የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናትን ቅዱስ ሲኖዶስ በወገኖቻችን ላይ የደረሰውን የሞት አደጋ አስመልክቶ የሀዘን መግለጫ አስተላለፈ

pp009

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን ፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ መጋቢት 2 ቀን 2009 ዓ.ም. ምሽት በወገኖቻችን ላይ የደረሰውን የሞት አደጋ አስመልክቶ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የተሰጠ የሀዘን
መግለጫ ፡፡
መጋቢት 2 ቀን 2009 ዓ.ም. ከምሽቱ 2፡00 ሰዓት ሲሆን በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ልዩ ስሙ ቆሼ እየተባለ በሚጠራው ስፍራ በሚኖሩ ወገኖቻችን ላይ ድንገተኛ የሞት አደጋ ደርሷል ፡፡ በደረሰውም አሳዛኝ አደጋ ከፍተኛ ኀዘን ተሰምቶናል፡፡
በመሆኑም እግዚአብሔር አምላካችን በደረሰው ሕልፈተ ሕይወት ለተጎዱ ወገኖች ቤተሰቦች መጽናናትን፣ ብርታትን እንዲሰጥልን፤ የሟቾቹንም ነፍሳት በመንግሥቱ እንዲቀበልልን በመጸለይ የተሰማንን ኀዘን እየገለፅን፣ ለእነዚሁ በድንገተኛ አደጋ ለተለዩ ወገኖቻችን ከመጋቢት 7 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ በመላ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናትና ገዳማት ጸሎተ ፍትሐት እንዲደረግላቸው፤ እንዲሁም ቤታቸው በመፍረሱ ምክንያት በመጠለያ ለሚገኙ ወገኖቻችን ከቤተ ክርስቲያናችን ብር 200.000.00 /ሁለት መቶ ሺህ ብር/ ርዳታ እንዲሰጥ ቋሚ ሲኖዶስ ወስኗል ፡፡
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