በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን 36ኛው ዓመታዊ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ተጀመረ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የመንበረ ፓትሪያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ በየዓመቱ በጥቅምት ወር በሚካሔደው አጠቃላይ ጉባኤ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የሚጠቅሙ መሠረታዊ ጉዳዮች ይዳሰሳሉ፡፡ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤትን ጨምሮ፣ በመላው ዓለም የሚገኙ አህጉረ ስብከት፣ የድርጅቶችና የመንፈሳዊያን ኮሌጆች ሪፖርቶች ቀርበው ይደመጣሉ፡፡በዘንድሮ ዓመትም አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ባስመዘገበው ልዩ እና ከፍተኛ የሥራ ውጤት ታጅቦ ዓመታዊ ስብሰባው ተጀምሯል፡፡ በስብሰባው ላይ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ፤ ብፁዓን ሊቃነ-ጳጳሳት ፤ የአህጉረ ስብከት ልዑካን ፤ የመምሪያዎችና የድርጅት ኃላፊዎች፤ የአዲስ አበባ ሃገረ-ስብከት ሥራ -አስኪያጅ ፤ የአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎችና ምክትል የሰበካ ጉባኤ ሊቃነ መናብርት ፤በድምሩ 794 ታዳሚዎች በተገኙበት በጠቅላይ ቤተ ክህነት የስብከተ ወንጌል አዳራሽ በብጹእ ወቅዱስ ፓትሪያርኩ አባታዊ ቡራኬና ጸሎት በይፋ ተከፍቷል፡፡የአጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ በቅዱስ ፓትርያሪኩ ርእሰ መንበርነትና በብፁእ ዋና ስራ- አስኪያጁ ምክትል ሰብሳቢነት የሚመራው ዓመታዊ ዓመታዊ ጉባኤው ሁሉም አህገረ ስብከቶችና ይልማት ድርጅቶች አጠቃላይ የስራ አፈጻጸም ክንውኖችና ያስመዘገቡትን የስራ ፍሬ እንዲሁም በስራ ላይ ያጋጠሟቸውን ተግዳሮቶችና የወሰዱትን የመፍትሔ እርምጃ የሚያሰሙበት የመወያያ መንፈሳዊ ጉባኤ ነው፡፡ የኢ/ኦ/ተ/ ቤተ-ክርስቲያን የራሷ የሆነ መዋቅራዊ አደረጃጀቷን ከዘረጋችበትና መተዳደሪያ ደንብና መመሪያዎቿን በስራ ላይ ካዋለችበት ከ3ኛው ፓትሪያርክ ከአቡነ ተክለሃይማኖት የፕትርክና ዘመን ጀምሮ መደበኛ በሆነ መልኩ ሲካሄድ ቆይቶ የዘንድሮው ማለትም የ2010 ዓ/ም 36ኛው ዓመታዊ ዓብይ ጉባኤ መሆኑን ከቤተክርስቲያን የታሪክ መዛግብት እንረዳለን፡፡ በጉባኤው መክፈቻ ላይ እንደተገለጸው የዘንድሮው አጠቃላይ ሰበካ መንፈሰዊ ጉባኤ ከሌሎቹ ልዩ የሚደርጉት ሁለት ዋና ዋና ነጥቦችን ለማስቀመጥ ተሞክሯል፡፡ እነዚህም፡-
