኮታዊ አደራ እየተወጣች ትገኛለች የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትም የቤተክርስቲያን አካል በመሆኑ ባለፈው የበጀት ዓመት ለደቡብ ኦሞ ሀገረ ስብከት ከፍተኛ የገንዘብና የአገልጋዮች ድጋፍ፡ ለገጠር አብያተ ክርስቲናት አብነት ተማሪዎች የድጎማ ገንዘብና የመሳሰሉትን በመለገስ የቤተክርስቲያንን ሥራ በእጅጉ በመጋራት ላይ ይገኛል ወደፊትም በዚሁ መልክ ይቀጥላል፡፡
በ2010 በጀተ-ዓመት ሊሰሩ የታሰቡ ዋና ዋና የሀገረ ስብከቱ እቅዶች
በ36ኛው አጠቃላይ መንፈሳዊ ጉባኤ ዋዜማ ከህትመት የወጣውንና ለአራተኛ ጊዜ ተሻሽሎ የቀረበውን አዲሱን ቃለ ዐዋዲ አስመልከቶ ግንዛቤ ማበስጨበጫ መስጠት፡በተለያዩ የአገልግሎት ዘርፎች ተሰማርተው ለሚገኙ የሃገረ ስብከቱና የክፍለ ከተማ ሰራተኞች እንዲሁም የአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎችና አገልጋዮች ለሙያው መሻሻል ይጠቅም ዘንድ የአቅም ግንባታ መስጠት፡ለሁሉም አገልጋዮች በሚባል መልኩ የጡረታ ዋስትና ማረጋገጥ፡ የ2010 የቤተክርስቲያናችንን ገቢ ሰላሳ ፐርሰት ማሳደግ ፡ቤተክርስቲያን ከልመናና ከሙዳዬ ምጽዋት ወጥታ የራሷ የሆነ ገቢ ያስፈልጋታልና የገቢ ማስገኛ ሁለገብ ህንጻዎች እንዲፋጠኑ ማድረግና አዳዲስ የልማት አውታሮችን መዘረጋት በድጋፍ ረገድም ለገጠር አብያተ ክርስቲያናት የቤተክርስቲያን ትምህርት ምንጭ እንዳይደርቅ 4 ሚሊዮን ብር ለመርዳት ዝግጅት ላይ መሆኑና እንዲሁም በቤተክርስቲያናችን ውስጥ ለሚደረጋው የሰንበቴ ማህበር የመተዳደሪያ ደንብ ማዘጋጀትና ልዩ ትኩረት ለሚስፈልጋቸው ለበጀት ዓመቱ የስራ ሂደቶች ወሳኝ እቅድ እንደሚያስልጋቸው በመግለጽና በሃገረ ስብከቱ ከፍተኛውን ድረሻ ከሚወስዱት ብጹእ ወቅዱስ ፓትርያሪኩ እስከ አድባራትና ገዳማት ያሉትን የሥራ ኃላፊዎቸና ባለድረሻ አካላት ለተሳካው የበጀት ዓመት በእግዚአብሔር ስም በማመስገንና በሚቀጥለው የበጀት ዓመት የቅዱስነታቸው ጸሎትና አባታዊ መመሪያ በመቀበል በጋራ ለመስራት ጥሪያቸውን አቅርበው ሪፖርታቸውን አጠናቀዋል፡፡
በአጠቃላይ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክርስቲያን ካሏት አህጉረ ስብከቶች ስልጠናንና ዓውደ ጥናትን፤የንብረት አያያዝና ጥበቃን፡መልካም አስተዳደር ማስፈንን፡የፐርስት አሰባሰብን፤የዓመቱ የሥራ አፈጻጸም አስመልክቶ ዓመታዊ የሥራ ግምገማና የሰው ሃብት አስተዳደር ክንዋኔን በተመለከተ የተጣለበትን መንፈሳዊና ሓዋርያዊ እንዲሁም ማህበራዊ ኃላፊነት በብቃት በመወጣት የአንበሳውን ድርሻ የያዘ አንጋፋ ሃገረ ስብከት ነው፡፡በተጨማሪም በዓመታዊ ሪፖርት ላይ የተገለጸው እያንዳንዱ የሥራ አፈጻጸም ክናዋኔና የተመዘገቡ ውጤቶች በወረቀት ላይ ብቻ የተቀመጠ ሳይሆን በተግባር የሚታይ ሊለካና ሊሰፈር የሚችል በእውነትና በታማኝነት ላይ የተመሰረተ ዓመታዊ የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ነው፡፡በመሆኑም ይህንን በአይኑ ያያ ማንኛውም የቤተክርስቲያናችን ባለድርሻ አካላት አይዞህ በርታ የሚል የማበረታቻ የሞራል ድጋፍና ክፍተቶችን ሊያሳይ የሚችል ጠቃሚ ሃሳብ ይዞ በመምጣትና ከሃገረ ስብከታችን ጎን እንዲሰለፍና የያዝነውን በጀት ዓመት የሥኬትና የውጤት ይሆን ዘንድ በጸሎት ትረዱን ዘንድ ምኞታችን ነው፡፡
ማሳሰቢያ
በአዋጅ ነጋሪ መጽሔት 10ኛ ዓመት ቁ 13 ገጽ17 ላይ ከኦዲትና ኢንስፔክሽን መምሪየ በመነሳት የቀረበውን ጹሑፍ በሚመለከት
1. የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ዋና ስራ አስኪያጁና ቁጥጥር መምሪያው በአዋጅ ነጋሪ መጽሔት 10ኛ ዓመት ቁ 13 ገጽ 17 ላይ የቀረበውን ሪፖርት ሁሉ ስህተት መሆኑን በገለፁት መሠረት ዘገባው የ2008 በጀት ዓመት እንጂ የ2009 በጀት ዓመት አለመሆኑ የ2008 በጀት ዓመት ኦዲት ሪፖርትም አስከአሁን ወደ ሀረ ስብከታችን ያልመጣ መሆኑ እንዲታወቅ
2. ንብረትነቱ የሀገረ ስብከቱ የሆነ በሀገረ ስብከቱ ሕንፃ ሥር የሚገኘውን ቤት የተከራየ ባሮክ ዲያልኖስቲካል ላቮራቶሪ ከህዳር ወር 2007 ዓ.ም እስከ ህዳር ወር 2008 ዓ.ም የኪራይ የውል ስምምነት ፈጽሞ የ3 ወር ከከፈለ በኋላ አቋርጦና ተጨማሪ የውል ዕድል አግኝቶ የ2 ዓመት ከሁለት ወራት ውዝፍ ኪራይ ብር 476,471.75 ባለመክፈሉ የሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት በየካቲት ወር 2008 ዓ.ም ውሉን በማቋረጥና ቤቱን በማሸግ በመደበኛ ፍ/ቤት ክስ አቅርቦ የነበረ ቢሆንም ከክርክር ይልቅ ከድርጅቱ ባለቤት ጋር በውይይት መጨረስ እንደሚሻል በማመን እልህ አስጨራሽ ውይይትና ክርክር ተደርጎ የነበረበትን ውዝፍ ኪራይ በሙሉ መጽሔቱ ላይ እንደተገለጸው የአንድ ዓመት ከ2 ወር እና ገንዘቡም መጽሔቱ ላይ እንደተገለጸው ሳይሆን የሁለት ዓመት ከ2 ወር ብር 476,471.75 ስለነበር በአግባቡ እንዲከፍል ተደርጎ በወቅቱ የቤተ ክርስቲያኒቱ ልሳን በሆነው ዜና ቤተ ክርስቲያን ጋዜጣ 63ኛ ዓመት ቁጥር 78 ጥርና የካቲት 2009 ዓ.ም እትም ላይ በሰፊው የተዘገበና በሪፖርትም የተገለጸ በመሆኑ በመጽሔቱ መካተት ከነበረበትም ይህ እውነታ ሊወጣ የገባ ነበር፡፡
በአጠቃላይ ከሁለት ዓመታት በፊት የተከፈለውን አበል እና መፍትሔ የተሰጠውን የቤት ኪራይ የ2009 ዓ.ም ድርጊት አስመስሎ ማቅረብ እጅግ አሳዛኝ በመሆኑ ለቤተ ክርስቲያን ታስቦ ከሆነም እውነቱን በማረጋገጥ አጥፊውን መቅጣት ቢቻል ሚዛናዊ ይሆን ነበር፤በመሆኑም ምንም እንኳን ሪፖርቱ እስከአሁን ባይደርሰንም በሪፖርቱ መሠረት እንዲፈጸምና እውነቱ ከላይ የገለጽነው መሆኑንና አሁን ያለውን አመራር የማይመለከት መሆኑ እንዲታረምልንና አንባብያን በዚህ መልኩ እንዲረዱልን እናሳስባለን፡፡