“የመስቀሉ ነገር ለሚጠፉት ሞኝነት ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚብሔር ኃይል ነው” 1ኛ. ቆሮ. 1÷18
መስቀል፡- ምስጢራዊ ትርጉሙ መከራ ማለት ነው፡፡ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቅዱስ ወንጌል ‹‹ዘኢጾረ መስቀለ ሞትየ ኢይክል ይጸመደኒ›› (የሞቴን መስቀል የማይሸከም ይከተለኝ ዘንድ አይችልም) /ማቴ. 16÷24/ ሲል የተናገረው ቃል መስቀል መከራ መሆኑን የሚገልጽ ነው፡፡
ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ከተሰቀለ በኋላ ሕሙማን መስቀሉን እየዳሰሱ በመስቀሉ እየታሹ ይፈወሱ ነበር፡፡ በዚህ በመስቀሉ በሚደረገው ተአምራት እየተሳቡ ብዙዎች ክርስቲያን ሆኑ፡፡ ይህንን ያዩ አይሁድ መስቀሉን ቀበሩት ለሦስት መቶ ዓመታት ተቀብሮ ቆየ፡፡ በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በ327 ዓ.ም የንጉሥ ቆስጠንጢኖስ እናት ንግሥት ዕሌኒ ይህን ታሪክ ትሰማ ነበርና መስቀሉን አስቆፍራ ለማስወጣት ወደ ኢየሩሳሌም ሄደች፡፡ እዚያም ደርሳ ጉብታ የሆነውን ሁሉ ብታስቆፍር መስቀሉ ያለበትን አላገኘችውም፡፡ ሰውም ብትጠይቅ የሚያውቅላት አላገኘችም በመጨረሻ ግን የመስቀሉ መውጣት የእግዚአብሔር ፈቃዱ ነበርና አንድ ኪራኮስ የሚባል ሽማግሌ የዕሌኒን መቸገር አይቶ እንደሚከተለው ይመክራታል፡፡ እንጨት አሰብስበሽ ከምረሽ ዕጣን አፍሺበት በእሳትም አያይዢው የዕጣኑ ጢስ ወደላይ ወጥቶ ወደታች ሲመለስ መስቀሉ ያለበትን ቦታ ሰው በጣት ጠቅሶ እንደሚያሳይ ያመለክትሻል አላት፡፡ እርሷም ያላትን ሁሉ አደረገች፡፡ የዕጣኑ ጢስ ወደላይ ወጥቶ መስቀሉ የተቀበረበትን ቦታ አሳያት ይህንንም አስመልክቶ መሠረተ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ያሬድ በዜማ ድርሰቱ ‹‹ዘዕጣን አንጸረ ሰገደ ጢስ›› (የዕጣኑ ጢስ መስቀሉ ያለበትን ቦታ አሳየ) ሲል ተናግሯል፡፡ ወዲያው ማስቆፈር ጀመረች ስታስቆፍር ቆይታ መጋቢት 10 ቀን መስቀሉ ከተቀበረበት ቦታ ወጥቷል፡፡
በዚህ መሠረት መስቀልን የምናከብርበት ምክንያት ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተሰቅሎ ዓለምን ስላዳነበትና በክቡር ደሙ ያከበረው በመሆኑ ነው፡፡
መስቀል በብሉይ ኪዳን ብዙ ምሳሌ አለው የኖኅ መርከብ የተሠራችበት እንጨት፣ የሙሴ በትር የመስቀል ምሳሌዎች ናቸው፡፡ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ሌላ ትምክህት ከእኔ ይራቅ›› /ገላ. 6÷14/ ሲል የተናገረው የመስቀሉን ክብርና ኃይል የሚገልጽ ነው፡፡
በአገራችን ክርስቲያኖች በግንባራቸውና በሌላውም አካላቸው በመስቀል ቅርጽ ይጠቆራሉ እንዲሁም ልብሳቸው ላይ በጥልፍ የመስቀል ቅርጽ ያደርጋሉ፡፡ ይህ ሁሉ የሚያመለክተው ክርስቲያኖች ለመስቀሉ ልባዊ ፍቅር ያላቸው መሆኑን ነው፡፡ መስቀል በሕይወተ ሥጋ ሳለን ብቻ ሳይሆን ከሞትንም በኋላ ከእኛ አይለይም አጽማችን በሚያርፍበት በመቃብራችን ላይ ይደረጋል ይህም የትንሣኤያችን ምልክት ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ብዙዎች ለክርስቶስ መስቀል ጠላቶቹ ሆነው ይመላለሳሉና ብዙ ጊዜ ስለ እነርሱ አልኳችሁ አሁንም እንኳን እያለቀስኩ እላለሁ መጨረሻቸው ጥፋት ነው ሆዳቸው አምላካቸው ነው ክብራቸው በነውራቸው ነው አሳባቸው ምድራዊ ነው እኛ ግን አገራችን በሰማይ ነው፡፡ ፊልጵ. /3÷18-19/ በማለት የተናገረው ለመስቀሉ ትልቅ ፍቅር እንዲኖረን ነው፡፡ ለመስቀል መስገድ እንደሚገባ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃ አለ፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት ‹‹ወንሰግድ ውስተ መካን ጎበ ቆመ እግረ እግዚእነ›› (እግሮቹ በሚቆሙበት ስፍራ እንሰግዳለን) /መዝ. 131÷7/ ሲል የተናገረው ለመስቀል መስገድ እንደሚገባ የሚገልጽ ነው፡፡ የሰላም ንጉሥ መድኃኔዓለም ክርስቶስ እኛን ለማዳን በመስቀል ላይ ሲሰቀል እግሮቹ ከመስቀሉ ጋር ተቸንክረዋል በዚህ መሠረት እግሮቹ በሚቆሙበት ስፍራ እንሰግዳለን ሲል ለመስቀሉ እንሰግዳለን ማለት ነው፡፡
በኦሪት ዘጸአት /14÷15-31/ እንደተጻፈው በሙሴ በትር፣ ድንቅ ድንቅ ተአምራት ተደርጓል በሙሴ በትር ተአምራት ከተደረገ አምላካችን በተሰቀለበት መስቀል እንዴት ተአምራት አይደረግ? በዚህ መሠረት መስቀል በቤተ ክርስቲያናችን ሕይወት ውስጥ ከፍተኛ ክብር አለው፡፡ መስቀል የድልና የነጻነት ምልክት ነው፡፡
‹‹የመስቀሉ ነገር ለሚጠፉት ሞኝነት ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነው›› እንዳለ ቅዱስ ጳውሎስ በረከተ መስቀሉ የሚደርሳቸው ላመኑ ሰዎች እንጂ ላላመኑ አይደለም፡፡ ስለዚህ በረከተ መስቀሉ እንዲደርሰን ጽኑ እምነትን ገንዘብ እናድርግ፡፡
ጽኑ እምነትን ገንዘብ አድርገን ሕጉን ትእዛዙን ጠብቀን በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት እንዲሁም በቅዱሳን አማላጅነት ሀገረ ሕይወት መንግሥተ ሰማያትን እንድንወርስ ልዑል እግዚአብሔር ወሰን በሌለው ቸርነቱ ይርዳን፡፡ ወስብሐት ለእግዚአብሔር
(ላዕከ ወንጌል በእደ ማርያም ይትባረክ (ቀሲስ) የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የትምህርት ሥርጭት ኃላፊ)