የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ለገዳማትና አድባራት የዕለት ገንዘብ ስብሳቢና ገንዘብ ያዥ በገንዘብ አያያዝ ላይ ሥልጠና መስጠት ጀመረ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በርእሰ ከተማው በሚገኙ ገዳማትና አድባራት ለተመደቡ ዋና ገንዘብ ያዥና የዕለት ገንዘብ ሰብሳቢዎች በገንዘብ ገቢና ወጭ አያያዝና አመዘገብ ዙሪያ ለ15 ቀናት ያህል የሚቆይ የሙያ ማሻሻያ ሥልጠና እየተሰጣቸው ሲሆን የስልጠናው ሂደትም በቃል/ በቲኦሪና /በተግባር (በኮምፒውተር በታገዘ) እንደዚሁም በቡድን እየተመደቡ የጋራ ውይይት በማድረግና ከዚያም አስፈላጊውን ጥያቄ በመጠየቅና ሐሳብም በመስጠት ስልጠናውን በተሳካ ሁኔታ እየተከታተሉት ይገኛሉ፡፡
የሰልጣኞች ቁጥር ብዛትም 340 ይደርሳሉ፤ ሰልጣኞቹ ከሰባቱም ክፍላተ ከተሞች የተውጣጡ ሲሆን ከአንድ ገዳም ወይም ደብር ሁለት ሰልጣኞች ተመድበዋል፤ በሰባቱ ክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነትም የተመደቡ ገንዘብ ያዦች የስልጠናው ተሳታፊዎች ሆነዋል፡፡ ሊቀ ተጉኃን ገብረ መስቀል ድራር የሀገረ ስብከቱ የቁጥጥር ዋና ኃላፊ የስልጠናውን ሂደት አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ ሰልጣኞቹ ከዘመኑ የሒሳብ አሠራር ጋር በማነፃፀር የሒሳቡን አሠራር እንዴት አድርገው ማሳለፍና መመዝገብ እና ሪፖርት ማድረግ እንዳለባቸው በተመለከተ የቲኦሪና የተግባር ሥልጠና እንዲወስዱ ለማድረግ ሥልጠናው ግንቦት 9 ቀን 2009 ዓ.ም ተጀምሮ በተገቢው ሁኔታ እየተካሄደ ይገኛል፡፡ ሥልጠናውን የሚሰጡት ሙያተኞች ሀገረ ስበከቱ ለዚሁ ለሥልጠና ሥራ ባስቀመጠው የሒሳብ ባለሙያና በተቋም ደረጃ በሚጋበዝ ባለሙያ ነው፡፡ ቀደም ሲል በሁለትና በሦስት ዙር የገዳማቱና የአድባራቱ የሒሳብና የቁጥጥር ሠራተኞች ስልጠና እንዲሰጣቸው ተደርጎ በተገቢና በተሳካ ሁኔታ ስልጠናው ተካሂዷል፡፡ በተሰጠውም ሥልጠና መሠረት ወደ ሥራ የተገባበት ሁኔታ አለ፡፡
ለዚሁም አጋዥ እንዲሆን ለሁሉም ገዳማትና አድባራት የፋይናንስ አሠራርንና አመዘጋገብን በሚመለከት ሥልጠናው ተሰጥቷል፡፡ የኦዲትና ቁጥጥር ማንዋልም ለሁሉም ገዳማትና አድባራት ተሠራጭቷል፡፡
የንብረትና የገንዘብ ሞዴላ ሞዴሎችን ከዘመናዊ የሒሳብ አሠራር ጋር እንዲጣጣሙ ተደርጎ በአዲስ መልክ አንጋፋ በሆነው የቤተ ክርስቲያናችን ማተሚያ ቤት ትንሣኤ ዘጉባኤ አሳትመን ለሁሉም ገዳማትና አድባራት እያሰራጨን እንገኛለን፡፡ ይህም በ2009 ዓ.ም የበጀት ዓመት በከፊል ወደትግበራ እየገባን ነው ያለነው፡፡
እንደ ሀገረ ስብከታችን እቅድና ፕሮግራም ከ2010 ዓ.ም የበጀት ዓመት ጀምሮ በሁሉም ገዳማትና አድባራት ዘመናዊ የሒሳብ አሠራር ይገባል ብለን እቅድ ይዘናል፡፡
ሥልጠናውም በተከታታይና በተፋጠነ መልኩ የሚሰጠው የሒሳብ፣ የቁጥጥርና የገንዘብ ያዥ ሠራተኞች ለእቅዱ ተፈጻሚነት ቀዳሚ ስለሆኑ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን የሁሉም አስተማሪና መካሪ፣ በዘመናዊ አሠራርም ቀዳማዊት እንደመሆንዋ መጠን አሁንም እንደ ጥንታዊነቷና እንደ ታሪካዊነቷ ታሪኳ ተጠብቆ ሥራዎችን ለመሥራት፣ የለውጥ አገልጋዩም ሆነ ተገልጋዩም ባንድነት በመሰለፍ ለውጡን ባጭር ጊዜ ለማየት እንድንችል ሁሉም የእኔ ነው፣ ይመለከተኛል በማለት ሥራው በዘመናዊ እና በሠለጠነ መልኩ እንዲከናወን ማድረግ ይገባል፡፡