1.በሐምሌ 9/2009 ዓ/ም የቤተክርስቲያንን ሐዋርያዊ ተልእኮ ለማፋጠን በፓትሪያርኩ አንብሮተ እድ የተሾሙት 15-ሊቃነ- ጳጳሳት በጉባኤው መገኘታቸውና
2.በ2004 ዓ/ም የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ተሻሽሎ እንዲቀርብ ባጸደቀው መሰረት የቤተክርስቲያናችን ባለ 66 አንቀጽ ቃለ-ዓዋዲ ወደ 67 አንቀጽ ከፍ በማለትና በ120 ገጾች በመጠቃለል ለ4ኛ ጊዜ ተሻሽሎና ተስተካክሎ ለጉባኤው የቀረበበት ወቅት በመሆኑ ጉባኤው ልዩ እንደሚያደርገው ተገልጿል፡፡
በመቀጠልም በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥር በሚተዳደረው የማህደረ ስብሐት ልደታ ለማርያም ወጣት ሰንበት ተማሪዎች “ኢይትዓጸው አናቅጽኪ ክቡራት ዕንቁ መሠረትኪ ሰናይት ሰላማዊት ቤተክርስቲያን “በሚል የቤተክርስቲያንን ቀጣይ ህልውና ላይ ተመስርተው የታዳሚውን ልብ በሚነካ መልኩ ያሬዳዊ ዝማሬ አቅርበዋል፡፡ ከቅዱስነታቸውም ቡራኬ ተቀብለዋል ፡፡ በዚሁ ጉባኤ ላይ ቅዱስ ፓትርያሪኩ “ጌታው በቤተሰቦቹ ላይ የሚሾመው ታማኝና መልካም አገልጋይ ማነው ማቴ 24 ፤45 በሚል ርእስ ባስተላለፉት አባታዊ መልእክት በጌታ በቤተሰቡና በአገልጋዩ መካከል ያለው ግንኙነት አስተማማኝና እጅግ በጣም ጤናማ ሆኖ እንዲቀጥል የጌታ ጽኑ ፍላጎት ነው፡፡ ጌታ ጥንቃቄ ማድረግ የፈለገው አገልጋዩን መሾም ላይ ነው፤ ምክንያቱም ለቤተሰቡ የተቃና እድገትና ኑሮ ወሳኝ ሚና የሚጫወተው አገልጋዩ ነውና……ይህ አማናዊ የሆነ የወልደ እግዚአብሔር ክርስቶስ ትምህርት መልካምና ታማኝ የሆኑ ካህናት ምእመናንን በመመገብ ረገድ ያላቸው ኃላፊነት ምን ያክል ታላቅ ጥንቃቄ የሚያስፈልገው እንደሆነ የሚያሳይ ነው፤ እንደ ጌታችን አስተምህሮ የምእመናን ህይወት መቃናትና አለመቃናት በካህናት እጅ የወደቀ ነው፤ በማያያዝም ልዩ ልዩ የቁጥር ዘገባዎችና መረጃዎች እንደሚያሳዩት በአሁኑ ጊዜ በመካከለኛውና በደቡብ የሃገራችን ክፍል የሚገኙ ምእመናን ምግብ /ቃለ-እግዚአብሔር/ ባለማግኘታቸው በተኩላዎች በከፍተኛ ደረጃ እየተነጠቁ መሆናቸውን መገንዘብ እንደሚገባ የጠቆሙት ቅዱስነታቸው እንደዚህ ያለው ክስተት ገዝፎ በሚታይበት በአሁኑ ወቅት የካህናት አገልግሎት በታማኝነትና በመልካም ሁኔታ እየተከናወነ ነው ብለን የምናስብ ከሆነ ሌላውን ሳይሆን ራስን ማታለል ነው የሚሆነው ብለዋል፡፡በተጨማሪም ሁላችንም ውሉደ ክህነት ጌታችን በቤተሰቡ ላይ የሾመን ነንና ከተሰጡን መንጎች አንድ ስንኳ እንዳይጠፋ ሥርዓተ-ቤተክርስቲያንን ማዕከል አድርገን በተሳሳተ መንገድ እየተጓዙ ቤተክርስቲያንን ለመከፋፈል የሚከጅሉ ልጆቻችንን አንድ ላይ ሆነን ተው፤ንስሐ ግቡ፤ታዘዙ፤የቤተክርስቲያንን አንድነትና ሥርዓት ጠብቃችሁ በአበው እግር ዋሉ እንበላቸው በማለት አባታዊ መመሪያ የሰጡት ቅዱስነታቸው