ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ የ2009 ዓ.ም የትንሣኤ በዓልን አስመልክተው መልእክት አስተላለፉ
ቃለ በረከት ዘብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱምወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዘተናገረ በእንተ በዓለ ትንሣኤ ቅድስት ዘእግዚእነ ወአምላክነ ወመድኃኒነ ኢየሱስ ክርስቶስ ሎቱ ስብሐት
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
• በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፤
• ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ
• የሀገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፉ የቆማችሁ፤
• በሕመም ምክንያት በየፀበሉና በየሆስፒታሉ ያላችሁ
• እንዲሁም የሕግ ታራሚዎች ሆናችሁ በየማረሚያ ቤቱ የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት፤
በትንሣኤው ኃይል በመቃብር ውስጥ በስብሶ መቅረትን ሽሮ ትንሣኤ ሙታንን ያበሠረ ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳን ለሁለት ሺሕ ዘጠኝ ዓመተ ምሕረት በዓለ ትንሣኤው በሰላም አደረሳችሁ!!
“ወሰበረ ኆኃተ ብርት፤ ወቀጥቀጠ መናሥግተ ዘሐጺን፤
የናስ ደጆችን ሰባበረ ፣ የብረት መወርወሪያዎችንም ቀጥቅጦ ቈራረጠ፤(መዝ 107፡16)፡፡
ይህ አምላካዊ ኃይለ ቃል ወልደ እግዚአብሔር የሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ በመሥዋዕትነቱ ብቃት እንደ ናስ የጠነከሩትን የኃጢአት ደጆች እንደሚሰባብር፣ እንደ ብረት የጸኑትን የሞት ብረቶች ቀጥቅጦ በመቆራረጥ እንደሚያስወግድ መንፈስ ቅዱስ በዳዊት አንደበት የተናገረው ቃለ ብሥራት ነው፤
የኃይለ ቃሉ ምሥጢራዊ ይዘት በጠንካራ ነገር የተዘጉና በጽኑ መወርወሪያዎች ክርችም ብለው የተዘጉ ደጆች መኖራቸውን ጠቁሞ፣ እነዚህን ሰባብሮና ቀጥቅጦ በሩን የሚከፍት አንድኃያል መሢሕ እንደሚመጣ የሚያመለክት ነው፡፡
በመጀመሪያው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል እንደምናነበው የሰው መኖሪያ የነበረው ነገተ ኤዶም በኃጢአተ ሰብእ ምክንያት በፍትሐ እግዚአብሔር ሲዘጋ፣ በሰይፈ ነበልባል እንደተከረቸመ፣ ኪሩባውያን ኃይላትም በጥበቃ እንደተመደቡበት በግልጽ ተመዝግቦአል፡፡
ይህ የጽድቅ የክብርና የሕይወት ደጅ በዚህ ሁኔታ ሲዘጋ፣ ለሰው ልጅ የቀረለት መኖሪያ ለሰይጣንና ለሠራዊቱ የተዘጋጀው፣ እሳቱ የማይጠፋ፣ ትሉ የማያንቀላፋ የእቶነ እሳት ከተማ ነበረ፤
ለመለኮታዊ ሱታፌና ለዘላለማዊ ሕይወት ታድሎ የነበረው የሰው ልጅ ለእግዚአብሔር ባለመታዘዙ ምክንያት ለአምስት ሺሕ አምስት መቶ ዓመታት ያህል የተጋዘው ከላይ በተጠቀሰው የዲያብሎስ ከተማ ነበር፡፡
