“የምናመልከው አምላካችን ከሚነደው ከእሳቱ እቶን ያድነን ዘንድ ይችላል”
ከ605 እስከ 562 ዓመተ ዓለም በባቢሎን የነገሠው ናቡከደነጾር ቁመቱ ስድሳ ክንድ፣ወርዱም ስድስት ክንድ የሆነውን የወርቁን ምስል አሠራ፤
በባቢሎንም አውራጃ በዱራ ሜዳ አቆመው፤ ንጉሥ ናቡከደነጾር መኳንንትንና ሹማምንቶችን፣ አዛዦችንና አዛውንቶችን፣ በጅሮንዶችንና አማካሪዎችን፣ መጋቢዎችንም፣አውራጃ ገዢዎችንም ሁሉ ይሰበሰቡ ዘንድ ንጉሡም ናቡነከደነጾር ላቆመው ምስል ምረቃ ይመጡ ዘንድ ላከ፡፡
በዚያን ጊዜም መኳንንቱና ሹማምንቱ አዛዦቹና አዛውንቶቹ በጅሮንዶቹና አማካሪዎቹ መጋቢዎቹና አውራጃ ገዢዎቹ ሁሉ ንጉሡ ናቡከደነጾር ላቆመው ምሥል ምረቃ ተሰበሰቡ ፡፡ ናቡከደነጾርም ባቆመው ምስል ፊት ቆሙ፤ አዋጅ ነጋሪውም እየጮኽ እንዲህ አለ፡፡ ወገኖችና አህዛብ በልዩ ልዩ ቋንቋም የምትናገሩ ሆይ የመለከትን፣ የእንቢልታን፣ የመሰንቆንና የክራርን፣የበገናንና የዋሽንትን፣ የዘፈንንም ሁሉ ድምፅ በሰማችሁ ጊዜ ተደፍታችሁ ንጉሡ ናቡከደነጾር ላቆመው ለወርቁ ምስልም እንድትሰግዱ ታዛችኋል፤ ተደፍቶ የማይሰግድ በዚያን ጊዜ በሚነድ እሳት አቶን ውስጥ ይጣላል የሚል አዋጅ የታወጀ በመሆኑ በአዋጁ መሠረት የበገናውንና የዘፈኑን ሁሉ ድምጽ የሚሰሙ አህዛብና በልዩ ልዩ ቋንቋ የሚናገሩ ወገኖች ጉንሥ ናቡከደነጾር ላቆመው የወርቅ ምስል ሰገዱ፡፡ በዚያን ጊዜ ግን ሲድራቅ፣ሚሳቅ፣አብድናጎ የሚባሉ ሶስት አይሁዳውያን ወጣቶች ናቡከደነጾር ላቆመው የወርቅ ምስል አንሰግድም በማለታቸው ተከሰው ለፍርድ ቅጣት ቀረቡ፡፡
ንጉሥ ናቡከነደጾርም በብስጭትና በቁጣ፣ ሲድራቅን፣ሚሳቅን እና አብድናጎን ወደ እርሱ ያመጡአቸው ዘንድ አዘዘ፡፡
ካመጡአቸውም በኋላ ለወርቁ ምስል አለመስገዳችሁ እውነት ነውን ብሎ ጠየቃቸው፡፡ ወጣቶቹም ለምስሉ እንደማይሰግዱ አረጋገጡለት፡፡
ንጉሡም በሚነድ እሳት ትጣላላችሁ ከእጄስ የሚአድናችሁ አምላክ ማን ነው ብሎ ተናገራቸው፡፡
ሲድራቅ ፣ሚሳቅ ፣አብድናጎም የምናመልከው አምላካችን ከሚነደው ከእሳቱ አቶን ያድነን ዘንድ ይችላል፤ከእጅህም ያድነናል፡፡ እርሱ ባያድነን አማልክትህን እንዳናመልክ ላቆምከውም ለወርቁ ምስል እንደማንሰግድ እወቅ አሉት፡፡ በዚያን ጊዜ ንጉሥ ናቡከደነጾር ተቆጥቶ ሲደራቅን ሚሳቅን አብድናጎን አስረው ወደ እሳቱ እቶን ይጥሏቸው ዘንድ ኃያላኑን አዘዘ፡፡
በዚያን ጊዜም 3ቱም ወጣቶች ከልብሳቸው ጋር በሚነደው የእሳት እቶን ውስጥ ተጣሉ፡፡
