ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ በተለምዶ 22 እየተባለ በሚጠራው አካባቢ በመገንባት ላይ ያለውን የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሁለገብ ሕንጻ ጎበኙ!!

0808

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት በተለምዶ 22 ሁለት እየተባለ በሚጠራው አካባቢና ጎላጎል ሕንጻ ጎን እየተገነባ የሚገኘውን የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሁለገብ የልማት ሕንጻ አርብ ሰኔ 2 ቀን 2009 ዓ.ም ከቦታው ድረስ ተገኝተው ጎብኝተዋል፡፡
የጉብኝቱ መርሐ ግብር በተካሄደበት በዚሁ ዕለት ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መምህር ጎይቶኦም ያይኑ የተገኙ ሲሆን የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞችም ቀድመው ከቦታው ድረስ በመገኘት ለቅዱስነታቸው፣ ለብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትና ለሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ለመምህር ጎይቶኦም ያይኑ ደማቅ አቀባበር አድርገውላቸዋል፡፡
የሕንጻውን የግንባታ ሥራ በባለሙያነት የሚመሩት ባለሙያዎች በጉብኝቱ ወቅት እንዳብራሩት የሕንጻው ግንባታ ሥራ ከተጀመረ የ9 ዓመት እድሜ ያለው ቢሆንም ነገር ግን ቀደም ሲል የግንባታው ሥራ የመዋቅር ችግሮች፣ የጎደሉ ምሰሶዎችና አግዳሚዎች የነበሩበት ሆኖ በመገኘቱ ክለሳ (ማስተካከያ) የተደረገበት ስለሆነ አሁን የሕንጻው ግንባታ በተመቻቸ መዋቅር ላይ ይገኛል፡፡  በባለሙያዎቹ እንደተብራራው የዲዛይን ክለሳ ሥራም ተከናውኗል፡፡ የግንባታው ሥራው እየተፋጠነ የሚገኘው ይህ ባለ 6 ፎቅ ዘመናዊና ግዙፍ ሕንጻ በውስጡ ዘመናዊ ቢሮዎች፣ የመሰብሰቢያ አዳራሽ እና ሌሎችም የገበያ ማዕከል ያካተተ ነው፡፡