የዚህ ከተማ ደጆችና በሮች፣ መዝጊያዎችና መወርወሪያዎች ኃጢአት፣ ፍትሐ ኵነኔና ሞተ ነፍስ ወሥጋ ነበሩ፤ የሰው ልጅ ኃጢአትን ስለ ሠራ እግዚአብሔር የቅጣት ፍርድን ፈረደበት፤ ቅጣቱም የነፍስና የሥጋ ሞት ነበረ፤ እነዚህ ነገሮች እርስ በርስ እንደ ሰንሰለት ተያይዘው የዲያብሎስን ከተማ የናስና የብረት ያህል ጠንካራ ደጅ እንዲሆን አድርገውታል፡፡
ይህንን በር ሰብሮና ፈልቅቆ የሰዎችን ነፍሳት ከዲያብሎስ ከተማ መዞ ማውጣት ለፍጡር ፈጽሞ የማይቻል ነበረ፤ ሦስቱም ነገሮች ከፍጡራን ዓቅም በላይ በመሆናቸው አምላካዊ ኃይል የግድ አስፈላጊ ሆነ፡፡
በዚህም ምክንያት ጌታችን ሥጋችንን ተዋሕዶ በዚህ ዓለም በመገለጥ እኛ ከኃጢአት ከፍትሐ ኵነኔና ከሞተ ነፍስ የምንድንበት መንገድ እርሱ ብቻ መሆኑን በአጽንዖት አስተማረ፡፡
በመጨረሻም እንደ ትምህርቱና እንደ ቃሉ በመስቀሉ ኃይል ወይም በመሥዋዕትነቱ ብቃት ሦስቱ ነገሮች ማለትም ኃጢአት፣ ፍትሐ ኵነኔና ሞተ ነፍስ ከሰው ጫንቃ ላይ እንዲወገዱ አደረገ፤
ለሰው የማይቻል የነበረ ይህ ግብረ አድኅኖ በተዋሕዶ አምላክም ሰውም ለሆነ ለጌታችን ለአምላካችንና ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የሚቻል ነበረና በእርሱ መሥዋዕትነት እውን ሆነ፡፡
ጥንቱም ለሰው ልጅ ሕይወትና ክብር ጠንቆች የነበሩ እነዚህ ሦስቱ ነበሩና እነሱ ተሰባብረውና ተቀጥቅጠው ሲወገዱ በሲኦል ይኖሩ የነበሩ የሰዎች ነፍሳት በአጠቃላይ ዓለም ከመፈጠሩ በፈት ወደተዘጋጀላቸው ወደ መንግሥተ እግዚአብሔር ተመልሰው ገቡ፡፡
ከክርስቶስ ሞት በኋላ የነፍሳተ ሰብእ ጉዞ ወደ ዲያብሎሰ ከተማ ወደ ሲኦል መሆኑ ቀርቶ ወደ እግዚአብሔር ከተማ ወደ ጽዮን መንግሥተ ሰማያት ሆነ
የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት
እኛ ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች በዓለ ትንሣኤን ከምንም በላይ በላቀ ሁኔታ የምናከብርበት ምክንያት ኃጢአት ፍትሐ ኵኔና ሞተ ነፍስ ወዲያ ተሽቀንጥረው በምትካቸው በክርስቶስ ቤዛነት ጽድቅን ይቅርታንና ሕይወተ ነፍስን የተቀዳጀንበትና ከድል ሁሉ የበለጠ የድል ቀን በመሆኑ ነው፡፡
ሁላችንም መገንዘብ ያለብን ዓቢይ ነገር የክርስቶስ ድርጊቶች በሙሉ ለሰው ድኅነት ሲባል ብቻ የተደረጉ እንጂ ለእግዚአብሔር የሚፈይዱት አንዳች ምክንያት የሌላቸው መሆኑን ነው፤ ይህም ማለት በክርስቶስ የተፈጸሙ ድርጊቶች በሙሉ ለእኛ ሲባል የተደረጉ መሆናቸውን መገንዘብ አለብን ማለት ነው፡፡
ክርስቶስ ተሰቀለ ሞተ ተቀበረ ተነሣ ሲባል እኛ ተሰቀልን ሞትን ተቀበርን ተነሣን ማለት እንደ ሆነ ልብ ብለን ልናስተውል ይገባል፤እኛ ተሰቅለን ሞተንና ተቀብረን የኃጢአታችንን ዕዳ የመክፈል ዓቅም ስላጣን ለኛ ያልተቻለውን ጌታችን ስለ እኛ ብሎ፣ በእኛ ምትክ ሆኖ ለኃጢአታቸን መከፈል የነበረበትን ዋጋ ሁሉ ከፍሎ አድኖናልና ነው፡፡
እኛ በክርስቶስ ቤዛነት ነጻነታችንን ተቀዳጅተን ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ዳግመኛ መግባት የቻልነው ክርስቶስ የከፈለው መሥዋዕትነት ለእኛ ተብሎ ስለ እኛ የተደረገ በመሆኑ ነው፡፡
የክርስቶስ ትንሣኤ የእርሱ ትንሣኤ ብቻ እንደሆነ አድርገን የምንገነዘብ ከሆነ ታላቅ ስሕተትም ኃጢአትም ነው፤ ኃጢአት ኵነኔና ሞተ ነፍስ የሌለበት እርሱማ ምን ትንሣኤ ያስፈልገዋል! ትንሣኤ ለሚያስፈልገን ለእኛ ተነሣልን እንጂ፤
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይህንን አስመልክቶ ሲያስተምር “እግዚአብሔር በምሕረቱ ባለ ጸጋ ስለሆነ በኢየሱስ ክርስቶስ አስነሣን ከእርሱ ጋርም በሰማያዊ ስፍራ አስቀመጠን” ብሎአል፤ (ኤፌ 2፡4-7)፡፡
ከዚህ አኳያ የቀን ጉዳይ ካልሆነ በቀር የትንሣኤያችን ጉዳይ በክርስቶስ ትንሣኤ የተረጋገጠና ያለቀለት ነገር እንደሆነ ማስተዋል፣ መገንዘብ፣ መረዳትና፣ ማመን ይገባናል፡፡
የጌታችን ትንሣኤ ለሰው ልጅ ተብሎ የተደረገ በመሆኑ የእኛ ትንሣኤ ነው ብለን ሁሌም መውሰድና መቀበል አለብን፤ ምክንያቱም የክርስቶስ ትንሣኤ የመጨረሻ ግቡ የሰው ልጆች ትንሣኤን ማረጋገጥ ነውና፤
የትንሣኤ ዕድል በክርስቶስ ቤዛነት ለሁሉም ተሰጥቶአል፤ አዋጁም ሕጉም በክርስቶስ ትንሣኤ ጸድቆአል፤ የቀረ ነገር ቢኖር የመጨረሻው ተግባራዊ ፍጻሜ ነው፤ እርሱም ቀነ ቀጠሮ የተያዘለት ስለሆነ ወደዚያው በእምነትና በሥነ ምግባር መገስገስ ነው፤ ሰውን ለዚህ ዓቢይ ጸጋና ዕድል ያበቃ እግዚአብሔር አምላካችን ክብርና ምስጋና ለእርሱ ይሁን፡፡
የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት፤
ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሠራውና ያስተማረው ሁሉ ምን ለማግኘት ነበረ ተብሎ ቢጠየቅ በአጭር ዐረፍተ ነገር “ሰውን ለማዳን” ነዋ ! ብሎ መመለስ ይቻላል፤ እውነቱም ሐቁም ይህና ይህ ብቻ ነው፤
ይህን ያህል ውጣ ውረድና ይህን ያህል ዋጋ ያስከፈለ የሰው መዳን በእግዚአብሔር ዘንድ ምን ያህል ተፈላጊ እንደሆነ በአድናቆት መመልከትና መቀበል ታላቅ አስተዋይነት ነው፡፡
በዚህ ሰውን የማዳን የእግዚአብሔር ክንውን እኛ ሰዎች የእግዚአብሔር ልጆች ለመሆን በቅተናል፤ ልጆቹም ሆነናል፤ ታድያ ልጅ በጠባይም፣ በመልክም በሥራም አባቱን ቢመስል ጌጥም የክብር ክብርም ነውና በሁሉም ነገር አባታችንን መከተልና መምሰል ከእኛ ይጠበቃል፡፡
እግዚአብሔር አባታችን እንደመሆኑ፣ እኛም ልጆቹ እንደመሆናችን መጠን የአባታችንን ተቀዳሚ መደበኛና ቀዋሚ ሥራ የሆነውን ሰውን የማዳን ሥራ ሳናቋርጥ የማስቀጠል ግዴታ አለብን፡፡
ዛሬም ዓለማችን የሚያድናት፣ እስከ ሞት ድረስም ደርሶ ቤዛ የሚሆናት፣ ሰላምንና ነጻነትን የሚያቀዳጃት የእግዚአብሔር ልጅ ትፈልጋለች፡፡
የጌታችን ትንሣኤ ከመቃብር በመነሣትና ሙታንን በማስነሣት ብቻ የሚገለጽ አይደለም፤ ጌታችን ከመሞቱና ከመነሣቱ በፊት ብዙ ሰዎችን ከረኃብ፣ ከበሽታ፣ ከሥነ-ልቡና ውድቀት አስነሥቶአል፤ ከተሳሳተ አመለካከት፣ ከጭካኔ፣ ከመለያየት አባዜም በተአምራትም በትምህርትም አድኖአል፡፡
ጌታችን ሰውን የማዳን ሥራ በእርሱ ብቻ ተሠርቶ እንዲቀር አላደረገም፤ እኛም እንድንሠራውና እንድንፈጽመው አዘዘ እንጂ፡፡
ከዚህ አንጻር በክርስቶስ ዘመን እንደነበረው ሁሉ ዛሬም ብዙ በሽተኞች የሚያድናቸው አጥተው በየጎዳናው፣ በየሰፈሩ፣ በየመንገዱ፣ ወድቀው ይሰቃያሉ፤ እነዚህን ማን ያድናቸው?
