የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በ2008 ዓ.ም የበጀት ዓመት ባስመዘገበው ከፍተኛ የፐርሰንት ገቢ እድገት ልዩ ተሸላሚ መሆኑ ተገለጸ!!

20090

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በ2008 ዓ.ም የበጀት ዓመት በርዕሰ ከተማው ከሚገኙት ገዳምትና አድባራት በሰበሰበው የላቀ የፐርሰንት ገቢ እድገት በ2009 ዓ.ም በተካሄደው 35ኛ መደበኛ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ላይ ልዩ ተሸላሚ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡
ሀገረ ስብከቱ በ2007 ዓ.ም ካስመዘገበው የፐርሰንት ገቢ የብር 30 ሚሊዮን ብልጫ በማሳየት ልዩ ተሸላሚ ለመሆን በቅቷል፡፡

ሀገረ ስብከቱ በ2008 ዓ.ም የበጀት ዓመት በመልካም አስተዳደር፣ በልማትና በፐርሰንት ገቢ አሰባሰብ ከወትሮው በተሻለ ሁኔታ የላቀ እድገት ያስመዘገበ በመሆኑ የተነሳ ከብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ እጅ የምስክር ወረቀት እና ከሰባት ያላነሱ ዘመናዊ ኮምፒውተሮች ተሸልሟል፡፡
በሽልማት የተባረኩት ሰባት ዘመናዊ ኮምፒውተሮች በርእሰ ከተማው ለሚገኙት ሰባት የከፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤቶች አገልገሎት እንዲሰጡ ለማድረግ የታሰበ መሆኑን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ በጉባኤው ለተገኘው ተሰብሳቢ በይፋ አብራርተዋል፡፡
የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ መምህር ጎይተኦም ያይኑ ለተሰብሳቢው ባቀረቡት ሪፖርት እንዳብራሩት በ2009 ዓ.ም የበጀት ዓመት ሀገረ ስብከቱ የላቀ የፐርሰንት ገቢ እድገት፣ የመልካም አስተዳደር እና የልማት እድገት በሀገረ ስብከቱ ዓመታዊ መሪ እቅድ እንደተመዘገበ አብራርተዋል፡፡