ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ የ2009 ዓ.ም የልደት በዓልን አስመልክተው መልእክት አስተላለፉ
ቃለ በረከት ዘብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
ዘተናገረ በእንተ በዓለ ልደቱ ለእግዚእነ ወአምላክነ ወመድኃኒነ ኢየሱስ ክርስቶስ ሎቱ ስብሐት!!
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!
-በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፤
-ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፤
-የሀገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፉ የቆማችሁ፤
-በሕመም ምክንያት በየፀበሉና በየሆስፒታሉ ያላችሁ፤
-እንዲሁም የሕግ ታራሚዎች ሆናችሁ በየማረሚያ ቤቱ የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት፤
እኛን ለማዳን በለበሰው ሥጋ በቤተ ልሔም ተወልዶ በመካከላችን የተገኘው፣ በመለኮታዊ ባህርዩ የማይወሰነው አካላዊ ቃል እግዚአብሔር ወልድ ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳን ለሁለት ሺሕ ዘጠኝ ዓመተ ምሕረት በዓለ ልደቱ በሰላም አደረሳችሁ!!
“ወበዘርዕከ ይትባረኩ ኵሎሙ አሕዛበ ምድር፤ የምድር አሕዛብ ሁሉ በዘርህ ይባረካሉ” ፤(ዘፍ 22፤18)፡፡
በሁሉም ዘንድ እንደሚታወቀው በረከት የመልካም ነገር ሁሉ ምንጭ ነው፤ እግዚአብሔር በጥንተ ፍጥረት ለሰው ልጅ የሰጠው የመጀመሪያው ጸጋ ብዝኃ በረከት ነው ፡፡ ቅዱስ መጽሐፍ ይህንን አስመልክቶ እንዲህ ይላል “እግዚአብሔርም ባረካቸው፤ እንዲህም አላቸው፤ ብዙ ተባዙ ምድርንም ሙሉአት፤ ግዙአትም፤ የባህርን ዓሣዎችና የሰማይን ወፎች በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ግዙአቸው” ይላል፤ (ዘፍ 1፤28)፡፡
ለሰው የተሰጠው በረከት በኃጢአት ምክንያት መሰናክል ቢገጥመውም፣ እግዚአብሔር በፍጡሩ ጨርሶ አይጨክንምና ሙሉና ፍጹም የሆነው በረከት እንደገና ተመልሶ ለሰው ልጅ እንዴት እንደሚሰጥ ለበረከት በጠራቸውና በመረጣቸው ቅዱሳን አበው አማካይነት ሲያስታውቅ ኖሮአል፡፡
በተለይም የበረከት አባት ተብሎ በሚታወቀው በአብርሃም ዘር በኩል መጻኢው በረከት እውን እንደሚሆን “በዘርህ የምድር አሕዛብ ሁሉ ይባረካሉ” ተብሎ በእግዚአብሔር አንደበት በማያሻማ ሁኔታ ተነግሮ ነበር፡፡
ከእውነተኛው በረከት ተራቁታ የቆየችው ዓለመ – ሰብእ፣ እግዚአብሔር በራሱ ቃል የገባላት ዘላቂውና እውነተኛው በረከት እስኪመለስላት ድረስ ለአምስት ሺሕ አምስት መቶ ዓመታት በተስፋ ስትጠባበቅ ቆይታለች፡፡
የተናገረውን የማያስቀር እግዚአብሔር በረከቱን ለሕዝቡ የሚያድልበት ጊዜ ሲደርስ ቅዱስ መንፈሱን ባሳደረባት ቅድስት እናት በኤልሳቤጥ አንደበት የበረከቱ ሙዳይ ቅድስት ድንግል ማርያም፣ በረከቱ ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑንና በረከቱን ለምድር አሕዛብ ሁሉ ሊያድል እንደመጣ “ከሴቶች ሁሉ ተለይተሸ አንቺ የተባረክሽ ነሽ የማኅፀንሽ ፍሬም የተባረከ ነው” ሲል የምሥራቹን ለዓለም አሰማ፤(ሉቃ 1፡41-43)፡፡
