የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ለ2ኛ ጊዜ ለገዳማትና አድባራት የቁጥጥር ሠራተኞች የኦዲት ሥልጠና መስጠት ጀመረ

kuttr

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በርዕሰ ከተማው ለሚገኙ 130 የገዳማትና አድባራት የቁጥጥር ሠራተኞች ከመጋቢት 18 ቀን 2009 ዓ.ም ጀምሮ ለአስር ተከታታይ ቀናት የሚቆይ የሒሳብ አያያዝና የኦዲት ስልጠና ለ2ኛ ጊዜ  መሰጠት ተጀምሯል ፡፡በዚሁ ሥልጠና ዕውቀትንና ግንዛቤን ለማዳበር ይረዳ ዘንድ ሰልጣኞቹ በሚሰጠው ሥልጠና ዙሪያ የተለያዩ ጥያቄዎችን በመጠየቅ ከአሠልጣኞቹ አጥጋቢ ምላሽ እያገኙ መሆናቸው ታውቋል፤ ሥልጠናው የሚሰጡት መምህራን በሀገረ ስብከቱ የሚገኙ ባለሙያዎች እና ከሌሎች ተቋማት በተጋበዙ ሞያተኞች ጭምር ነው፡፡
ሠልጣኞቹ ሥልጠናውን የሚወስዱት በቲዎሪ እና በተግባር ላይ በተደገፈ አሠራር ሲሆን  ሠልጣኞቹ ከብዛታቸው የተነሣ በሦስት ቡድን ተከፋፍለው ሁለቱ ቡድን  አራት ኪሎ በሚገኘው በሲፒዮ ኮሌጅ በኮምፒውተር በተግባር ስልጠናውን ሲወስዱ አንደኛው ቡድን ደግሞ ሀገረ ስብከቱ ባዘጋጀው የሥልጠና ማዕከል በተግባር በተደገፈ በኮምፒውተር እየሰለጠኑ መሆናቸው ታውቋል፡፡
የሥልጠናው  ዋና ፍሬ ሐሳብ መሠረታዊ የሒሳብ አያያዝ፣ የንብረት አመዘጋገብና የኦዲት ምርመራ ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ሀገረ ስብከቱ ለገዳማትና አድባራት የቁጥጥር ሠራተኞች የሙያ ማሻሻያ ስልጠና መስጠት የጀመረው በአለፈው 2008 ዓ.ም ሲሆን በአንደኛው ዙር ከሀገረ ስብከቱ የሒሳብና የቁጥጥር ሠራተኞች፣ ከ7ቱ ክፍላተ ከተማ ለተወጣጡ የሒሳብና የቁጥጥር ሠራተኞች ጋር ከ60 ያላነሱ የገዳማትና የአድባራት የቁጥጥር ሠራተኞች ሠልጥነዋል፤ ሀገረ ስብከቱ ይህን መሠረታዊ የሙያ ማሻሻያ ሥልጠና መስጠት ያስፈለገበት ዐቢይ ምክንያት በገዳማትና አድባራቱ ቀደም ሲል የነበረው የሒሳብ አያያዝ እና የቁጥጥር አሠራር ሥርዓት የነጠላ ሒሳብ (single entry) አያያዝ ሲሆን ይህም አሠራር የቤተ ክርስቲያንን ገንዘብ ለብክነት የሚያጋልጥ ሆኖ በመገኘቱ ነው፤ ይህም በመሆኑ አሁን እየተሰጠ ባለው ሥልጠና የመንትያ ሒሳብ አያያዝ፣ (double entry) የቁጥጥር እና የኦዲት አሠራር የቤተ ክርስቲያንን ሀብትና ንብረት በአንድ ላይ መዝግቦ የሚይዝ እና ለቁጥጥርም አመቺ በመሆኑ ነው፡፡
ይህ ዘመናዊ የሁለትዮሽ (double entry) የሒሳብ አያያዝ እና የኦዲት ምርመራ ሥልጠና ሙሉ በሙሉ ከተጠናቀቀ በኋላ የገዳማቱና አድባራቱ የሒሳብ አያያዝ በሀገሪቱ ውስጥ ከሚገኙት የግልና የመንግሥት ተቋማት ጋር ተፎካካሪ እና ተወዳዳሪ ሆኖ ለመሥራትየሚስችል ሲሆን የገዳማቱና አድባራቱ ሀብትና ንብረት በአግባቡ ተጠብቆ ለታለመለት ዓላማ ሊውል እንደሚችል ሥልጠናውን ከሚሠጡት ባለሙያዎች ለመረዳት ተችሏል፡፡
በሀገረ ስብከቱ እቅድ መሠረት ሁሉም ገዳማትና አድባራት ከሐምሌ 1/2009 ዓ.ም.ጀምሮ ይህ ዘመናዊ የሒሳብ አያያዝ (Double entry) እና የኦዲት ምርመራ ሥራ ተጠናክሮ ሥራ ላይ እንደሚውል ታውቋል፤ ሠልጣኞቹ በጋራ የተማሩዋቸው የሒሳብ አያያዝ እና የኦዲት ምርመራ ትምህርቶች ካጠናቀቁ በኋላ በሀገረ ስብከቱ በተዘጋጀው የሥልጠና ማዕከል በማንኛውም ጊዜ እየተመላለሱ ግንዛቤያቸውን እንደሚያሠፉ እና የተሻለ የአሠራር ልምድ እንደሚወስዱ ከሀገረ ስብከቱ የቁጥጥር አገልግሎት ዋና ክፍል ተጠቁሟል፡፡
ስለዚህ በሁሉም አቅጣጫ ያለው የአሠራር ችግር ሊፈታ የሚችለውና የቤተ ክርስቲያናችን ሀብትና ንብረት በአግባቡ ተጠብቆ ለታለመለት ዓላማ ሊውል የሚችለው የሠራተኛው አእምሮ በሥልጠና ሲዳብር ስለሆነ ሀገረ ስብከቱ በያዘው እቅድ መሠረት  ሥልጠናው ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባዋል እንላለን፡፡