ቆሞስ አባ ሠርቀ ብርሃን ወልደ ሳሙኤል የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጸሐፊ ሆነው ተመደቡ!!
ከአዲሱ የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጸሐፊ ከቆሞስ አባ ሠርቀ ብርሃን ወልደ ሳሙኤል ጋር በቤተ ክርስቲያናችን ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ የተደረገ ቃለ ምልልስ፡፡
የተከበሩ አባታችን መምህርና ቆሞስ አባ ሠርቀ ብርሃን ወልደ ሳሙኤል እንደ እግዚአብሔር ቸርነትና ፈቃድ የብፁዕ ወቅዱስ አባታችን ልዩ ጸሐፊ ሆነው የተመደቡ መሆነዎ ይታወቃል፡፡ በዚህ ዓለም አቀፋዊ የቤተ ክርስቲያናችን ልዩ ጽ/ቤት በመመደበዎ ምን ተሰማዎት?
ቆሞስ አባ ሠርቀ ብርሃን ወልደ ሳሙኤል
የብፁዕ ወቅዱስ አባታችን አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ልዩ ጽ/ቤት አገልጋይ ሆኜ በመመደቤ የተሰማኝ ደስታ በሁለት ይመደባል፡፡
በሰለጠነው ዓለም ከነበሩትና በገዳም ካሉት አባቶቻችን በበለጠ የምናኔ ሕይወት ካላቸው ቅዱስ አባት ሥር ሆኜ አመራር እየተቀበልኩኝ ለመሥራት መብቃት እጅግ መታደል ስለሆነ በቅዱስ አባታችን ልዩ ጽ/ቤት አገልጋይ ሆኜ በመመደቤ ትልቅ በረከትና ዕድል ነው እላለሁ፡፡ ቅዱስ አባታችን መንኖ ጥሪት ያላቸው ማለትም ለሌላ መሆን እንጂ ለራስ አለመሆንን ያየንባቸው አባት ናቸው፡፡
በሌላ በኩል የተሰጠኝ ኃላፊነት እጅግ ከባድ ነው፤ ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን ከክርስቶስ በታች የቤተ ክርስቲያን ርዕሰ መንበር ናቸው፤ ርዕሰ አበውም ናቸው፤ በዚህ ታላቅ ጽ/ቤት የሚከናወኑ ሥራዎችም እጅግ በርካታዎች ናቸው፤ ዓለም አቀፍና ሀገር አቀፍ ጉዳዮች ሁሉ ወደዚህ ጽ/ቤት ነው የሚጎርፉት ስለዚህ ይህ ታላቅ ጽ/ቤት ያለው ኃላፊነት እጅግ በርካታ ከመሆኑ አንጻር ይህንን በሚገባና በትክክል ለማስኬድ ከፍተኛ ኃላፊነትና ከፍተኛ ጥረት እንደሚጠይቀኝ ስለሚረዳኝና ስለሚገባኝ የቅዱስ አባታችንና የብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ጸሎት አግዞኝ እችለዋለሁ ብዬ አምናለሁ እንጂ በዚህ ከባድ ተልዕኮ ውስጥ በመሆኔ የእግዚአብሔርን ርዳታ እጠይቃለሁ፡፡
ወደ ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን ልዩ ጽ/ቤት በጸሐፊነት ከመምጣተዎ በፊት በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት የትምህርትና ማሰልጠኛ መምሪያ ኃላፊነት ሆነው ሢሠሩ መቆየተዎ ይታወቃል፤ ስለሆነም በመምሪያው ያከናወኑአቸው ዋና ዋና ተግባራት ምን ምን ነበሩ?
ቆሞስ አባ ሠርቀ ብርሃን ወልደ ሳሙኤል
ከሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ወደ ትምህርትና ማሰልጠኛ መምሪያ ነው የተዛወርኩት ከሰንበት ት/ቤት መምሪያ በተነሳሁበት ጊዜ በዚያ ያበረከትኳቸውን የሥራ አስተዋፅኦዎች ከግምት በማስገባትና በመመልከት በረከታቸው ይድረሰንና ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ እና በአሁኑ ጊዜ በሕይወተ ሥጋ የተለዩን አባታችን አቡነ ፊልጶስ መልካም ፈቃድና ውይይት መሠረት የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ምክትል ሥራ አስኪያጅ ሆኜ ነበር በመጀመሪያ የተመደብኩት፤ ያም ሆነ ይህ በፈቃደ እግዚአብሔር በወቅቱ ልሠራበት የተመቻቸልኝ የትምህርትና ማሰልጠኛ መምሪያ ስለነበር በዚያ መምሪያ ተመደብኩኝ፡፡ የትምህርትና ማሠልጠኛ መምሪያ የቤተ ክርስቲያናችን የጀርባ አጥንት ነው፤ትምህርት ከሌለ ምንም ነገር የለም፤ ምንም እንኳን ቀደም ሲል ከሌሎቹ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት መምሪያዎች መካከል ትምህርትና ማሠልጠኛ መምሪያ አናሳ ተደርጎ ቢታይም ገና በሀገራችን በኢትዮጵያ ዘመናዊ ትምህርት ቤት ገብቶ ሥራ ከመጀመሩ በፊት እንደ ትምህርት ሚንስተር ሆኖ የትምህርትና ማሠልጠኛ ባይባልም የቤተ ክህነት ትምህርት ቤት እየተባለ ሲመራ የነበረ ተቋም ነው፡፡
ስለዚህ ወደዚህ መምሪያ ከመጣሁ በኋላ መምሪያውን ያገኘሁት እጅግ ተዳግሞ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ብዙ አባቶች መምሪያውን እየመሩ የቆዩ ሲሆን ከማኅደረ ጉዳዩ እንደተረዳሁት መምሪያውን ከወደቀበት ለማንሳት ያላደረጉት ጥረት የለም፡፡ ነገር ግን የዘመኑ ትምህርት እያየለ ሲመጣ የነገሥታቱ፣ የመኳንንቱ እና የብፁዓን አባቶች ዝንባሌ ወደዚያ እየገፋ ሲሄድ የአብነት ትምህርት ቤቶች ወደ ኋላ እየቀሩ በመሆናቸው በዚሁ ስጋት የተሰማቸው አባቶች ሲጮኹ ቆይተዋል፡፡ የነሱ ጩኸት ለመምሪያው በር እንዲከፍት አድርጓል፡፡ ይህም ማለት የራሱ ቢሮ፣ የተሟላ የጽፈት ቤት ማቴሪያል እና የራሱ የሰው ኃይል እንዲኖረው ተደርጓል ማለት ነው፡፡ ካለፈው ዓመት ጀምሮ አሁን እስከደረስንበት ድረስ ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን በተገኙበት የተለያዩ ስልጠናዎችን ሰጥተናል፤ በዚህም ስለ አብነት ት/ቤቶች እጅግ ሰፋ ያለ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ሰጥተናል፤ ከዚያ ቀጥሎ ትንሣኤ ለአብነት ት/ቤቶች እና ለአብነት መምህራን በሚል ርዕስ ከፍተኛ የሆነ ሥራ ሥንሰራ ቆይተናል፤ በተለይ ደግሞ በ2008 ዓ.ም ተደርጎ የማይታወቀው በ38 አህጉረ ስብከት እስከ ገጠሪቱ ሀገራችን በየገዳማቱና በየአድባራቱ ያሉትንና የተረሱትን የአብነት ትምህርት ቤቶች፣ መምህራንና ደቀ ማዛሙርት እንዲጎበኙ ተደርጎ በብፁዕ ወቅዱስ አባታችን አቡነ ማትያስ መሪነት በወቅቱ በነበሩት ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ በብፁዕ አቡነ ማቴዎስ አመራር ሰጪነት እስከ ገጠሪቱ የደረሰ የዳሰሳ ጥናት አደርገናል፤ እነዚህን ሁሉ ስናያቸው ወደዚህ ልዩ ጽ/ቤት እስከ መጣሁበት ጊዜ ድረስ ለ2009 ዓ.ም የዕቅድ አቅጣጫ አመላክቼ ነው የመጣሁት፤ ይህም አሠራር ትልቅ የሆነ ለውጥ ያሳየንበት ነው፡፡
የገዳማዊ ሕይወትዎን፣ የመንፈሳዊ ትምህርት ዕውቀትዎን እና የዘመናዊ ትምህርት ደረጃዎን ቢነግሩን?