0817

የካቴድራሉ ዋና ጸሐፊ መምህር ሰሎሞን በቀለ ባቀረቡት በጽሑፍ የተደገፈ ሪፖርት ላይ እንደተገለጸው የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ቦታ የቤተ ክርስቲያኑ ታላቅ ባለውለታ ከነበሩት በኲረ ምዕመናን ከበደ ተካልኝ በ1996 ዓ.ም በስጦታ የተገኘ ሲሆን የቦታው አጠቃላይ ስፋት በካርታው ላይ እንደሚታየው 1636 ካሬ ሜትር ስፋት ያለው እና አሁን በግንባታ ላይ ያለው ሕንጻም የዲዛይን ሥራውን ከሠራው ኤምጂኤም ኮንሰልት እንደተረዳነውና ፕላኑም እንደሚያሳየው ሕንጻው ያረፈበት ቦታ 1080 ካ.ሜ ሲሆን ቀደም ሲል በ1999 ዓ.ም የነበረው የሰበካ ጉባዔ አስተዳደርና የልማት ኮሚቴ የሕንጻ ግንባታውን ለማስጀመር ኤምጂኤም ኮንሰልት በተባለው አማካሪ ድርጅት የከተማውን ማስተር ፕላን መሠረት ባደረገ መልኩ የዲዛይን ሥራውን በማስጠናት የሕንጻው ከፍታ ቤዝመንት፣ ምድር ቤትና ባለ አራት ፎቅ ሕንጻ ለማስገንባት የግንባታ ፈቃድ ከግንባታ ቁጥጥርና ባለሥልጣን በማስፈቀድ በ2000 ዓ.ም ኃይለ ልዑል ተክለ ማርያም ከተባለው የሕንጻ ግንባታ ድርጅት ጋር የግንባታ ውል እንዲሁም ካማካሪ ድርጅት ጋር ደግሞ የሕንጻ ቁጥጥርና የማማከር ሥራውን ውል በመፈጸም የግንባታ ሥራው ተጀምሮ ሣለ የሕንጻው ተቆጣጣሪ መሐንዲሱ ሥራውን በተገቢው ሁኔታ  ባለመቆጣጠሩና የተሰጠውን ኃላፊነት በአግባቡ ባለመወጣቱ እንዲሁም የግንባታ ሥራው በአግባቡ እየተሠራ ባለመሆኑና በተጨማሪ በኮንስትራክሽን ድርጅቱ የሚጠየቀው ተገቢ ያልሆነ የገንዘብ ክፍያ ጥያቄ በካቴድራሉ የምሐንድስና ቴክኒክ ባለሞያዎች እንዲጣራ ተደርገጎ የግንባታ ሥራውም ሆነ የተጠየቀው ክፍያ ትክክል አለመሆኑን በቴክኒክ ኮሚቴው አባላት ተጣርቶ በመቅረቡ ከሕንጻ ተቋራጩ ድርጅት ጋር ከፍተኛ የሆነ ግጭት ተፈጥሮ ከ2004 እስከ 2007 ዓ.ም ጥር ወር ድረስ ሥራው ተቋርጦ ጉዳዩ ወደ ፍርድ ቤት አምርቶና ውሳኔ አግኝቶ ቀደም ሲል የዲዛይን ሥራውን ከሠራው ድርጅት ጋር ውል በመፈጸም በብፁዕ ወቅዱስ አባታችን በተሠጠው መመሪያ ተግባራዊ ለማድረግ ከዚሁ ድርጅት ጋር በመመካከር በፊት የተሠራው የሕንፃው ዲዛይን ለዕንግዳ ማረፊያ (ገስት ሀውስ) አገልግሎት መዋሉ ቀርቶ ለገበያ ማዕከልና ተያያዥ ሥራዎች እንዲውል በጠየቅነው መሠረት አማካሪ ድርጅቱ የዲዛይን ክለሳ በማድረግ ቀደም ሲል የነበረው አገልግሎት ተቀይሮ እንዲሁም አምስት ፎቅ የነበረው ወደ ስድስት ከፍ ብሎ ተሠርቶ ይህንኑ ዲዛይን ለግንባታ ፈቃድና ክትትል ባለሥልጣን ቀርቦ በተሠራው ዲዛይን መሠረት ግንባታው እንዲቀጥል በ2005 ዓ.ም ፈቃድ ተሠጥቶ የሕንጻ ግንባታውን እንደገና ለማስቀጠል የሀገሪቱን ብሔራዊ የጨረታ ሕግ በመከተል ግልጽ ጨረታ በማውጣትና በማወዳደር ጨረታውን ካሸነፈው ባማኮን ኢንጅነሪንግ ከተባለው ሥራ ተቋራጭ ጋር ህጋዊ የኮንስትራክሽን ውል ስምምነት በ2007 ዓ.ም የስትራክቸራል ሥራውን ማለትም ቦሎኬት ደርድሮ፣ ልስን ለስኖ፣ የመብራትና የውሃ እንዲሁም ተያያዥ ሥራዎችን ሠርቶ ሊያስረክብ ከ31,000,000.00 (ሰላሳ አንድ ሚሊዮን ብር) በላይ ውል በመፈጸም ወደ ሥራ የተገባ ቢሆንም አሁን ሥራውን እየሠራ ያለው ባማኮን ኢንጅነሪንግ የግንባታ ሥራውን ለመጀመር የኮንስትራክሽን እና የብረት ጥንካሬው ሳይፈተሽ (ቴስት ሳይደረግ) ሥራ እንደማይጀመር በመግለጹ ይኸው በድርጅቱ የቀረበው ጥያቄ በአማካሪ መሐንዲሱና በካቴድራሉ የቴክኒክ ባለሞያዎች የተደገፈ በመሆኑ የፍተሻ ተግባሩ በመንግሥትና ግል ድርጅቶች ተፈፅሞ ውጤቱ እንደሚያሳየው ከመሠረት ጀምሮ ከፕላን ትዕዛዝና ዝርዝር ሥራ ውጪ የኮንክሪት ሥራዎቹ በፕላኑ መሠረት በትክክል ባለመሠራታቸው ምክንያት በአማካሪው ድርጅት በኩል እንደገና የዳሰሳ ጥናት ተደርጎ ከመሠረት (ከፉቲንግ ፓድ) ጀምሮ እስከ ሁለተኛ ፎቅ ድረስ ማጠናከሪያ ሥራ የተሠራ ሲሆን ለዚህም በተጨማሪ ሥራ ምክንያት የካቴድራሉ ሰበካ ጉባዔ ጽ/ቤት ለተጨማሪ ወጪ የተዳረገ ሲሆን በአጠቃላይ ይህንን የተጨማሪ ክፍያ ጨምሮ የሕንጻ ግንባታው ሥራ እስከ አሁን ድረስ ብር 20,000,000 (ሃያ ሚሊዮን ብር) በላይ ወጪ ተደርጓል በማለት ገልጸዋል፡፡
በመጨረሻም ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን ባስተላለፉት አባታዊ መመሪያና መልእክት ሕንጻውን ስንመለከተው ከሰማነው በላይ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡ በእጅጉም ተደስተናል፡፡ የተደረገውም የማሻሻያ ሥራ ተገቢ ነው የሥራው አስተማማኝነት እየተመለከትን የሚገባውን ሁሉ እየተመካከርን ይፈጸማል፡፡ ለዚህ ሕንጻ ግንባታ እንዲውል ቦታውን በስጦታ ያበረከቱት ግለሰብ እግዚአብሔር አምላክ ነፍሳቸውን በዓለመ መንግሥተ ሰማያት እንዲያሳርፍልን እንጸልያለን፡፡ የሕንጻውንም ሥራ በሙያ የሚከታተሉትን ባለሙያዎች ለሥራው ጥራት የሚያደርጉትን አስተዋጽኦ እያበረታታን የሕንጻው ግንባታው በታቀደበት ጊዜ እንዲያልቅ ሁሉም የበኩልን አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ይገባል በማለት አባታዊ መመሪያና መልእክት አስተላልፈዋል፡፡