ይህ ሲሆን መልካምና ታማኝ እረኛ መሆናችንን እናረጋግጣለን በማለት ገልጸዋል “፡፡ ከቅዱስነታቸው መልእክት እንደምንረዳው በእግዚአብሔር፤በአገልጋዩና በቤተሰቡ መካከል ያለው የሶስትዮሽ መስተጋብራዊ ግንኙነት ጤናማ እንዲሆን ከፍተኛ ጥናቃቄ የሚደረገው የአገልገይ አመራረጥ ሂደት ላይ ነው፡፡አገልጋዩ ጤናማ ከሆነ የጌታ ቤተሰብ ጤናማ መንፈሳዊ ህይወትና ጤናማ ማህበራዊ ግንኙነት ይኖረዋል፤የአገልጋዩ ስነ-ምግባር በተቃራኒው ከሆናና በቤተክርስቲያን ያልተስተካከለ የአገልጋይነት ሥነ-ምግባር ካለ የመሪውና የተመሪው፤የጌታና የቤተሰቡ ግንኙነት በጣም የቀዘቀዘ፤ለመበጠስም የቀረበ መሆኑ የማያጠያይቅ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ አሁን ባለንበት ዘመን የቤተክርስቲያንን የመገለጥ መሰረታዊ ዓላማ በአግባቡ ለመረዳትና ተልእኮውንም ለማስቀጠል ኢየሱስ ክርስቶስ ለሐዋርያት የስጠውን መለኮታዊ ኃላፊነት በማስታወስና ለቃሉም በመገዛት ታማኝ አገልጋዮች ሆነን ካልተገኘን መክሊቱን እንደቀበረው ባላደራ ተወቃሾች መሆናችን አይቀሬ ነው፡፡ይልቁንም ከተወቃሽነት ለመዳንና ከጌታ የአገልግሎት ሽልማትና ምስጋናን ለማግኘት ታማኝ አገልጋይ ሆኖ መገኘት አማራጭ የሌለው ሁነኛ መፍትሔ ነው፡፡ ጠቅለል ባለ መልኩ ከዚህ መልእክት ታማኝ አገልጋይ ማለት ምን ማለት እንደሆነ፤የታማኝ አገልጋይና ታማኝነቱን ያጎደለ አገልጋይ መገለጫዊ ባህርያት ምን ምን መሆናቸውን በሚገባ እንገነዘባለን፡፡
ከቅዱስ ፓትሪያርኩ መልእክትና አባታዊ ትምህርት በማስከተልም የጠቅላይ ቤተክህነት ስራ አስኪያጅ ብፁእ አቡነ ዲዮስቆሮስ ቤተክርስቲያን በተሰጣት አደራ መሰረት በ2009 ዓ/ም ያከናወነቻቸውን ዋና ዋና ተግባራት ማለትም የጠቅላይ ቤተክህነት የመምሪያዎች፤ የድርጅቶችና የቤተክርስቲያኒቱ ተልእኮ ማስፈጸሚያ መንፈሳዊ ኮሌጆች ያስመዘገቡትን ጠንካራና ደካማ ጎን በአጠቃላይ ሪፖርት በማካተትና የ2010 ዓ/ም በጀት ዓመት አቅድ በማሰማት ከስዓት በፊት የነበረው የስብሰባ መርሃ ግብር ተጠናቋል፡፡ከምሳ ስዓት በኋላ በነበረው ቆይታም የአክሱም፤የሲዳማ፡የሰሜን ጎንደር፡ የሰሜን ሽዋ ሰላሌ፡ የጅማ ዞን፡የመቀሌ፡የኢሊባቡር፡የድሬዳዋ፡የጋሞጎፋ፡የሰሜን-ወሎ፡የባሌና የምስራቅ ሐረርጌ በድምሩ አስራ ሁለት አህጉረ -ስብከቶች ተራቸውን መሰረት በማድረግ የ2009 ዓ/ም ዓመታዊ ሪፖርትና በሚቀጥለው የሥራ ዘመን የቅዱስ ሲኖዶስን መመሪያ በመቀበልና በመተግበር ሊያከናውኑት ያቀዱትን እቅድ በማሰማት የመጀመሪያው ቀን የጉባኤ መርሃ ግብር በዚህ መልኩ ተጠናቋል፡፡በሚቀጥሉት የጉባኤ ቀናት የሚከናወኑትን ክንውኖችና ውይይቶች እየተከታተልን የምንዘግብ መሆኑን ከወዲሁ እናስታውቃለን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር