የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤት የ2009 ዓ.ም የሥራ እቅዱን ይፋ አደረገ!!
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይኖት የ2009 ዓ.ም ዓለም አቀፋዊ የሆነውን ሐዋርያዊ እና አስተዳደራዊ አገልግሎትን አስመልክቶ በልዩ ጽ/ቤት የተዘጋጀው ሰፊ የሥራ እቅድ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የአስተዳደር ጉባኤ መሰብሰቢያ አዳራሽ የጠቅላይ ቤተ ክህነት የየመምሪያ ኃላፊዎች በተገኙበት ሐሙስ መስከረም 5 ቀን 2009 ዓ.ም በቆሞስ አባ ሠረቀ ብርሃን ወልደ ሳሙኤል የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጸሐፊ አቅራቢነት በእስላይድ በታገዘ የጽሑፍ መሪ እቅድ ቀርቧል፡፡
በእቅዱ አላማ እና ዝርዝር ላይ በርካታ ነጥቦች የተካተቱ ሲሆን የእቅዱ ዋና መነሻ ምክንያትም ልዩ ጽ/ቤቱ በመዋቅራዊ ቁመና የጸደቀ መመሪያ እንዲኖረው ታስቦ የተዘጋጀ መሪ እቅድ መሆኑ በእቅዱ አንቀጽ ላይ ተገልጿል፡፡ እቅዱ የልዩ ጽ/ቤቱ አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ባለ ጉዳዮች በእኩልነትና በአግባቡ እንዲስተናገዱ ለማድረግ እና በአንዳንድ ግለሰቦች የሚባክነውን የቤተ ክርስቲያን ንብረት ለመጠበቅ የሚሰጠው ጥቅም የጎላ መሆኑን ጠቁሟል፡፡ በእቅዱ ዋና ዋና ተግባራት መሠረት መመሪያዎችን ማሠራጨት፣ ቅድመ ሁኔታዎችን ማስተካከል፣ አስፈላጊውን ድጋፍ መስጠት እና ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በመቀራረብ መሥራት ነው፡፡
የእቅዱ መመሪያ በመጽሔቶች፣ በበራሪ ጽሑፎች እና በመሳሰሉት በማዘጋጀት ጉዳዩ ለሚመለከተው ሁሉ እንዲደርሰው ይደረጋል፡፡ ከአሀት አቢያተ ክርስቲያናት ጋር ያለው ግንኙነትም ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ የላእላይ እና የታእታይ መዋቅርን በማጠናከር ሐዋርያዊ ጉዞ የሚደረግባቸው አህጉረ ስብከቶች ተለይተው እንዲታወቁ በማድረግ የተሟላ አገልግሎት ይሰጣል፡፡
የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ታሪካዊ ሥራዎችን የያዘ መጽሐፍ በተመረጠ ማተሚያ ቤት ታትሞ አገልግሎት ላይ ይውላል፡፡ በዓበይት በአላት የሚተላለፉ መልእክቶች ተለይተው ይታወቃሉ፡፡ በወቅታዊ ችግሮች ዙሪያ የሚተላለፉት አጽናኝ እና አስተማሪ መልእክቶች ይዘጋጃሉ፡፡
ዜና ልሳነ ፓትርያርክ በሚል ርዕስ ተከታታይነት ባለው መልኩ እና በተለያዩ ቋንቋዎች በመጽሔትና በጋዜጣ እየታተመ ለምእመናን እንዲሰራጭ ይደረጋል፡፡ አስፈላጊ በሆኑ ወቅቶች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናዎችም ይሰጣሉ፡፡
የብፁዕ ወቅዱስ ልዩ ጽ/ቤት የቤተ ክርስቲያኒቱ ላእላይ ተቋም እንደ መሆኑ መጠን ጥራቱን የጠበቀ የቪአይፒ አሰራር እንዲኖር ይደረጋል፡፡ የአበው ሊቃነ ጳጳሳት ጤንነት እንዲበቅ አስፈላጊው ተግባር ይከናወናል፡፡
በሕገ ቤተ ክርስቲያን አንቀጽ 50 ላይ በተደነገገው መሠረት የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ሀገረ ስብከት በመሆኑ የተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ ከመቼውም በተሻለ መልኩ ተጠነክሮ እንዲቀጥል፣ መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን የፋይናንስ አያያዝ እንዲሻሻል፣ የሰው ኃይል አደረጃጀት እንዲፈተሽ ይደረጋል፡፡ የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔዎች ተፈጻሚ እንዲሆኑ እና የቅዱስ ሲኖዶስን ሉአላዊነት የሚጋፉት ኃይሎች ስርአት እንዲይዙ ይደረጋል፡፡ የገዳማት የቀጣይ ታሪካዊ ህልውና እንዲጠበቅ እና ቅርሶቹም አስፈላጊ እንክብካቤ ይደረግላቸዋል፡፡ ምሁራንን በማሳተፍ የቤቶች ልማት ሥራ እንዲስፋፋ ይደረጋል፡፡ ለአብነት መምህራን፣ ለሰባክያን፣ ለመንፈሳዊ ኮሌጆች እና ለሰንበት ት/ቤቶችም አስፈላጊውን እንክብካቤ ይደረግላቸዋል፡፡ አስፈላጊ በሆኑ እና በተመረጡ የትምህርት ዘርፎች ላይ ለዲግሪ መርሐ ግብር፣ የእስኮላር ሺፕ እድል ይመቻቻል፡፡ ከዓለም አብያተ ቤተ ክርስቲያናት ጋር በሚያገናኙን ጉዳዮች ዙሪያ ጠንካራ ግንኙነት እንዲፈጸም ይደረጋል የሚሉት የእቅዱ ዋና ዋና ይዘቶች ሲሆኑ በቀረበው ዝርዝር የእቅድ ሪፖርት መሠረት የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት የየመምሪያ ኃላፊዎች ገንቢ የሆኑ አስተያየቶችን ለግሰዋል፡፡
በተመሳሳይ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የመሰብሰቢያ አዳራሽ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ረዳት እና የከፋ ሸካ ቤንጂ እና ማጂ አህጉረ ስብከት፣ የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ ሊቀ ጳጳስ፣ መምህር ጎይተኦም ያይኑ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የአገረ ስብከቱ የዋና ክፍል ኃላፊዎች፣ የሰባቱ ክፍላተ ከተማ የሥራ ኃላፊዎች እና ሠራተኞች በተገኙበት አርብ መስከረም 6 ቀን 2009 ዓ.ም የልዩ ጽ/ቤት እቅድ በድጋሚ በቆሞስ አባ ሠረቀ ብርሃን ወልደ ሳሙኤል ቀርቧል፡፡ እቅዱ በቀረበበት ወቅት ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል ባስተላለፉት አባታዊ መልእክት አከለክሙ ዘሐለፈ መዋዕል… በሚል መጽሐፋዊ ቃል ተነስተው የዕቅድ ጀማሪ እና ፈጻሚ አምላካችን እግዚአብሔር መሆኑ በማብራራት የቀረበው መሪ እቅድ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በመሪ እቅዱ አቀራረብ ወቅት ንቁ ተሳትፎ ያደረጉት ተሳታፊዎች ተጨማሪ ግብአት የሚጠቅሙ አስተያየቶችን በመስጠት የእቅዱን ይዘት እና ዝርዝር ተግባራት በማድነቅ ተፈጻሚ እንዲሆን ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