ንጉሥ ናቡከደነጾር የ3ቱን ወጣቶች ሁኔታ ለማየት ውደ እሳቱ እቶን በቀረበበት ወቅት ወጣቶቹ እሳቱ ሳያቃጥላቸው ከመልአኩ ጋር በእሳቱ መካከል ሲመላለሱ በማየቱ መልአኩን የላከ ፣ ከአምላካቸውም በቀር ማንንም አምላክ እንዳያስመልኩና እንዳይሰግዱ ሰውነታቸውን አሳልፈው የሰጡትን የንጉሡንም ቃል የተላለፉትን በእርሱ የታመኑት ባሪያዎቹን ያዳነ የሲድራቅና የሚሳቅ የአብድናጎም አምላክ ይባረክ በማለት ንጉሥ ናቡከደነጾር 3ቱን ወጣቶች በባቢሎን አውራጃ ውስጥ ከፍ ከፍ አድርጋቸው (ዳን3፤1-30)
ንጉሥ ናቡከደነጾርም “መንግሥቱ ዘለዓለም ወምኩናኑኒ ለትውልደ ትውልድ” መንግሥቱ የዘለዓለም መንግሥት ነው ግዛቱም ለልጅ ልጅ ነው በማለት የእግዚአብሔርን ታላቅነት አደነቀ (ዳን4፤3)
ንጉሥ ናቡከደነጾር የወርቁን ምስል ያቆመበት ቦታ ልዩ ስሙ ዱራ ሜዳ በመባል የሚታወቅ ሲሆን የዱራ ሜዳ ከባቢሎን በስተደቡብ ርቆ የሚገኝ እና የደንጊያ ክምር የበዛበት ቦታ ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ማብራሪያዎች ላይ በተገለጸው መሠረት የጣዎቱ መጠሪያ ስም ናቡ በመባል የተሰየመ ሲሆን ይኽውም የንጉስ ናቡከደነጾር ስም የመጀመሪያዎቹ ሁለት ፊደላት ናቸው፡፡ 3ቱ ወጣቶች ከንጉሡ ቃል ይልቅ ለእግዚአብሔር ቃል ታዘዙ፡፡ እግዚአብሔር ከሚደው የእሳት እቶን ይታደጋቸው ዘንድ ፈቃደኛ ቢሆንም ባይሆንም የእግዚአብሔርን ቃል ለመፈጸም በእምነታቸው ፀኑ፡፡ ናቡከደነጾር ከ3ቱ ወጣቶች ጋር 4ኛ ሆኖ በእሳቱ ውስጥ ሲመላለስ የነበረውን ሁሉን በሚችል የእስራኤል አምላክ የተላከ ነው ብሎ በማመን ያለማመንታት ተቀበለ፡፡ ይህ መልእክተኛ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ መሠረት መልአከ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ነው፡፡
ለዚህም የሚቀርበው ማስረጃ በትንቢተ ዳንኤል መጽሐፍ ስሙ ተገልጿል፡፡ (ዳን8፤15) (ዳን፤21) በሌላ አገላለጽ “ገብርኤል ብሒል ብእሲ ወአምላክ” ገብርኤል ማለት ሰውና አምላክ ማለት ነው ተብሎ ስለሚተረጎም “ወራብኡሰ ይመስል ከመ ወልደ እግዚአብሔር” አራተኛው የእግዚአብሔርን ልጅ ይመስላል በማለት የተገለጠው መልአከ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል መሆኑን በግብፅ ያሳያል፡፡ ከታሪኩ እንደምንረዳው የእግዚአብሔር መልአክ ዋና አገልግሎት እግዚአብሔርን ማመስገን (ኢሳ 6፤1) ቢሆንም አማኞችንም በማገልገል ይታወቃል(ዕብ 1፤14) ንስሐ በሚገባ ሰውም ደስ ይለዋል (ሉቃ 15፤10)
እግዚአብሔርን የሚፈሩትን ሰዎችም ይጠብቃል (መዝ 34፤7) ኃጢአተኞችንም ይቀጣል፡፡ (ዘካ፤ 4)
(መምህር ሣህሉ አድማሱ)