የየካ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት በበጀት ዓመቱ ባስመዘገበው የልማት ስኬት የሽልማት መርሐ ግብር አካሄደ!!

0176

በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የየካ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት በ2009 ዓ.ም የበጀት ዓመት በፐርሰንት ክፍያ ዕድገት፣ በአብያተ ክርስቲያናት መስፋፋት እና በመልካም አስተዳደር ከፍተኛ ዕድገት ያስመዘገበ በመሆኑ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፣ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነት የየመምሪያ ኃላፊዎች፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መምህር ጎይቶኦም ያይኑ፣ የየካ ክፍለ ከተማ የሥራ ኃላፊዎችና የጸጥታ ኃይሎች፣ የየካ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት የሥራ ኃላፊዎችና የክፍለ ከተማው አብያተ ክርስቲያናት ተወካዮች  በተገኙበት አርብ የካቲት 17 ቀን 2009 ዓ.ም  በመንበረ ፓትርያርክ ጽ/ቤት የመሠብሰቢያ አዳራሽ የሽልማቱ ሥነ ሥርዓት ተከናውኗል፡፡
የክፍለ ከተማው ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ መልአከ ገነት ቀሲስ ሙሴ ዘነበ፣ በመርሐ ግብሩ ወቅት ባስተላለፉት የመክፈቻ መልእክት የክፍለ ከተማው ቤተ ክህነት በ2009 ዓ.ም ግማሽ የበጀት ዓመት ከስምንት ያላነሱ አዳዲስ አብያተ ክርስቲያናት ተተክለዋል፡፡
የፐርሰንት ክፍያው ከዕጥፍ በላይ እያደገ ይገኛል፡፡ ከክፍለ ከተማው መስተዳደርና ከጸጥታ ኃይሎች ጋር በመተባበር በክፍለ ከተማው የመሠረተ ልማትና የሰላም ማስፈን ሥራ ተሠርቷል፡፡
በዘንድሮው 2009 ዓ.ም የጥምቀት በዓል አከባበርን አስመልክቶ የሁሉም አብያተ ክርስቲየናት ታቦታት ወደ ጥምቀተ ባህሩ በመጓዝ በዓሉ በሰላምና በደማቅ ሁኔታ ተከብሯል፡፡
ይህንኑ ምክንያት በማድረግ የክፍለ ከተማው ቤተ ክህነት አጠቃላይ የሥራዎቹን ስኬት አስመልክቶ ለሁሉም ባለድርሻ አካላት የማበረታቻ ሽልማት ያዘጋጀ መሆኑን መልአከ ገነት ቀሲስ ሙሴ ዘነበ ካብራሩ በኋላ የሽልማቱ መርሐ ግብር በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ እጅ ተከናውኗል፡፡
በመጨረሻም ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ በየካ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት የተከናወኑትን የመሠረተ ልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎች አስመልክተው ባስተላለፉት አባታዊ መልእክት “ይደልዎ አስቦ ለዘይትቀነይ” ለሚአገለግል ዋጋው ይገባዋል፡፡ (ማቴ 10)
አሁን የተሰጠው የዕውቅና ሽልማት ለሠራችሁትና ላበረከታችሁት አገልግሎት ዋጋ ነው፡፡ የፖሊስ ኮሚሽነሮችም በሰላሙ ረገድ ላደረጉት ዕገዛና በጠቅላላ በጸጥታው ዙሪያ ላበረከታችሁት የላቀ አስተዋጽኦ የክፍለ ከተማው ጽ/ቤት ዛሬ ሽልማት ተሰጥቷችኋል፡፡ ምክንያቱም መልካም ላደረገ ሁሉ ዕውቅና መስጠቱ ተገቢ ነው፡፡
በመንፈሳዊ ተግባር ጸጥታውን ከማስከበርም በተጨማሪ ቤተ ክርስቲያን በዓመት በዓመት ከምታከብራቸው ዓበይት በዓላት አንዱ የሆነውን በዓለ ጥምቀትን በማክበር፣ ለቤተ ክርስቲያናችን መስፋፋት ተጨማሪ ቦታ እንዲገኝ በማድረግ፣ ጸጥታውን በማስከበርና በዓሉም በሰላማዊ ሁኔታ እንዲከበር በማድረግ በየበዓላቱ ለምታደርጉት የሰላምና የጸጥታ ማስከበር ሥራ ዋጋችሁን እግዚአብሔር አምላክ አስፍቶ እንዲሰጣችሁ እንጸልያለን፡፡ የሃይማኖቱ ባለ ድርሻዎች በመሆናችሁ ትብብራችሁ ምን ጊዜም ቢሆን እንዳይለየን አደራ እላለሁ፡፡
