ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ በሕንድ ኬሬላ ለስድስት ቀናት ያደረጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት አጠናቅቀው ተመለሱ

                                                                                                  በመምህር ሙሴ ኃይሉ

p033

ከአምስቱ አኀት አብያተ ክርስቲያናት መሪዎች መካከል አንዱ የሆኑት የሕንድ ማላንካራ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ፓትርያርክ ካቶሊኮስ ባስልዮስ ማርቶማ ጳውሎስ ዳግማዊ የህንድን ቤተ ክርስቲያን እንዲጎበኙ ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ባደረጉላቸው ጥሪ መሠረት ጎብኝተዋል፡፡
ቅዱስ ፓትርያርኩ ኬሬላ አየር ማረፊያ ሲደርሱም የሕንድ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳሳት፣ በሕንድ የኢትዮጵያ አምባሳደር የሆኑት ክቡር አቶ አሰፋው ዲንጋሞና የኤምባሲው ሠራተኞች በሕንድ ከሚኖሩ ኢትዮጵያን ጋር በመሆን ደማቅ አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡
በመቀጠልም የሕንድ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ካቶሊኮስ ከብፁዓን ሊቃነ ጳጰሳት ጋር በመሆን ደማቅ የሆነ ይፋዊ የእንኳን ደህና መጣችሁ አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡
የሕንድ ማላንካራ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ፓትርያርክ ካቶሊኮስ ባስልዮስ ማርቶማ ጳውሎስ ዳግማዊ በአቀባበሉ ባስተላለፉት መልእክታቸው በዋናነት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ የሕንድን ቤተ ክርስቲያን እንዲጎበኙ ለረጅም ጊዜ ሲመኙ የነበረ መሆኑን በመግለጽ የቅዱሳን ፓትርያርኮች ጉብኝት ከአብያተ ክርስቲያናቱ በተጨማሪ የሁለቱንም ሀገሮች ሕዝቦች ሁለንተናዊ ግንኙነት ወደ ተሻለ ደረጃ የማድረስ አቅም እንዳለው በስፋት አብራርተዋል፡፡
በመቀጠልም የኢትዮጵያና የሕንድ ኦርቶዶክሳውያን አብያተ ክርስቲያናት አንድ ዓይነት ትምህርተ ሃይማኖት የሚከተሉ፣ ከጥንት ጀምሮ ተከባብረውና ተፈቃቅረው የሚኖሩ መሆናቸውን ጠቅሰው ይህ ታሪካዊ የብፁዕ ቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ጉብኝትም የቆየውን ግንኙነት ወደ ተሻለ ትብብርና ስምምነት የሚያሸጋግር መልካም አጋጣሚ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ በበኩላቸው ከቀደምት አብያተ ክርስቲያናት መካከል ከሆነችውና በሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ የተመሠረተችውን የሕንድ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን ለመጎብኘት በመብቃታቸው የተሰማቸውን መንፈሳዊ ደስታ ገልጸው ከሁለቱም አብያተ ክርስቲያናት በተጨማሪ ኢትዮጵያንና ሕንድን ብዙ የሚያመሳስላቸው ነገሮች መኖራቸውን፣ የቋንቋና የብሔር ብሔረሰብ ብዝኅነትንና በፍቅር ተስማምቶ የመኖር ዕሴቶቻቸውን እንደ ምሳሌ በመጥቀስ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ የኢትዮጵያና የሕንድ በፍቅርና በመተሳሰብ ላይ የተመሠረተ ግንኙነትም ቅድመ ልደተ ክርስቶስ ከአክሱም ዘመነ መንግሥት ጀምሮ የቆየ መሆኑን ታሪካዊ ገለጻ ካደረጉ በኋላ ብዙ ሕንዳውያን ለሥራ በኢትዮጵያ ሲኖሩ እንደቤታቸው ሆነው መኖራቸው፤ እንዲሁም ብዙ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ለጥናትና ምርምር ሕንድን መምረጣቸው የቆየው የሁለቱንም ሀገሮች የመልካም ግንኙነት ተምሳሌታዊ ምስክር መሆኑን ገልጸው ስለተደረገላቸው አቀባበልም ከፍተኛ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በሕንድ የኢትዮጵያ አምባሳደር የሆኑት አቶ አሰፋ ዲንጋሞ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉ ሲሆን በንግግራቸው ትኩረት የሰጡት የሁለቱም ኦርቶዶክሳውያን አብያተ ክርስቲያናት ግንኙነት ጥንታዊ መሆኑንና ይህ መልካም የሃይማኖት ግንኙነትም የሁለቱም ሕዝቦች ግንኙነት በመተማመን እና በመተባበር ላይ የተመሠረተ እንዲሆን ማስቻሉን ታሪካዊ ክስተቶችን ጠቅሰው መልእክት አስተላልፈዋል፡፡ አያይዘውም የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ ሐዋርያዊ ጉብኝት የቆየውን የመንግሥት ለመንግሥት መልካም ግንኙነት ከማጠናከር በተጨማሪ በሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ግንባር ቀደም ጠቀሜታ እንደሚኖረው አስታውቀዋል፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ በሕንድ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ለስድስት ቀናት ባደረጉት ጉብኝት አንድ ዓለም አቀፍ የካንሰር ሕሙማን መርጃ ሆስፒታልን ጨምሮ በርካታ በቤተክርስቲያኗ የተሠሩ የልማት ተቋማትን ባርከው በመክፈት ተዘዋውረውም ጎብኝተዋል፡፡ ሁለቱም ፓትርያርኮች ባደረጉት ውይይትም በሁለቱም ጥንታውያን አብያተ ክርስቲያናት ሁለተናዊ ግንኙነት መጠናከር ዙርያ በስፋት ከተወያዩ በኋላ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ለሕንድ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ካቶልኮስ ባስልዮስ ማርቶማ ጳውሎስ ደግማዊ በሀገራችን የሚከበረውን የመስቀል ደመራ በዓል አከባበር ምክንያት በማድረግ በመስከረም 16 ቀን 2010 ዓ.ም ኢትዮጵያን እንዲጎበኙ ያቀረቡላቸውን ግብዣ በደስታ መቀበላቸውን ገልጸዋል፡፡
ፓትርያርኩ በቆይታቸው እጅግ በጣም ብዙ ሕዝብ ተሰብስቦ በሚከበርባቸው ዓበይት በዓላት ላይ ተገኝተው መልእክት ያስተላለፉ ሲሆን በቅዱስ ፓትርያርኩ የተመራው የቤተ ክርስቲያኒቷ የቅዱስ ሲኖዶስ ልዑክ በሕንድ ያደረጉትን ቆይታ አጠናቅቀው አዲስ አበባ ገብተዋል፡፡
ቅዱስነታቸው አዲስ አበባ ሲደርሱ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ጉብኝቱ የተሳካና ውጤታማ የሆነ፣ የሁለቱን አብያተ ክርስቲያናት ግንኙነት የተጠናከረ እንዲሆን ከፍተኛ አስተዋፅኦ የሚያደርግ እንደነበር ገልጸዋል፡፡