ቀዳማዊ የሆነ እግዚአብሔር ወልድ በድንግል ማርያም ማኅፀን ውስጥ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን በፅንስ ቆይቶ የዛሬ ሁለት ሺሕ ዘጠኝ ዓመተ ምሕረት ታሕሣሥ ሃያ ዘጠኝ ቀን በቤተ ልሔም ተወለደ ጌታችን በተወለደ ጊዜ የሰማይ ሠራዊት ማለትም መላእክትና የመላእክት አለቆች “ወናሁ ተወልደ ለክሙ መድኅን ዘውእቱ እግዚእ ቡሩክ፤ እነሆ መድኅን ተወልዶላችኋል፤ ይኸውም ቡሩክ የሆነ ጌታ ነው” በማለት የሕጻኑን ማንነት ከገለጹ በኋላ “በሰማያት ለእግዚአብሔር ክብር ይሁን፤ በምድርም ሰላም ይሁን፤ ለሰውም በጎ ፈቃዱ ይደረግለት” እያሉ የተወለደው ሕጻን ለሰው ልጅ የሚያስገኘውን ሰላምና መልካም በረከት በመግለጽ ደስታቸውን በቃለ መዝሙር በቤተ ልሔም ዙሪያ አስተጋብተዋል፡፡
ከሰው ወገንም ቅድስት ድንግል ማርያም፣ ከእርስዋ ጋር የነበሩ ወገኖች፣ እንደዚሁም በአካባቢው የነበሩ የከብት እረኞች በመላእክት የምስጋና መዝሙር ተሳታፊዎች ነበሩ፤ (ሉቃ 2፤8-20)፡፡
እንግዲህ ከጥንት ጀምሮ በአበው ሲነገርና ሲጠበቅ የነበረው የበረከት ተስፋ በቃልም፣ በመልእክትም፣ በሐሳብም፣ በምሥጢርም ተፋልሶ ሳያጋጥመው፣ ከላይ ጀምሮ እስከ ታች ፍሰቱና ምሥጢሩ ተጠብቆ በተነገረው መሠረት ተፈጽሞ መገኘቱ፣ የክርስትና ሃይማኖት ምን ያህል አምላካዊ የሆነ ጽኑ መሠረት እንዳለው ያረጋግጣል ፡፡
የክርስትና ሃይማኖት መሠረቱ “ባርኮ እባርከከ፤ መባረክን እባርክሃለሁ” ከሚል ተነሥቶ፣ “የአባቴ ቡሩካን መንግሥተ ሰማያትን ትወርሱ ዘንድ ወደኔ ኑ!” በሚል የሚጠናቀቅ፣ መነሻውና መድረሻው በረከት የሆነ ሃይማኖት ነው፡፡
የክርስትና ሃይማኖት “ለሰላሙም ፍጻሜ የለውም” ከሚል ተነሥቶ “በምድርም ሰላም ይሁን” በሚል ተንደርድሮ፣ በምስጋና፣ በክብርና በሰላም፣ በማያልፍም ሕይወት ዘላለማዊነቱን የሚያውጅ ሃይማኖት ነው፡፡
የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት
መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደበት ዕለት ከወደላይ የተላለፈው ዓቢይ መልእክት ሰላምና በረከት በምድር ላይ ሆነ የሚል እንደሆነ ማስተዋል አለብን ፡፡
ታላቁ ሊቅና ኢትዮጵያዊው አባት ቅዱስ ያሬድ ስለዚህ በረከት ሲናገር “ በእንተ ልደቱ ለክርስቶስ አድባር ኮኑ ኅብስተ ሕይወት፤ወዕፀወ ገዳምኒ ፈረዩ አስካለ በረከት፤ ወማየ ባህርኒ ኮነት ሐሊበ ወመዓረ፤ ማለትም ክርስቶስ በተወለደ ጊዜ ተራሮች የሕይወት እንጀራ ሆኑ፤የበረሀ ዛፎችም የበረከት እሸትን አፈሩ ፤የባህር ውሀም ወተትና ማር ሆነች” ይላል፡፡
የቅዱስ ያሬድ ቃለ ዝማሬ ሕያዋኑም ግኡዛኑም ሁሉ በልደተ ክርስቶስ ምክንያት በበረከት እንደ ተንበሸበሹ ይመሰክራል፡፡
ከዚህ አኳያ በበዓለ ልደተ ክርስቶስ የሚበላ እንጀራና የሚጠጣ ውሃ አጥቶ በረኃብና በጥም ተጐሳቊሎ የዋለ አልነበረም ብቻ ሳይሆን፤ እንጀራውም ወተቱም ማሩም ፍጥረቱ ሁሉ እንደ ፈለገው እየተመገበ በሰላምና በደስታ ቀኑን ሁሉ ማሳለፉን እንገነዘባለን ፡፡
የልደተ ክርስቶስ በረከት ገደብ የለሽ መሆኑን ያወቅን የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮች ነን የምንል ክርስቲያኖች በዚህ ቀን ርቦትና ጠምቶት፣ አዝኖና ተክዞ የሚውል ሰው እንዳይኖር ያለውን በማካፈልና በጋራ በመመገብ የታረዘውን በማልበስ የታመመውን በመጠየቅ የበዓሉን ሃይማኖታዊና ሥነ ምግባራዊ ገጽታ መጠበቅና ማስጠበቅ ይኖርብናል፡፡
በዓለ ልደተ ክርስቶስ የበረከት ቀን ከመሆኑም ሌላ የዕርቅ፣ የእኩልነትና የአንድነት በዓልም ነው፡፡ ከብዙ ጊዜ መለያየትና መራራቅ በኋላ፣ ፈጣሪ የሰዎችን ሥጋ አካሉ አድርጎ በሰዎች መካከል በአካል መገኘት ከዕርቅ ሁሉ የበለጠ ዕርቅ መሆኑን መዘንጋት የለበትም ፡፡