አቶ ገብረ ሕይወት አስገዶም የሀገረ ስብከቱ የሒሳብና በጀት ዋና ክፍል ኃላፊ በበኩላቸው በሰጡት ማብራሪያ በዋናነት የሥልጠናው ተጠቃሚ መሆን የሚገባቸው የእለት ገንዘብ ሰብሳቢዎችና ገንዘብ ያዦች ናቸው፡፡ ምክንያቱም በመጀመሪያ ከምዕመናን ጋር ግንኙነት ያላቸው እና ንብረትም ሆነ ገንዘብ የሚሰበስቡ እነርሱ ናቸው፡፡
ይሁን እንጂ ቀደም ብሎ በሀገረ ስብከቱ በተያዘው መርሐ ግብር መሠረት የገዳማቱ የሒሳብ እና የቁጥጥር ሠራተኞች ስለሰለጠኑ በዚያው ለመቀጠል ታስቦ እንጂ በመጀመሪያ መሰልጠን የሚገባቸው የእለት ገንዘብ ሰብሳቢዎችና ገንዘብ ያዦች ነበሩ፡፡
ስለዚህ የእለት ገንዘብ ሰብሳቢዎችና ገንዘብ ያዦች ሥልጠና መውሰዳቸው ተገቢ በመሆኑ ነው አሁን መርሐግብሩ እየተካሄደ ያለው፡፡ ከዚህ በፊት በነበረው የገንዘብ አሰባሰብና አያያዝ ሁኔታ ችግሮች አልተከሠቱም፡፡ ነገር ግን ዓለምን የዋጀውን የሒሳብ አሠራር ግልፅነት እና ተጠያቂነት እንዲኖረው ሒሳቡን ለማዘመን ካልሆነ በስተቀር ቀደም ሲል የነበረው የሒሳብ አሠራርና የገንዘብ አሰባሰብ አባቶቻችን ያቆዩልን አሠራር ከዘመኑ ጋር የሚሄድ ባለመሆኑ እንጂ የሥራ ችግር ኖሮበት አይደለም ወደዚህ አሠራር የመጣነው፡፡ በ2008 ዓ.ም የበጀት ዓመት ሥልጠና ተካሂዷል፡፡ 2009 ዓ.ም የበጀት ዓመትም ከሠላሳ በላይ የገዳማትና አድባራት የሒሳብ ሠራተኞች ወደዘመናዊው ሥራ ገብተው እየሠሩ ይገኛሉ፡፡
ኦዲቱም የሚካሄደው በዘመናዊው የሒሳብ አሠራር መሠረት ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በተሰጠው ስልጠና መቶ በመቶ ለውጡ መጥቷል ባይባልም በተወሰነ ሂደት ለውጡ መጥቷል ብለን እናስባለን፡፡ ምንክንያቱም ለውጡ ሲመጣ ቀናትንና ወራትን እያስቆጠረ የሚመጣ ስለሆነ ለውጡ 50% ታይቷል (ደርሰናል)፡፡ ሥለጠናው ለወደፊቱም ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ ከዚህ በፊት የሰለጠኑትም ቢሆን የበለጠ ግንዛቤያቸውን ለማስፋት እንዲችሉ ስልጠናው ቀጣይነት እንዲነኖረው ነው እቅድ የተያዘው፡፡ በሒሳብ ክፍል፣ በዕለት ገንዘብ ሰብሳቢ፣ በገንዘብ ያዥና በንብረት ክፍል ያለው አሠራር አጠቃላይ ግልፅነት እንዲኖረው ሥልጠናው በ2010 የበጀት ዓመትም ይቀጥላል፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን ጥንታዊትና ቀዳማዊት እንደመሆንዋ መጠን አስተማሪ የነበረች ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡
ስለዚህ በአስተማሪነት ሥራዋ እንድትቀጥል ያለውን የዘመናዊውን አሠራር በበለጠ አጠናክራ እንድትቀጥል ለማድረግ ሁሉም ወደዚህ መስመር እንዲገባ ነው የሚአስፈልገው፡፡ለዚህ ለውጥ ሁሉም ያገባኛል፣ ይመለከተኛል ብሎ ለለውጡ እንቅስቃሴ ተባባሪ ሊሆን ይገባዋል ብለዋል፡፡
በተያያዘ ዜና በ2009 የበጀት ዓመት ለኦዲቲንግ ሥራ የሚሠማሩ የሀገረ ስብከቱና ለክፍለ ከተማ ሠራተኞች ከግንቦት 14/2009 እስከ ግንቦት 23/2990 ዓም ድረስ የሚቆይ የኦዲቲንግ ሥልጠና በመሠጠት ላይ ነው፡፡