የተመጣጠነና በቂ ምግብ አጥተው ብዙ ሕጻናት፣ እናቶችና አረጋውያን በረኃብ አለንጋ ይገረፋሉ፤ ኅብስቱን አበርክቶ እነርሱን ማን ይመግባቸው?
በተሳሳተ አመለካከት ለሥነ ልቡና ውድቀት፣ ለቀቢፀ ተስፋና እንደዚሁም ለስሑት ትምህርተ ሃይማኖት ተጋልጠው ሃይማኖታቸውንና ታሪካቸውን በመጻረር የሚገኙ ብዙ ናቸው፤ እነዚህን ማን አስተምሮ ወደ እውነቱ ይመልሳቸው?
በእግዚአብሔር ዘንድ እነዚህን ሥራዎች መሥራትና ማስተካከል የሕዝበ ክርስቲያኑና የመምህራነ ወንጌል ግዴታዎች ናቸው፡፡
በማኅበረ ሰቡ ሥር ሰደውና ተስፋፍተው የሚታዩት እነዚህ መሰል ሃይማኖታዊና ማኅበራዊ ችግሮችን በወሳኝነት ለመቋቋም ትምህርትና ልማት መተኪያ የሌለው ሚና ይጫወታሉ፤
ለሀገራችን ድህነት መወገድ ቁልፍ መፍትሔ ሃይማኖትና ልማትን አጣምሮ መያዝና በእነርሱ ጸንቶ መኖር አማራጭ የሌለው ነው፡፡
ከነዚህ ውጭ የሆነ ኑሮ ምንም ቢሆን ምሉእ አይደለም፤ ጣዕምም የለውም፤ የሰውን ሁለንተናዊ ሕይወት ለማዳንሁለቱንም በተግባር መተርጐም ያስፈል ጋል፡፡
ሀገራችን ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ በእነዚህ ነገሮች የታደለች እንደነበረችና እነዚህን አጣምራ በመያዝ የት ደርሳ እንደነበረ በሀገሪቱ ውስጥ ያሉ የሚታዩና የማይታዩ መረጃዎች ምስክርነታቸውን ከመስጠት ዛሬም አልተገቱም፡፡
በአሁኑ ጊዜ ሀገራችን የተያያዘችውን የልማትና የሰላም ጉዞ አጠናክራ እስከ ቀጠለች ድረስ ሕሙማን የሚፈወሱባት፣ ርኁባን ጠግበው የሚኖሩባት፣ በመንፈሳዊና በዘመናዊ ዕውቀት የበለፀጉ ዜጎች የሚታዩባት ሀገር የማትሆንበት ምክንያት ምንም የለም፡፡
መላው የሀገራችን ሕዝቦች በኑሮአቸወና በሕይወታቸው መሠረታዊ ለውጥ ማምጣት የሚችሉት በሌላ ሳይሆን እነርሱ ራሳቸው እንደቀድሞ አባቶቻቸው በራስ በመተማመንና በልበ ሙሉነት፣ በትጋትና በቅንነት፣ በፍቅርና በስምምነት፣ በእኩልነትና በወንድማማችነት፣ በሰላምና በአንድነት በመቻቻልና በአብሮነት ሆነው በሚያስመዘግቡት የልማት ውጤት እንደሆነ መርሳት የለባቸውም፡፡
ሀገርን ለማልማትና የጠላትን ጥቃት በብቃት ለመመከት በአንድነት ሆኖ ከመታገል የተሻለ አማራጭ የለም፤ ስለዚህ ሕዝባችን እነዚህን እስከመቼውም ቢሆን በንቃት ሊከታተላቸውና ሊጠብቃቸው ይገባል፤ በአእምሮ የላቁ ሆኖ መገኘት በራሱ እውነተኛ ትንሣኤ ነውና፡፡
በመጨረሻም
የጌታችን ትንሣኤ “ሰውን የማዳን የእግዚአብሔር ዓላማን ያሳካ ፍጻሜ እንደሆነ ሁሉ የትንሣኤ ልጆች የሆን እኛ ሰውን ለማዳን በሚደረገው መንፈሳዊና ልማታዊ ርብርቦሽ ተሳትፎአችንን አጠናክረን እንድንቀጥል መንፈሳዊና አባታዊ መልእክታችንን በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን፣፡፡
መልካም በዓለ ትንሣኤ ያድርግልን፡፡
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ ይቀድስ
ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን
አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
ሚያዚያ ፰ ቀን ፳፻ወ፱ዓ.ም.
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