“ይኩንኪ በከመ ተአመንኪ” (እንዳመንሽ ይሁንልሽ)
ይህ ቃል ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለከነናዊት ሴት የተናገረው ቃል ነው፡፡ ታሪኩም/በማቴዎስ ወንጌል ም. 15፡21-28/ ላይ ይገኛል፡፡ ታሪኩም እንደሚከተለው ነው፡፡
ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ጢሮስና ወደ ሲዶና አገር ሄደ፡፡ በዚያም ከነናዊት ሴት ጌታ ሆይ! የዳዊት ልጅ ማረኝ ልጄን ጋኔን ክፉኛ ይዟታል ብላ ጮኸች፡፡ እርሱ ግን ለጊዜው አንዳች አልመለሰላትም፡፡ ደቀ መዛሙርቱም ወደ እርሱ ቀርበው በኋላችን ትጮኻለችና አሰናብታት እያሉ አማለዷት፡፡ እርሱም መልሶ ከእስራኤል ቤት ለጠፋት በጎች በቀር አልተላክሁም አለ፡፡ ይህም ማለት ትምህርት፣ መምህር አጥተው የተጎዱ እስራኤልን ላስተምር ሰው ሆኛለሁ ማለቱ ነው፡፡ እርሷ ግን ጌታ ሆይ፡- እርዳኝ እያለች ሰገደችለት፡፡ እርሱ ግን መልሶ የልጆችን እንጀራ ለውሾች መስጠት አይገባም አለ፡፡ እርስዋም አዎን ጌታ ሆይ፡- ውሾችም እኮ ከጌቶቻቸው ማዕድ የወደወቀውን ፍርፋሪ ይበላሉ አለች፡፡ የልጆችን እንጀራ ለውሾች መስጠት አይገባም ሲል የምስጢር ባለቤት መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተናገረውን ቃል አባቶቻችን ሊቃውንት ሲያመሰጥሩት ለእስራኤል የማደርገውን ተአምራት ለአሕዛብ አላደርገውም ማለት ነው፡፡ ይህች ከነናዊት ሴት ከአሕዛብ ወገን ናትና፡፡ እርሷም የሰጠችው መልስ ውሾችም እኮ ከጌቶቻቸው ማዕድ የወደቀውን ፍርፋሪ ይባላሉ፡፡ የዚህም ምስጢር ለእስራኤል ደጋጉን ተአምራት ብታደርግላቸው ለኔ ደግሞ ጥቃቅኑን ተአምራት አታደርግልኝም? ማለት ነው፡፡
በዚህን ጊዜ የምሕረት ባለቤት አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ መልሶ አንቺ ሴት እምነትሽ ታላቅ ነው፡፡ “ይኩንኪ በከመ ተአመንኪ” (እንዳመንሽ ይሁንልሽ አላት) ከዚያች ሰዓት ጀምሮ ልጇ ዳነች፡፡
ሊቃውንት እንደሚያመሰጥሩት ይህች ከነናዊት ሴት ሶስት ነገሮችን ይዛ ስለተገኘች ልጇ ድናላታለች፡፡ እነዚህም ሶስት ነገሮች ሃይማኖት፣ ትሕትና፣ ጥበብ ናቸው፡፡ ሃይማኖት፡- ልጄን ያድንልኛል ብላ ሳትጠራጠር በፍጹም እምነት መቅረቧ ነው፡፡ ትሕትና፡- የልጆችን እንጀራ ለውሾች መስጠት አይገባም ሲላት ውሾችም እኮ ከጌቶቻቸው ማዕድ የወደቀውን ፍርፋሪ ይበላሉ በማለት መልስ መስጠቷ ነው፤ ጥበብ መስሎ ቢነግራት መስላ መናገር ነው፡፡
ከመጀመሪያው ከሃይማኖት ስንጀምር ሃይማኖት እምነት ነው፡፡ ለመንፈሳዊ ሕይወት መሠረቱ እምነት ነው፡፡ እየተጠራጠርን የምናቀርበው ልመና ከደመና በታች ነው የሚቀረው ለዚህም ቅዱስ ያዕቆብ የተናገረው ቃል ትልቅ ማስረጃ ነው፡፡ ይህም “የሚጠራጠር ሰው በነፋስ የተገፋና የተነቃነቀ የባሕርን ማዕበል ይመስላል” /ያዕ. 1፡6/ ስለዚህ እምነተ ጠንካራ መሆን ያስፈልጋል፡፡
ሁለተኛ ከነናዊቷ ሴት ገንዘብ ያደረገችው ትሕትናን ነው፡፡ ትሕትና፡- ራስን ዝቅ አድርጎ ሌላውን ከፍ ማድረግ ነው፡፡ “ራሱን ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ዝቅ ይላልና ራሱንም የሚያዋርድ ከፍ ይላል” /ሉቃ. 14፡11/ ትሕትናን መጀመሪያ ያስተማረን የትሕትና ባለቤት መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው የጸሎተ ሐሙስ ዕለት የቅዱሳን ሐዋርያትን እግር አጥቦ “እኔ እግራችሁን እንዳጠብኳችሁ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ እግራችሁን ትተጣጠቡ ዘንድ ይገባችኋል እኔ ለእናንተ እንዳደረግሁ እናንተ ደግሞ ለሌሎች ታደርጉ ዘንድ ምሳሌ ሰጥቻችኋለሁና” /ዮሐ. 13፡14/ በዚህ መሠረት ትሕትናን ገንዘብ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
ሦስተኛ ከነናዊቷ ሴት ይዛ የተገኘችው ጥበብን ነው፡፡ የጥበብ ሁሉ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው “የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው” /መዝ. 110፡10/፣ /ምሳ. 9፡10/ በማለት ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊትና ታላቁ ንጉሥ ሰሎሞን ተናግረዋል፡፡ እንዲሁም “ቀኑን ሙሉ እግዚአብሔርን በመፍራት ኑር በእውነት ፍጻሜ አለህና ተስፋህም አይጠፋምና፡፡” /ምሳ. 23፡ 17-18/ ሲል ሰሎሞን የተናገረው ቃል በመዋዕለ ዘመናችን ሁሉ እግዚአብሔርን በመፍራት እንድንኖር ነው፡፡ ስለዚህ የጥበብ፣ የዕውቀት መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት በመሆኑ እግዚአብሔርን በመፍራት መኖር ያስፈልጋል፡፡ ጥበብን ገንዘብ ማድረግ እንደሚገባም ‹‹ኩኑ ጠቢባነ ከመ አርዌ ምድር ወየዋሃነ ከመ ርግብ›› ( እንደ እባብ ብልሆች እንደ ርግብ የዋሆች ሁኑ) /ማቴ 10÷16/ ሲል መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተናገረው ጥበብ አስፈላጊ መሆኑን ለመግለጽ ነው፡፡ ስለዚህ ጥበብን መያዝ ያስፈልጋል፡፡
ሃይማኖት፣ ትሕትና፣ ጥበብ፣ እነዚህን ይዘን በመገኘት በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት እንዲሁም በቅዱሳን አማላጅነት መንግሥተ ሰማያትን እንድንወርስ ልዑል እግዚአብሔር ወሰን በሌለው ችርነቱ ይርዳን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
(ላዕከ ወንጌል በእደ ማርያም ይትባረክ (ቀሲስ) የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የትምህርት ሥርጭት ኃላፊ)