ቆሞስ አባ ሠርቀ ብርሃን ወልደ ሳሙኤል
በመሠረቱ እስከ አሁን ጊዜ ድረስ ተማሪ ነኝ፤ አንደሚታወቀው ሁሉ ትምህርት አያልቅም፤ ያም ሆነ ይህ ግን ይህን ያህል ተምሬአለሁ ብዬ የምመካበትና የምኩራራበት ነገር አይኖርም፤ ምክንያቱም ወደ ፊት ብዙ መማር የለብኝ ሰው ነኝ፤ የእኔ ወደ እግዚአብሔር ቤት መምጣት መንፈሳዊ ጥሪ ነው፤ እንደ እኔ መንፈሳዊ ጥሪ ያላቸው በርካታ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ፤ የእኔ መንፈሳዊ ጥሪ ግን ለየት ይላል፤ የሥጋ ወላጆቼ በመጀመሪያ ያስገቡኝ ወደ መንፈሳዊ ትምህርት ነው፤ ከዚያ ስማር ከቆየሁ በኋላ በአጋጣሚ ዘመኑ ተቀየረና ዘመናዊ ትምህርት ቤት እየገሰገሰ በሚመጣበት ጊዜ በወቅቱ የነበሩትን ጓደኞቼን በማየት መንፈሳዊ ትምህርቱን አቋርጬ ወደ ዘመናዊ ትምህርት ቤት በመግባት የአንደኛ ደረጃ ትምህርቴን ካጠናቀቅሁ በኋላ እንደገና በመንፈስ ቅዱስ ጥሪ ወደ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ተመለስኩኝ፤ ከዚያም ከተወለድኩበት ሀገር ተነስቼ አርባዕቱ እንስሳ ወደ ሚባል አንድ ትልቅ ገዳም ሄድኩኝ፤ በጊዜው ለጋ ህፃን ነበርኩኝ፤ በገዳሙ የነበሩ አንድ መናኝ አባት ልትማር ትፈልጋለህን ብለው ሲጠይቁኝ አዎ አልኩአቸው፤ ከሳቸው ዓመት ከስድስት ወር እስከ ጸዋትዎ ዜማ ድረስ ተማርኩኝ፤ ከዚያም በኋላ ከብፁዕ አቡነ ናትናኤል አክሱም ጽዮን የዲቁና ማዕረግ ተቀበልኩኝ፤ ከዚያም በኋላ አባ ተስፋ ማርያም የሚባሉ መነኩሴ ስንቅ ሰጥተው ወደ ደብር ዓባይ ላኩኝ፤ በዚያም የቅዳሴ ትምህርት ተምሬ እንደጨረስኩኝ በገዳሙ በልዩ ልዩ አገልግሎት ገዳሙን ረዳሁ፤ በዚሁ መሠረት በገዳሙ ሥርዓት ተፈቅዶልኝ ወደ ምንኩስናው ዓለም ገባሁ፤ ከምንኩስናው በኋላ የገዳሙ ቁጥጥር ኃላፊ በመሆን ወደ አገልግሎቱ ተሰማራሁ፤
በዚህ አገልግሎት ከቆየሁ በኋላ በመንፈስ ቅዱስ ጥሪ መሠረት ከገዳሙ ተነስቼ ወደ ጎንደር በመሄድ ወገራ ሳሙኤል ከሚባል ቦታ በቅዳሴ መምህርነት አስተምህር ነበር፤ ከዚያም በኋላ ወደ ቅኔ ትምህርት ቤት ሄጄ መንክር ግጨው ከሚባሉ የቅኔ መምህር ቅኔ ከእነ አገባቡ በመማር በመምህርነት ተመርቄአለሁ፤ አገባቦችንም ጽፌአለሁ፤ በወቅቱ የሰሜን ጎንደር ሊቀ ጳጳስ በነበሩት በብፁዕ አቡነ ያዕቆብ ዘመን ጎንደር ጭልጋ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን በቅኔ መምህርነት ተመድቤ ሳስተምር ቆይቻለሁ፤ ከዚያም የማስተማር ሥራውን ትቼ ወደ መንበረ መንግሥት መድኃኔዓለም መጥቼ የሐዲሳት ትምህርት ስማር ቆይቼ በወቅቱ በነበረው የፖለቲካ አለመረጋጋት ምክንያት በአካባቢው ሰላም ስላልነበር ወደ አዲስ አበባ መጣሁ፤ በዚያም ወቅት አቡነ ያዕቆብን አቃቤ መንበር ሆነው ስለአገኘኋቸው በእሳቸው መልካም ፈቃድ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የስብከተ ወንጌል ክፍል ኃላፊ ሆኜ ተመድቤ ሠርቻለሁ፡፡ ከዚያ በኋላ ወደ ሰሜን አሜሪካ ተጉዤ በዚያ አብያተ ክርስቲያናትን ብዙ ሳገለግል ቆይቼአለሁ፡፡
ምን እንኳን ወደ ልዩ ጽ/ቤት የመጡት በቅርብ ጊዜ ቢሆንም ወደ ፊት ሊሠሯቸው ያቀዱአቸው ወይም ያሰቧቸው ዋና ዋና ሥራዎች አሉ? ካሉ ቢገልፁልኝ?