ቤተ ክርስቲያን የራሷ የሆነ መንፈሳዊ አገልግሎት አላት፡፡ ስለ ሀገር ሰላም፣ ስለ ፍቅር፣ ስለ አንድነት በመጸለይና በቀኖናዋም መሠረት ለምዕመናን መንፈሳዊ አገልግሎት የምታበረክት ናት፡፡
ይህንን መልካም ሥራዋን ሁሉም ሊአውቅላት ይገባል፡፡ መንግሥት በድርሻው ሀገርን  የመጠበቅ አገልግሎት ይሰጣል፡፡ ቤተ ክርስቲያን ደግሞ በመንፈሳዊ ሥራዋ ለሀገር ሰላም ትጸልያለች፣ ታጠምቃለች፣ ታቆርባለች፡፡
ቤተ ክርስቲያናችን ጥንታዊት፣ ታሪካዊት፣ ዓለም አቀፋዊ ናት፡፡ ስለዚህ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ  ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የተለየ ክብር ይገባታል፡፡ ቤተ ክርስቲያንዋ እስከ አሁን ድረስ ያቆየችው ታሪክና ወደ ፊትም ለቀጣዩ  ትውልድ  የምትሰጠው አገልግሎት ሰፊ ነው፡፡ አብያተ ክርስቲያናትን በማስፋፋት የተጋችሁ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችም ከስምንት ያላነሱ አብያተ ክርስቲያናትን በመሥራት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ተጨማሪ መንፈሳዊ ሀብት እንዲኖራት በማድረግ የማስተባበሩን ሥራ፣ በመሥራታችሁ ልትመሰገኑ ይገባችኋል፡፡
የክፍለ ከተማው ቤተ ክህነት ኃላፊ የሆኑት ቀሲስ መልአከ ገነት ሙሴ ዘነበ፣ ትጉህ አገልጋይና ዕውቀትም ያላቸው ስለሆኑ ይህንን ሥራ በማስተባበር ሥራው እንዲከናውን በማድረግና በሥራው ለተሳተፉ ወንድሞች ይገባቸዋል በማለት ይህንን የሽልማት ሥራ በማከናወናቸው ሊመሰገኑ ይገባቸዋል፡፡ ለወደፊቱም ለሚሰጡት አገልግሎት እግዚአብሔር አምላክ እንዲረዳቸው እንጸልያለን፡፡
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መምህር ጎይቶም ያይቶ በማስተባበር፣ ለክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት አስፈላጊውን ዕገዛ በማድረግ ባጠቃላይ ለመላው ሕዝብ ክርስቲያን ተገቢውን አገልግሎት በመስጠት ባበረከቱት አገልግሎት ሊመሰገኑ ይገባቸዋል፡፡ ወደፊትም ይህ አገልግሎት ተጠናክሮ እንዲቀጥል እንፈልጋለን፡፡
ከሁሉም በላይ ሰላም፣ ፍቅርና አንድነት እንዲሰፍን፣ ጭቅጭቅና ንትርክ መፍጠር፣ አድማና ያልሆነ ወሬ ማስወራት ኃጢአት ስለሆነ በዚህ ተግባር ላይ ተሠማርተው አሉባልታ የሚአናፍሱ ሰዎች ሊታገሡ ይገባቸዋል፡፡ ምን አልባት ጥሩ የሠራን መስሏቸው ከሆነ ድርጊቱ እነርሱንም ሆነ ቤተ ክርስቲያንን እየጎዳ ያለ ስለሆነ ከዚህ መጥፎ ድርጊት ሊታቀቡ ይገባቸዋል፡፡
ይህንን መጥፎ ሥራ የሚሠሩትን ወገኖች መምከር፣ ማስተማርና ማስረዳት ያስፈልጋል፡፡ ቤተ ክርስቲያን የምታስተምረው ትህትናን፣ ፍቅርንና አንድነትን ነው፡፡ በጾምና በሱባኤ ወቅት ወደ ቤተ ክርስቲያን እየመጡ ሰላማዊውን ህዝብ እስከማወክ የደረሱም አሉ፡፡
በተለይ አገልደጋዮች በጾሙ ለምዕመናን ተገቢውን አገልግሎት በመስጠት ፈንታ ኃላፊነታቸውን ዘንግተው ከባድ ችግር እንዳጋጠማቸው በማስመሰል በሱባኤው ቤተ ክርስቲያን እየሄዱና እየጮኹ ማስቸገራቸው ተገቢ ስላልሆነ ለወደፊቱ አእምሮ እንዲገዙ ቢመከሩ የተሻለ ነው፡፡ እንዲህ አይነቱ ድርጊት ከቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችና ከመንፈሳዊ ሰዎች አይጠበቅም በማለት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ሰፋ ያለ አባታዊ ትምህርትና መመሪያ ሰጥተዋል፡፡