በዕለተ ልደተ ክርስቶስ መላእክትና ሰዎች ፈጣሪያቸው በተወለደበት ዙሪያ ተሰባስበው በእኩልነትና በአንድነት ሲዘምሩና ሲያመሰግኑ ማየትና መስማትም የፍጡራንን እኩልነትና አንድነት ያረጋገጠ ሌላው ክሥተት ነበረ፡፡
ሰማያውያንና ምድራውያን ለሰው ልጅ ህልውና ወሳኝ የሆነውን ‹‹ ሰላም በምድር ይሁን›› እያሉ በአንድ ቃል መዘመራቸውም ለሰማያውያኑም ሆነ ለምድራውያኑ ከሰላም የበለጠ ትልቅ ጸጋ የሌለ መሆኑ የሚያስገነዝብ ነበረ፡፡
እንዲህም ስለሆነ ከልደተ ክርስቶስ ያልተማርነው ትምርት የለም ማለት ይቻላል፤ እግዚአብሔር በልደተ ክርስቶስ ዕለት ያስተማረን ብቻ አጥብቀን ብንይዝና ይህንኑ ብንፈጽም ከበቂ በላይ ነው ቢባል ፍጹም እውነት ነው፡፡
ተራራው ሁሉ የሕይወት እንጀራ ሆነ ፤የበረሀ ዛፍ ሁሉ የበረከት እሸት ሆነ፤የባህር ውሃም ማርና ወተት ሆነች ተብሎ ሲነገር በዓለ ልደተ ክርስቶስ የልማት፣ የዕድገትና፣ የብልፅግና አስተማሪ መሆኑን ያስገነዝባል ፡፡
ከዚህ አንጻር ዛሬም ቤተ ክርስቲያን የምታስተምረው ተራራው ይልማ፣በረሀው በደን ይሸፈን፣ ውሃው ከብክለት ድኖ ለምግብነት የሚያገለግሉ ሕይወታውያን ፍጡራን በብዛት ይኑሩበት የሚለው በልማትና በበረከት የተሞላው የልደተ ክርስቶስ አስተምህሮ ነው፤ ሕዝበ ክርስቲያኑ ይህንን አምላካዊ አስተምህሮ በምልአት ተቀብሎ ወደ ልማት ከተሠማራ በዚያው መጠን በረከቱን በገፍ ያፍሳል፡፡
ከዚህም ጋር “የሺሕ ፍልጥ ማሠሪያው ልጥ›› እንደሚባለው የሁሉም ማሠሪያ ሰላም ስለሆነ የድሮ ነጋዴ ለንግድ ሲወጣ ስንቁን በትከሻው ተሸክሞ እንደሚጓዝ ሁሉ፣ዛሬም የልማት ነጋዴ ሕዝባችን ሰላምን በልቡ ቋጥሮ መጓዝ ይኖርበታል፡፡
ሁሉም ችግሮች ከሰላም በታች መሆናቸውን ሁሉም ማኅበረሰባችን መገንዘብ አለበት፤ ሁሉም ለአንድነት፣ ለእኩልነት፣ ለፍትሕ፣ ለወንድማማችነት፣ ለመተማመንና ለመከባበር መስፈን የማያወላውል አቋም ሊይዝ ይገባል፡፡
የቀደሙት አባቶቻችን ኢትዮጵያን ታላቅ ሀገር እንድትሆን ያበቋት አንድነታቸውን ጠብቀው በጋራ ስለሠሩ ነው፤ያለ አንድነት ታላቅነትም፣ ኃያልነትም፣ ልማትና ዕድገትም፣ ፈጽሞ እንደማይገኝ ሳይታለም የተፈታ ነውና ሕዝባችን ይህንን በውል ማጤን ይኖርበታል፡፡
በመጨረሻም
ከላይ ለመግለፅ እንደተሞከረው የክርስቶስ መወለድ ዋና ዓላማ መለያየትና መቃቃርን፣ መነታረክንና፣ በጥላቻ ዓይን መተያየትን አስወግዶ በምትኩ ዕርቅን፣ ዘላቂ ሰላምና አንድነትን በሰው ሁሉ አእምሮ ውስጥ ማስፈን እንደሆነ እናውቃለን ፡፡
በመሆኑም ይህ ነገረ ሕይወት ከተሰበከባቸው የዓለማችን ሀገራት ኢትዮጵያ ቀዳሚዋ ሀገር እንደመሆኗ መጠን፣ በእግዚአብሔር ከተሰጣት የቅድሚያ ኃላፊነት አንጻር በሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃም ሁሉ፣ እንደ ድሮው ደማቁ የአንድነት ታሪኳና ተደናቂው ሥልጣኔዋ፣ እንደዚሁም ጽኑ ሰላምዋና ልማቷ ጠብቃ በማስጠበቅ አስተማሪነትዋ ጎልቶ እንዲወጣ “ችግሮች ሁሉ ከሰላም በታች ናቸው” የሚለውን ጠንካራ የሰላም አስተሳሰብ መርሕ በማድረግ ሁሉም በአንድነት፣ በኃላፊነት፣ በቅንነትና በተቈርቋሪነት ሀገሩን እንዲጠብቅና እንዲያለማ መልእክታችንን በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን፡፡
መልካም የልደት በዓል ያድርግልን
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝባችንን ይባርክልን
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
አሜን
አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፤
ታሕሣሥ 2009ዓ.ም
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