ቆሞስ አባ ሠርቀ ብርሃን ወልደ ሳሙኤል
በመጀመሪያ የብፁዕ ወቅዱስ አባታችን ጸሎትና በረከት እንደማይለየኝና እንደሚረዳኝ አምናለሁ፡፡ የብዙ ዓመታት ልምድ ካላቸው ብፁዓን አባቶች ለምሳሌ እንደ ብፁዕ አቡነ ገሪማ መመሪያ በመቀበልና የእነሱን ድጋፍ በመተማመን በንቡረዕድ ኤልያስ አብርሃ የተዘጋጀውን የ2009 ዓ.ም ዕቅድ መሠረት በማድረግ፣ በማስፋፋትና በማጉላት ለመሥራት ታቅዷል፡፡
ይህ ጽ/ቤት ትልቅ ተቋም እንደመሆኑ መጠንና ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን ካላቸው ትልቅ ኃላፊነት የቤተ ክርስቲያንዋም እንደ ራሴ እንደመሆናቸው መጠን በሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም የሚዳረስ አጀንዳ ይዘው እንዲወጡና ዓለም አቀፋዊ አጀንዳ እንዲኖራቸው ለማድረግ ታቅዷል፡፡ በ2009 ዓ.ም ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን ለሰላምና ለፍቅር ዓለም አቀፋዊ ጫና ፈጣሪ እንዲሆኑ ታቅዷል፡፡ በሀገር ደረጃ የተለመደው እንዳለ ሆኖ ታላላቅ ኮንፈረንሶችን በማዘጋጀት፣ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት የመወያያ መድረኮችን በመክፈት፣ በኢኮኖሚአዊ፣ በማኅበራዊ ዙሪያ ሥራ ለመሥራት ይህንን እያቀድን ነው ያለነው፡፡
በዚህም ዕቅዳችን በርካታ ኤክስፐርቶች እንዲካተቱበት ይደረጋል ብለን በዕቅድ ይዘነዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን ደምቃ እንድትወጣ እና ቅዱስ አባታችንም ከሌሎቹ ተሰሚነት አላቸው ከሚባሉት ሁሉ የተሻለ ውጤት እንዲያሳዩ ለማድረግ ታቅዷል፡፡
የሚአስተላልፉት መልእክት አለ?
ቆሞስ አባ ሠርቀ ብርሃን ወልደ ሳሙኤል
መንፈሳዊ መሪዎች ከአምላካችንና ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ በተማርነው መሠረት እኛ አገልጋዮች እንጂ ተገልጋዮች አይደለንም፡፡ ጌታም ያስተማረው ይህንኑ ነው፡፡ እኔም ወደዚህ ስመጣ ሕዝብን ለማገልገል ነው፡፡
ስለዚህ ከላይ እስከ ታች ወቅቱን በመዋጀት ሕዝባችንን በታማኝነትና በተጠያቂነት ማገልገል አለብን፡፡ በተለይ የብፁዕ ወቅዱስ አባታችንን ራዕይ ለማስፈጸም ልንተጋ ይገባናል፡፡
ቅዱስ አባታችን ከሙስና የጸዱ እጆች ይፈልጋሉ፡፡ ስለዚህ እነዚህን ነገሮች የተጸየፈ አሠራር እንዲኖረን ያስፈልጋል፡፡ በሁሉም አርአያ መሆን አለብን፡፡ በዘመናችን በአባቶች ላይ የሚደረገው የስም ማጥፋት ዘመቻ አሳሳቢ ነው፡፡ ይህም ቤተ ክርስቲያንን የማፍረስ ሥራ ነውና በትልቁ ሊታሰብበት ይገባል፡፡ ቤተ ክርስቲያንናችን የራሷ መመሪያ አላት፡፡ ይህም ምስጢረ ክህነት ይባላል፡፡ አንድ ዲያቆን ሲአጠፋ የሚቀጣበት መንገድ አለው፡፡ አንድ ካህን ሲአጠፋ የሚቀጣበት መንገድ አለው ከዘያም በላይ ያለው ሁሉ ሲአጠፉ የሚከሰስበትና የሚቀጣበት መመሪያ አለው፡፡
ይህ ሆኖ እያለ ሰውን ያጠቃን እየመሰለን የቤተ ክርስቲያንን መመሪያ እየተጣስን ነው ያለነው፡፡ ጌታ በወንጌል የተናገረው ብርሃናችሁ በሰው ሁሉ ፊት ይብራ ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ደግሞ “ወበእንቲአክሙ ይጸርፉ አሕዛብ ላዕለ ስመ እግዚአብሔር” እግዚብሔርን የማያውቁ አሕዛብ በእናንተ መጥፎ ተግባር ስመ እግዚአብሔርን ይሰድባሉ ተብሏል፡፡ ዛሬም ስመ እግዚአብሔርን፣ አባቶችንና ቤተ ክርስቲያንን ለመሳደብ የተሰማሩ ወገኖች ቆም ብለው በማሰብ ከማን ጋራ እየታገሉ እንደሆነ ሊያስቡ ይገባል እላለሁ፡፡
ኆኅተ ጥበብ ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ
ስለሰጡን ማብራሪያ ከልብ እናመሰግናለን፡፡